ለዮሐንስ የተገለጠለት ራእይ 13:1-18

  • ሰባት ራሶች ያሉት አንድ አውሬ ከባሕር ወጣ (1-10)

  • ሁለት ቀንዶች ያሉት አውሬ ከምድር ወጣ (11-13)

  • ሰባት ራሶች ያሉት አውሬ ምስል (14, 15)

  • የአውሬው ምልክትና ቁጥር (16-18)

13  እሱም* በባሕር አሸዋ ላይ ቆመ። እኔም አሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ያሉት አንድ አውሬ+ ከባሕር+ ሲወጣ አየሁ፤ በቀንዶቹም ላይ አሥር ዘውዶች የነበሩት ሲሆን በራሶቹ ላይ አምላክን የሚሰድቡ ስሞች ነበሩት።  ያየሁትም አውሬ ነብር ይመስል ነበር፤ እግሮቹ ግን የድብ እግር፣ አፉ ደግሞ የአንበሳ አፍ ይመስል ነበር። ዘንዶውም+ ለአውሬው ኃይልና ዙፋን እንዲሁም ታላቅ ሥልጣን ሰጠው።+  እኔም አየሁ፤ ከአውሬው ራሶች አንዱ የሞተ ያህል እስኪሆን ድረስ ቆስሎ ነበር፤ ሆኖም ለሞት የሚዳርገው ቁስሉ ዳነ፤+ ምድርም ሁሉ አውሬውን በአድናቆት ተከተለው።  ሰዎችም ዘንዶው ለአውሬው ሥልጣን ስለሰጠው ዘንዶውን አመለኩ፤ እንዲሁም “እንደ አውሬው ያለ ማን ነው? ከእሱስ ጋር ማን ሊዋጋ ይችላል?” በማለት አውሬውን አመለኩ።  እሱም የትዕቢት ቃል የሚናገርበትና አምላክን የሚሳደብበት አፍ ተሰጠው፤ ደግሞም ለ42 ወር የፈለገውን እንዲያደርግ ሥልጣን ተሰጠው።+  አምላክን ለመሳደብ+ ይኸውም የአምላክን ስምና የአምላክን መኖሪያ እንዲሁም በሰማይ የሚኖሩትን ለመሳደብ አፉን ከፈተ።+  ቅዱሳኑን እንዲዋጋና ድል እንዲያደርጋቸው ተፈቀደለት፤+ ደግሞም በነገድ፣ በሕዝብ፣ በቋንቋና በብሔር ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው።  በምድር ላይ የሚኖሩም ሁሉ ያመልኩታል። ዓለም ከተመሠረተበት* ጊዜ ጀምሮ የአንዳቸውም ስም በታረደው በግ+ የሕይወት መጽሐፍ ጥቅልል+ ላይ አልሰፈረም።  ጆሮ ያለው ካለ ይስማ።+ 10  ማንም ሰው መማረክ ካለበት ይማረካል። በሰይፍ የሚገድል ካለ* በሰይፍ መገደል አለበት።+ ቅዱሳን+ ጽናትና+ እምነት ማሳየት+ የሚያስፈልጋቸው እዚህ ላይ ነው። 11  ከዚያም ሌላ አውሬ ከምድር ሲወጣ አየሁ፤ እሱም እንደ በግ ሁለት ቀንዶች ነበሩት፤ ሆኖም እንደ ዘንዶ+ መናገር ጀመረ። 12  በመጀመሪያው አውሬ ፊት የመጀመሪያውን አውሬ+ ሥልጣን ሙሉ በሙሉ ይጠቀማል። ምድርና የምድር ነዋሪዎች፣ ለሞት የሚዳርገው ቁስል የዳነለትን+ የመጀመሪያውን አውሬ እንዲያመልኩ ያደርጋል። 13  በሰው ልጆችም ፊት ታላላቅ ምልክቶችን ይፈጽማል፤ እሳትንም እንኳ ከሰማይ ወደ ምድር ያወርዳል። 14  በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች በሰይፍ ቆስሎ ለነበረው በኋላ ግን ላገገመው+ አውሬ፣ ምስል+ እንዲሠሩ እያዘዘ በአውሬው ፊት እንዲፈጽማቸው በተፈቀዱለት ምልክቶች አማካኝነት በምድር ላይ የሚኖሩትን ያስታል። 15  እንዲሁም ለአውሬው ምስል እስትንፋስ* እንዲሰጠው ተፈቀደለት፤ ይህም የሆነው የአውሬው ምስል መናገር እንዲችልና የአውሬውን ምስል የማያመልኩትን ሁሉ እንዲያስገድል ነው። 16  ሰዎች ሁሉ ማለትም ታናናሾችና ታላላቆች፣ ሀብታሞችና ድሆች እንዲሁም ነፃ ሰዎችና ባሪያዎች በቀኝ እጃቸው ወይም በግንባራቸው ላይ ምልክት እንዲደረግባቸው አስገደደ፤+ 17  ይህም የሆነው ምልክቱ ይኸውም የአውሬው ስም+ ወይም የስሙ ቁጥር+ ካለው ሰው በስተቀር ማንም መግዛት ወይም መሸጥ እንዳይችል ነው። 18  ጥበብ የሚያስፈልገው እዚህ ላይ ነው፦ የማስተዋል ችሎታ ያለው ሰው የአውሬውን ቁጥር ያስላ፤ ቁጥሩ የሰው ቁጥር ነውና፤ ቁጥሩም 666 ነው።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ዘንዶውን ያመለክታል።
ይህ አባባል የአዳምንና የሔዋንን ዘሮች ያመለክታል።
“በሰይፍ የሚገደል ካለ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “መንፈስ።”