በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የኤላህ ሸለቆ

ዳዊትና ጎልያድ—ታሪኩ እውነት ነው?

ዳዊትና ጎልያድ—ታሪኩ እውነት ነው?

አንዳንድ ሰዎች ስለ ዳዊትና ስለ ጎልያድ የሚናገረው ዘገባ እውነተኛ ታሪክ ስለመሆኑ ይጠራጠራሉ። አንተስ ከዚህ በፊት የነበረውን ርዕስ ስታነብ እንዲህ ያለ ጥያቄ ተፈጥሮብህ ይሆን? ከሆነ ቀጥሎ የቀረቡትን ሦስት ጥያቄዎች እንድትመረምር እንጋብዝሃለን።

1 | በእርግጥ 2.9 ሜትር ገደማ ርዝመት ያለው ሰው ሊኖር ይችላል?

መጽሐፍ ቅዱስ የጎልያድ ቁመት “ስድስት ክንድ ከአንድ ስንዝር” እንደነበረ ይናገራል። (1 ሳሙኤል 17:4) እዚህ ላይ የተጠቀሰው ክንድ 44.5 ሳንቲ ሜትር ርዝመት አለው፤ ስንዝር ደግሞ 22.2 ሳንቲ ሜትር ርዝመት አለው። ስለዚህ ጥቅሱ ላይ የተገለጹትን አኃዞች ስንደምራቸው 2.9 ሜትር ይሆናሉ። አንዳንዶች ጎልያድ ያን ያህል ርዝመት ሊኖረው እንደማይችል ይናገራሉ፤ ይሁን እንጂ እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ በዘመናችን የዓለማችን ረጅም ሰው ተብሎ በታሪክ መዝገብ የሠፈረው ሰው ቁመቱ 2.7 ሜትር ነው። ታዲያ ከዚህ ሰው በ15 ሳንቲ ሜትር ብቻ የሚበልጠው የጎልያድ ቁመት ለማመን የሚከብድ ነው? ጎልያድ የረፋይም ጎሳ ተወላጅ ሲሆን እነዚህ ሰዎች በጣም ግዙፍ በመሆናቸው ይታወቃሉ። በ13ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የተዘጋጀ አንድ የግብፃውያን ሰነድ፣ በከነዓን ክልል የነበሩ አንዳንድ አስፈሪ ጦረኞች ቁመታቸው ከ2.4 ሜትር በላይ እንደነበረ ይጠቅሳል። እርግጥ የጎልያድ ቁመት ያልተለመደ ነው፤ ሆኖም ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ግን አይደለም።

2 | ዳዊት በሕይወት ኖሮ የሚያውቅ ሰው ነው?

አንዳንድ ምሁራን ንጉሥ ዳዊት በምናብ የተፈጠረ ሰው እንደሆነ አድርገው ለመናገር ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም። ምክንያቱም የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች “የዳዊት ቤት” የሚል ትርጉም ያለው ጽሑፍ የተቀረጸበት በጣም ጥንታዊ የሆነ ድንጋይ በቁፋሮ አግኝተዋል። ከዚህም በላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳዊት በሕይወት ኖሮ የሚያውቅ ሰው እንደነበረ ተናግሯል። (ማቴዎስ 12:3፤ 22:43-45) በተጨማሪም ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ለይተው የሚያሳውቁ ሁለት የዘር ሐረግ ዝርዝሮች፣ ኢየሱስ የመጣው ከንጉሥ ዳዊት የዘር ሐረግ እንደሆነ ይናገራሉ። (ማቴዎስ 1:6-16፤ ሉቃስ 3:23-31) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ዳዊት በሕይወት ኖሮ የሚያውቅ ሰው ነው።

3 | በታሪኩ ውስጥ የተገለጹት ቦታዎች በገሐዱ ዓለም ያሉ ናቸው?

መጽሐፍ ቅዱስ ውጊያው በኤላህ ሸለቆ እንደተካሄደ ይናገራል። ይሁን እንጂ ዘገባው ከዚያም አልፎ ፍልስጤማውያን የሰፈሩት ሶኮህና አዜቃ በሚባሉ ሁለት ከተሞች መካከል በሚገኝ ስፍራ እንደነበረ በመግለጽ ዝርዝር ጉዳዮችን ይናገራል። እስራኤላውያን በተቃራኒው አቅጣጫ ኮረብታው ላይ ሰፍረው ነበር። ታዲያ እነዚህ ቦታዎች በእውን የነበሩ ስፍራዎች ናቸው?

በቅርቡ ወደ አካባቢው ለጉብኝት ሄዶ የነበረ አንድ ሰው የተናገረውን ልብ በል፦ “አስጎብኚያችን ወደ ኤላህ ሸለቆ ወሰደን፤ ሰውየው ሃይማኖተኛ ሰው አይደለም። ወደ አንድ ኮረብታ አፋፍ የሚወስደንን መንገድ ይዘን ሽቅብ መውጣት ጀመርን። አሻግረን ሸለቆውን እየተመለከትን እያለ 1 ሳሙኤል 17:1-3⁠ን እንድናነብ አደረገን። ከዚያም ወደ ሸለቆው ማዶ እያመለከተ ‘እዚያ ማዶ በስተ ግራ በኩል የምታዩት የሶኮህ ፍርስራሽ ነው’ አለን። ዞር ብሎ ‘እዚያ በስተ ቀኝ በኩል የምታዩት ደግሞ የአዜቃ ፍርስራሽ ነው። ፍልስጤማውያን ሰፍረው የነበሩት ከማዶ በምታዩአቸው በእነዚያ ሁለት ከተሞች መካከል ባለ ኮረብታ ላይ ነው። ስለዚህ አሁን የቆምነው እስራኤላውያን ሰፍረው በነበረበት ቦታ ላይ ሳይሆን አይቀርም’ አለ። እዚያው በቆምኩበት ቦታ ሆኜ ስለ ሳኦልና ዳዊት ማሰብ ጀመርኩ። ከዚያም ቁልቁል ወረድንና በድንጋይ የተሞላውንና በአብዛኛው ደረቅ የሆነውን በሸለቆ ውስጥ የሚያልፍ ወንዝ ተሻገርን። ዳዊት ጎልያድን የገደለበትን ድንጋይ ጨምሮ አምስት ድቡልቡል ድንጋዮች አጎንብሶ ሲለቅም በዓይነ ሕሊናዬ ይታየኝ ነበር።” ይህ ጎብኚ እንደ ሌሎች ጎብኚዎች ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ በሰፈረው ዝርዝር ታሪክ እውነተኝነት በጣም ተደንቋል።

የዚህን ታሪካዊ ዘገባ እውነተኝነት እንድንጠራጠር የሚያደርግ ምንም ነገር የለም። በታሪኩ ላይ የተጠቀሱት ሰዎችም ሆነ ቦታዎች በገሐዱ ዓለም የነበሩ ናቸው። ከሁሉም የበለጠው ማስረጃ ግን ታሪኩ አምላክ በመንፈሱ መሪነት ባስጻፈው ቃሉ ውስጥ የሚገኝ መሆኑ ነው፤ ያስጻፈው “ሊዋሽ የማይችለው” የእውነት አምላክ ነው።—ቲቶ 1:2፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16