በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምትወደው ሰው ሲሞት

የምትወደው ሰው ሲሞት

“ታላቅ ወንድሜ በድንገት ሲሞት፣ የምይዘው የምጨብጠው ጠፍቶኝ ነበር። ወራት ካለፉ በኋላም እንኳ ወንድሜ ትዝ ሲለኝ በጩቤ የተወጋሁ ያህል ሕመም ይሰማኝ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በጣም እበሳጫለሁ። ‘ወንድሜ እንዴት ይሞታል?’ ብዬ አስባለሁ። እንዲሁም በሕይወት ሳለ አብሬው ብዙ ጊዜ ባለማሳለፌ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማኝ ነበር።”—ቫኔሳ፣ አውስትራሊያ

አንተም የምትወደውን ሰው በሞት አጥተህ ከሆነ የተለያዩ ስሜቶች ሊፈራረቁብህ ይችላሉ፤ ሐዘን፣ ብቸኝነትና የከንቱነት ስሜት ይሰማህ ይሆናል። በተጨማሪም ልትበሳጭ፣ የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማህና ፍርሃት ሊያድርብህ አልፎ ተርፎም ‘በሕይወት መኖሬ ምን ዋጋ አለው?’ ብለህ ልታስብ ትችላለህ።

በሐዘን መደቆስህ የድክመት ምልክት እንዳልሆነ እርግጠኛ ሁን። ከዚህ ይልቅ በሞት ያጣኸውን ሰው ምን ያህል ትወደው እንደነበር የሚያሳይ ነው። ይሁንና ከዚህ ጥልቅ ሐዘን በተወሰነ መጠንም ቢሆን መጽናናት የምትችልበት መንገድ ይኖር ይሆን?

አንዳንዶች መጽናናት የቻሉት እንዴት ነው?

ሥቃይህ ማባሪያ የሌለው ሊመስልህ ቢችልም ቀጥሎ የቀረቡትን ምክሮች ተግባራዊ ማድረግህ ከሐዘንህ እንድትጽናና ሊረዳህ ይችላል፦

አዝነህ ይውጣልህ

ሰዎች ሐዘናቸውን የሚገልጹበት መንገድ የተለያየ ነው፤ ከሐዘናቸው ለመጽናናት የሚፈጅባቸው ጊዜም ቢሆን ይለያያል። በጥቅሉ ሲታይ ግን ማልቀስ በውስጥህ የታመቀው ሐዘን እንዲወጣልህ ሊያደርግ ይችላል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ቫኔሳ “ዝም ብዬ የማለቅስበት ጊዜ አለ፤ በውስጤ የሚሰማኝን ሥቃይ ማስተንፈስ እፈልጋለሁ” ብላለች። እህቷ በድንገት የሞተችባት ሶፊያ የተባለች ሴት ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “የተፈጠረውን ነገር መለስ ብሎ ማሰብ፣ የመረቀዘ ቁስልን ከፍቶ የማጽዳት ያህል በጣም የሚያም ነገር ነው። ሕመሙ ልቋቋመው ከምችለው በላይ እንደሆነ ቢሰማኝም ቁስሉ ሊሽር የሚችለው እንዲህ ካደረግኩ ብቻ ነው።”

የውስጥህን ሐሳብና ስሜትህን አውጥተህ ተናገር

አንዳንድ ጊዜ ብቻህን መሆን ልትፈልግ እንደምትችል የታወቀ ነው። ሆኖም ሐዘን፣ ብቻህን ልትሸከመው የማትችለው ከባድ ሸክም ነው። አባቱን በሞት ያጣው የ17 ዓመቱ ጃሬድ እንዲህ ብሏል፦ “የተሰማኝን ስሜት አውጥቼ እናገር ነበር። የምናገረው ነገር ትርጉም ሰጠም አልሰጠ ሐሳቤን መግለጽ መቻሌ በራሱ ጠቅሞኛል።” በመጀመሪያው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው ጃኒስ ስሜትን አውጥቶ መናገር ያለውን ሌላ ጥቅም ስትናገር “ከሌሎች ጋር ማውራቴ በጣም አጽናንቶኛል። ስሜቴን የሚረዳልኝ ሰው እንዳለ እንዳውቅና ብቸኝነት እንዳይሰማኝ ረድቶኛል” ብላለች።

የሌሎችን እርዳታ ለመቀበል ፈቃደኛ ሁን

የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑ አንድ ሐኪም እንዲህ ብለዋል፦ “ሐዘኑ ገና ትኩስ ባለበት ወቅት የጓደኞቻቸውንና የዘመዶቻቸውን እርዳታ ለመቀበል ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ሐዘናቸውን በተሻለ ሁኔታ መቋቋም ይችላሉ።” ስለዚህ ወዳጆችህ ምን ዓይነት እርዳታ ሊያደርጉልህ እንደሚችሉ ንገራቸው፤ ምናልባት እነሱም ሊረዱህ ፈልገው በምን መንገድ እንደሚረዱህ ግራ ገብቷቸው ሊሆን ይችላል።—ምሳሌ 17:17

ወደ አምላክ ይበልጥ ቅረብ

ቲና እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ባለቤቴ ድንገት በካንሰር ከሞተ በኋላ እንደቀድሞው ችግሮቼንና ጭንቀቶቼን ላዋየው ስለማልችል ሁሉንም ነገር ለአምላክ እነግረው ጀመር! እያንዳንዱን ቀን እንደ ምንም ብዬ ማለፍ እንድችል እንዲረዳኝ አምላክን እለምነው ነበር። እሱም ዘርዝሬ ልጨርስ ከምችለው በላይ በብዙ መንገድ ረድቶኛል።” በ22 ዓመቷ እናቷን በሞት ያጣችው ታርሻ እንዲህ ብላለች፦ “በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቤ በእጅጉ አጽናንቶኛል። መጽሐፍ ቅዱስን ሳነብ፣ ላሰላስልበት የምችለው አበረታች ሐሳብ አገኛለሁ።”

የምትወደው ሰው ከሞት የሚነሳበት ጊዜ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ

ቲና አክላም እንዲህ ብላለች፦ “መጀመሪያ ላይ የትንሣኤ ተስፋ ያን ያህል አያጽናናኝም ነበር። ምክንያቱም ባለቤቴ አሁኑኑ ከጎኔ እንዲሆን እፈልግ ነበር፤ ልጆቼም ቢሆኑ አባታቸው ያስፈልጋቸዋል። አሁን አራት ዓመት ካለፈ በኋላ ግን የትንሣኤ ተስፋ በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ቦታ የምሰጠው ነገር ሆኗል። ቀጥ አድርጎ ያቆመኝ ይህ ተስፋ ነው። ባለቤቴን ዳግመኛ የማገኝበት ጊዜ በዓይነ ሕሊናዬ ይታየኛል፤ ይህም ውስጣዊ ሰላምና ደስታ ይሰጠኛል!”

እርግጥ ነው፣ እነዚህን ነገሮች ብታደርግም ወዲያውኑ ከሐዘንህ ላትጽናና ትችላለህ። ሆኖም የቫኔሳ ተሞክሮ፣ ተስፋ እንዳትቆርጥ ይረዳሃል። ቫኔሳ እንዲህ ብላለች፦ “ከሐዘናችሁ ፈጽሞ ልትጽናኑ እንደማትችሉ ይሰማችሁ ይሆናል፤ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ግን ሐዘኑ ቀለል ይልላችኋል።”

የምትወደውን ሰው በሞት ማጣትህ የፈጠረብህን የባዶነት ስሜት ማስወገድ ባትችል እንኳ በሕይወትህ ደስተኛ መሆን እንደምትችል እርግጠኛ ሁን። ሩኅሩኅ የሆነው አምላክ እርዳታ ስለማይለይህ ከወዳጆችህ ጋር አስደሳች ጊዜ ማሳለፍና ዓላማ ያለው ሕይወት መምራት ትችላለህ። በቅርቡ ደግሞ አምላክ በሞት ያንቀላፉትን ሰዎች ያስነሳቸዋል። አምላክ፣ የሞተብህን ሰው መልሰህ እንድታገኝ ይፈልጋል። በዚያን ጊዜ፣ በሐዘን የቆሰለው ልብህ ሙሉ በሙሉ ይፈወሳል!