በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ታላቂቱ ባቢሎን የአምላክን ሕዝቦች በምርኮ ይዛ የነበረው መቼ ነው?

ይህ መንፈሳዊ ምርኮ ከሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. እስከ 1919 ቆይቷል። ለመሆኑ በግንዛቤያችን ላይ እንዲህ ዓይነት ማስተካከያ ማድረጋችን ተገቢ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

ይህ ምርኮ ያበቃው ቅቡዓን ክርስቲያኖች በ1919 እንደገና በተቋቋመው ጉባኤ ውስጥ በተሰበሰቡበት ወቅት እንደሆነ ማስረጃዎቹ በአጠቃላይ ይጠቁማሉ። እስቲ የሚከተሉትን ነገሮች አስብ፦ የአምላክ ሕዝቦች፣ የአምላክ መንግሥት በ1914 በሰማይ ከተቋቋመ በኋላ በነበሩት ዓመታት ተፈትነዋል እንዲሁም ጠርተዋል። * (ሚል. 3:1-4) ከዚያም በ1919 ኢየሱስ ለነጹት የአምላክ ሕዝቦች ‘በተገቢው ጊዜ መንፈሳዊ ምግብ’ የሚሰጥ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሾመ። (ማቴ. 24:45-47) የአምላክ ሕዝቦች፣ አምላክ ወደሰጣቸው መንፈሳዊ ርስት መመለስ የጀመሩት በዚህ ዓመት ነው። ከታላቂቱ ባቢሎን መንፈሳዊ ምርኮ ነፃ የወጡትም በዚሁ ጊዜ ነበር። (ራእይ 18:4) ይሁንና በምርኮ የተወሰዱበት ትክክለኛ ጊዜ መቼ ነበር?

ለበርካታ ዓመታት፣ የአምላክ ሕዝቦች በባቢሎን ምርኮ የተያዙት ከ1918 ጀምሮ እንደነበረና ይህም ለአጭር ጊዜ እንደዘለቀ ስንገልጽ ቆይተናል። ለምሳሌ ያህል፣ በመጋቢት 15, 1992 መጠበቂያ ግንብ ላይ እንዲህ የሚል ሐሳብ ወጥቶ ነበር፦ “የአምላክ ጥንታዊ ሕዝቦች ለጊዜው ወደ ባቢሎናዊ ምርኮ ተወስደው እንደነበረ ሁሉ የይሖዋ አገልጋዮችም በ1918 በታላቂቱ ባቢሎን እስራት ስር ወድቀው ነበር።” ይሁን እንጂ በዚህ ጉዳይ ላይ የተደረገ ተጨማሪ ምርምር ይህ ምርኮ የጀመረው ከ1918 በጣም ቀደም ብሎ እንደነበር አሳይቷል።

ለምሳሌ የአምላክ ሕዝቦች በምርኮ እንደሚወሰዱና ነፃ እንደሚወጡ ከሚናገሩት ትንቢቶች መካከል አንዱን እንመልከት። ትንቢቱ በሕዝቅኤል 37:1-14 ላይ ይገኛል። ይህ ዘገባ ሕዝቅኤል በአጥንቶች የተሞላ ሸለቆ በራእይ እንደተመለከተ ይናገራል። ይሖዋ እነዚህ አጥንቶች ‘መላውን የእስራኤል ቤት’ እንደሚያመለክቱ ለሕዝቅኤል ነግሮታል። ሆኖም ስለ መልሶ መቋቋም የሚናገረው ይህ ትንቢት የላቀ ፍጻሜውን የሚያገኘው “በአምላክ እስራኤል” ላይ ነው። (ገላ. 6:16፤ ሥራ 3:21) በመቀጠልም እነዚህ አጥንቶች ሕያው ሆኑ፤ ከዚያም ታላቅ ሠራዊት ሆነዋል። በእርግጥም ይህ ራእይ የአምላክ ሕዝቦች በ1919 ከታላቂቱ ባቢሎን ምርኮ ነፃ የወጡበትን መንገድ ጥሩ አድርጎ ይገልጻል! ይሁንና የአምላክ ሕዝቦች በምርኮ የሚቆዩበትን የጊዜ ርዝማኔ በተመለከተ ራእዩ የሚነግረን ነገር አለ?

አንደኛ፣ አጥንቶቹ “ደርቀዋል” ወይም “በጣም ደርቀው ነበር” ተብለው እንደተገለጹ ልብ ማለት ያስፈልጋል። (ሕዝ. 37:2, 11) አጥንት ብቻ መገኘቱ ሰዎቹ ከሞቱ በጣም ረጅም ጊዜ እንዳለፋቸው የሚጠቁም ነው። ሁለተኛ፣ እነዚህ አጥንቶች መልሰው ሕያው የሆኑት በአንድ ጊዜ ሳይሆን ቀስ በቀስ እንደሆነ ተገልጿል። መጀመሪያ ላይ “የሚንኮሻኮሽ ድምፅ ተሰማ፤ አጥንቶቹም እርስ በርስ መገጣጠም ጀመሩ።” ከዚያም “ጅማትና ሥጋ” ለበሱ። ቀጥሎም አጥንቶቹ፣ ጅማቶቹና ሥጋው በቆዳ ተሸፈኑ። በኋላም “[እስትንፋስ] ገባባቸው፤ እነሱም ሕያው” ሆኑ። በመጨረሻም ይሖዋ ዳግመኛ ሕያው የሆኑትን ሰዎች በምድራቸው ላይ አሰፈራቸው። እነዚህ ነገሮች ጊዜ እንደሚወስዱ ግልጽ ነው።—ሕዝ. 37:7-10, 14

የጥንቶቹ እስራኤላውያን በምርኮ የቆዩት ረዘም ላለ ጊዜ ነበር። ይህ ወቅት የጀመረው አሥሩን ነገዶች ያቀፈው ሰሜናዊው መንግሥት በ740 ዓ.ዓ. ሲወድቅና ብዙ ሕዝብ በግዞት ሲወሰድ ነው። ከዚያም በ607 ዓ.ዓ. ኢየሩሳሌም ጠፋች፤ በዚህ ጊዜ የደቡባዊው የይሁዳ መንግሥት ነዋሪዎችም በግዞት ተወሰዱ። ይህ ምርኮ ያበቃው በ537 ዓ.ዓ. አይሁዳውያን ቀሪዎች ተመልሰው መጥተው በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደሱን መልሰው በገነቡበትና ንጹሑን አምልኮ እንደገና ባቋቋሙበት ጊዜ ነበር።

እነዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ዝርዝር ጉዳዮች እንደሚያሳዩት የአምላክ ሕዝቦች በታላቂቱ ባቢሎን ምርኮ የቆዩበት ዘመን ረጅም መሆን አለበት፤ በመሆኑም ከ1918-1919 ያለው ጊዜ ብቻ ሊሆን አይችልም። የምርኮው ወቅት ኢየሱስ በዘሪው ምሳሌ ላይ የጠቀሰው እንክርዳድ፣ ከስንዴው ማለትም ‘ከመንግሥቱ ልጆች’ ጋር አብሮ ከሚያድግበት ጊዜ ጋር ተመሳሳይ ነው። (ማቴ. 13:36-43) ስንዴውና እንክርዳዱ አብረው ባደጉበት ወቅት የከሃዲዎች ቁጥር ከእውነተኛ ክርስቲያኖች ቁጥር እጅግ በልጦ ነበር። በመሆኑም የክርስቲያን ጉባኤ በታላቂቱ ባቢሎን በምርኮ ተይዞ ነበር ሊባል ይችላል። ይህ ምርኮ በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. የጀመረ ሲሆን መንፈሳዊው ቤት መቅደስ እስከነጻበት እስከ ፍጻሜው ዘመን ድረስ ቀጥሏል።—ሥራ 20:29, 30፤ 2 ተሰ. 2:3, 6፤ 1 ዮሐ. 2:18, 19

መንፈሳዊ ምርኮው በቀጠለበት በዚህ ረጅም ጊዜ ቀሳውስትና ሥልጣናቸውን ማስነካት የማይፈልጉት የፖለቲካ አጋሮቻቸው በሥራቸው ያለው ሕዝብ የአምላክን ቃል እንዳያነብ አግደው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ተራው ሕዝብ በሚግባባበት ቋንቋ ማንበብ እንደ ወንጀል የሚቆጠርበት ጊዜ ነበር። እንዲያውም አንዳንዶች እንዲህ በማድረጋቸው እንጨት ላይ ተሰቅለው ተቃጥለዋል። ቀሳውስቱ ከሚያስተምሩት ነገር የተለየ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ከፍተኛ ቅጣት ይደርስባቸው ስለነበር የእውነትን ብርሃን ለማዳረስ የሚደረገው ጥረት ተፈታታኝ ሆኖ ነበር።

ስለ ሁለተኛው ነጥብ ማለትም በራእዩ ላይ መልሶ ስለ መቋቋም የሚገልጸው ሐሳብ የተፈጸመው መቼና እንዴት ነበር? የአምላክ ሕዝቦች በመንፈሳዊ ያንሰራሩት ቀስ በቀስ ነበር። ራእዩ “የሚንኮሻኮሽ ድምፅ” እንደተሰማ ይናገራል፤ ይህ ድምፅ መሰማት የጀመረው ደግሞ ከፍጻሜው ዘመን በፊት ባሉት ጥቂት መቶ ዓመታት ውስጥ ነበር። በእነዚያ ዓመታት የሐሰት ትምህርት ከፍተኛ ተሰሚነት የነበረው ቢሆንም አንዳንድ ታማኝ ሰዎች አቅማቸው እስከፈቀደ ድረስ ለእውነተኛው አምልኮ ጥብቅና ቆመዋል። አንዳንዶቹ ተራው ሕዝብ በሚጠቀምበት ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎም ጥረት አድርገዋል። ሌሎች ደግሞ የአምላክን ቃል ሲያነቡ ያገኟቸውን እውነቶች አውጀዋል።

ከዚያም በ1800ዎቹ መገባደጃ ላይ ቻርልስ ቴዝ ራስልና አጋሮቹ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንዲታወቅ በቅንዓት እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመሩ። መንፈሳዊው አጽም በምሳሌያዊ ሁኔታ ሥጋና ቆዳ መልበስ የጀመረ ያህል ነበር። ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በጽዮን መጠበቂያ ግንብ እና በሌሎች ጽሑፎች አማካኝነት መንፈሳዊ እውነቶችን ማወቅ ችለዋል። በኋላ ደግሞ በ1914 መታየት የጀመረው “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” እንዲሁም በ1917 የወጣው ያለቀለት ሚስጥር (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍም ሆነ ሌሎች መሣሪያዎች የአምላክን ሕዝቦች መንፈሳዊነት አጠናክረዋል። በመጨረሻም በ1919 የአምላክ ሕዝቦች በመንፈሳዊ ሕያው ሆኑ፤ ከዚያም በአዲሱ መንፈሳዊ ርስታቸው ሰፈሩ። ውሎ አድሮ፣ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች ከእነዚህ ቅቡዓን ቀሪዎች ጋር ተቀላቀሉ፤ “እጅግ ታላቅ ሠራዊትም ሆኑ።”—ሕዝ. 37:10፤ ዘካ. 8:20-23 *

ከተመለከትናቸው ነጥቦች በመነሳት የአምላክ ሕዝቦች በታላቂቱ ባቢሎን ምርኮ የተያዙት ክህደቱ በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እንደሆነ በግልጽ መረዳት እንችላለን። ይህ ጊዜ እስራኤላውያን በግዞት ከነበሩበት ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል የጨለማ ዘመን ነበር። ይሁንና የአምላክ ሕዝቦች ለዘመናት መንፈሳዊ ጭቆና ሲደርስባቸው ከቆየ በኋላ “ጥልቅ ማስተዋል ያላቸው ሰዎች [በሚያበሩበት]” እንዲሁም ‘ራሳቸውን በሚያጸዱበትና በሚያጠሩበት’ ዘመን ላይ በመኖራችን ምንኛ ደስተኞች ነን!—ዳንኤል 12:3, 10

ሰይጣን ኢየሱስን ሲፈትነው ወደ ቤተ መቅደሱ የወሰደው ቃል በቃል በአካል ነበር?

በአጭር አገላለጽ፣ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደሱ የሄደው በአካል ስለመሆኑ አሊያም ሰይጣን ቤተ መቅደሱን ያሳየው በራእይ ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን አንችልም። ሁለቱም ሁኔታዎች በጽሑፎቻችን ላይ የቀረቡበት ጊዜ አለ።

በመጀመሪያ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባው ምን እንደሚል እንመልከት። ሐዋርያው ማቴዎስ በወንጌል ዘገባው ላይ በመንፈስ መሪነት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ ‘ከዚያም ዲያብሎስ ወደ ቅድስቲቱ ከተማ [ኢየሱስን] ከወሰደው በኋላ በቤተ መቅደሱ አናት [“በቤተ መቅደሱ ጣሪያ ዙሪያ ያለ ግንብ፤ ጫፍ” ግርጌ] ላይ አቆመው።’ (ማቴ. 4:5) ሉቃስ የጻፈው ተመሳሳይ ዘገባ ደግሞ “ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ከወሰደው በኋላ በቤተ መቅደሱ አናት ላይ አቁሞ እንዲህ አለው” ይላል።—ሉቃስ 4:9

ቀደም ሲል ጽሑፎቻችን ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደሱ የተወሰደው በአካል ላይሆን እንደሚችል ይገልጹ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በመጋቢት 1, 1961 መጠበቂያ ግንብ ላይ የሚከተለው ሐሳብ ወጥቷል፦ “ኢየሱስ በምድረ በዳ ስለመፈተኑ በሚናገረው ዘገባ ላይ የተጠቀሰው ነገር ሁሉ ቃል በቃል ተፈጽሟል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይመስልም። ከየትኛውም ተራራ ላይ ሆኖ ለአንድ ሰው ‘የዓለምን መንግሥታት ሁሉና ክብራቸውን’ ማሳየት እንደማይቻል ግልጽ ነው። በተመሳሳይም ሰይጣን ኢየሱስን በአካል ወይም ቃል በቃል ‘ወደ ቅድስቲቱ ከተማ’ ወስዶ ‘በቤተ መቅደሱ አናት ላይ አቁሞታል’ ብሎ መደምደም ምክንያታዊ አይደለም። ፈተናው ክብደት እንዲኖረው እንዲህ ማድረግ አያስፈልገውም።” ይሁንና በዚህ መጽሔት ቀጣይ እትሞች ላይ፣ ኢየሱስ ለሰይጣን ፈተና ተሸንፎ ከቤተ መቅደሱ አናት ላይ ቢዘል ኖሮ ራሱን ሊገድል እንደሚችል ተገልጿል።

አንዳንዶች ኢየሱስ ሌዋዊ ስላልሆነ በቤተ መቅደሱ አናት ላይ መቆም እንደማይፈቀድለት ይናገራሉ። በመሆኑም ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደሱ ‘የተወሰደው’ በራእይ አማካኝነት ሊሆን እንደሚችል ይታሰብ ነበር። ይህ ደግሞ ከበርካታ ዘመናት በፊት ነቢዩ ሕዝቅኤል ካጋጠመው ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው።—ሕዝ. 8:3, 7-10፤ 11:1, 24፤ 37:1, 2

ሆኖም ይህ ፈተና የቀረበው በራእይ መልክ ብቻ ከሆነ የሚከተሉት ጥያቄዎች ይነሳሉ፦

  • ፈተናው እውነተኛ ነው ወይስ ምናባዊ?

  • ኢየሱስ ድንጋዮቹን ወደ ዳቦ እንዲቀይር ወይም አንድ ጊዜ ተደፍቶ እንዲያመልከው ሰይጣን ጠይቆት ነበር፤ በዚህ ጊዜ ሰይጣን የፈተነው ቃል በቃል ድንጋዩን ዳቦ እንዲያደርግ ወይም እንዲሰግድለት ከሆነ ከቤተ መቅደሱ አናት ላይ ራሱን እንዲወረውር ያቀረበው ፈተናም ቃል በቃል ይህን እንዲያደርግ የቀረበ ፈተና መሆን አይኖርበትም?

በሌላ በኩል ደግሞ ኢየሱስ የቤተ መቅደሱ አናት ላይ የቆመው በአካል ከሆነ ሌሎች ጥያቄዎች ይነሳሉ፦

  • ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ አናት ላይ በመቆም ሕጉን ጥሷል?

  • ኢየሱስ ከምድረ በዳው ወደ ኢየሩሳሌም የሄደው እንዴት ነው?

በዚህ ጉዳይ ላይ የተደረገው ተጨማሪ ምርምር የመጨረሻዎቹን ሁለት ጥያቄዎች ለመመለስ ሊረዱን የሚችሉ አንዳንድ ሁኔታዎችን እንድናስብ ያስችለናል።

በመጀመሪያ ደረጃ፣ ፕሮፌሰር ካርሰን እንደተናገሩት በሁለቱም ዘገባዎች ላይ ‘ቤተ መቅደስ’ ተብሎ የተተረጎመው ሂሮን የሚለው የግሪክኛ ቃል የሚያመለክተው “የቤተ መቅደሱን ሕንፃ ብቻ ሳይሆን ግቢው ውስጥ ያሉትን ሕንፃዎች በሙሉ ሊሆን ይችላል።” በመሆኑም ኢየሱስ የቆመው የቤተ መቅደሱ ሕንፃ ላይ ላይሆን ይችላል። ለምሳሌ በቤተ መቅደሱ ግቢ ደቡብ ምሥራቃዊ ጫፍ ላይ ቆሞ ሊሆን ይችላል። ከዚያ ቦታ ቁልቁል እስከ ቄድሮን ሸለቆ ወለል ድረስ ርቀቱ 137 ሜትር ገደማ ነው። በስተ ደቡብ ምሥራቅ የሚገኘው ሕንፃ ጠፍጣፋ ጣርያ ኖሮት ዙሪያውን ማገጃ ግንብ ያለው ሲሆን በቤተ መቅደሱ ውስጥ ካሉት ሁሉ በጣም ረጅሙ ሕንፃ ነው። በጥንት ጊዜ የነበረው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ አንድ ሰው ከዚህ ሕንፃ ላይ ሆኖ ወደታች ቢመለከት ከከፍታው የተነሳ “ሊያዞረው እንደሚችል” ገልጿል። ሌዋዊ ያልሆነው ኢየሱስ እዚህ ቦታ ላይ መቆም አይከለከልም፤ እዚህ ቦታ ላይ ቆሞ መታየቱም ሕዝቡ እንዲቆጣ የሚያደርግ ነገር አይደለም።

ይሁን እንጂ በምድረ በዳ የነበረው ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደሱ ሊወሰድ የቻለው እንዴት ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ በእርግጠኝነት መናገር አንችልም። ስለ ፈተናዎቹ የሚገልጸው አጭር ዘገባ ፈተናው የቆየው ለምን ያህል ጊዜ እንደሆነ ወይም ኢየሱስ በምድረ በዳ ውስጥ የት ቦታ እንደነበረ አይገልጽም። ምናልባትም ኢየሱስ ኢየሩሳሌም ድረስ በእግሩ ተጉዞ ሊሆን ይችላል፤ እርግጥ ይህ ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ግልጽ ነው። በተጨማሪም ዘገባው ኢየሱስ የተፈተነበትን ጊዜ በሙሉ በምድረ በዳ እንዳሳለፈ አይገልጽም። ከዚህ ይልቅ ተመዝግቦ የምናገኘው ወደ ኢየሩሳሌም መወሰዱን የሚገልጽ ሐሳብ ብቻ ነው።

ሰይጣን ለኢየሱስ “የዓለምን መንግሥታት ሁሉ” በማሳየት ስላቀረበው ፈተናስ ምን ማለት ይቻላል? ኢየሱስ እነዚህን መንግሥታት ቃል በቃል እንዳልተመለከተ ግልጽ ነው፤ ምክንያቱም የዓለም መንግሥታት በሙሉ ሊታዩ የሚችሉበት ተራራ የለም። አንድ ሰው የተለያዩ የምድር ክፍሎችን በፕሮጀክተር አማካኝነት ስክሪን ላይ ሊያሳይ እንደሚችል ሁሉ ሰይጣንም ለኢየሱስ እነዚህን መንግሥታት ያሳየው በራእይ መልክ ሊሆን ይችላል። ሰይጣን ፈተናውን ያቀረበው በራእይ አማካኝነት ሊሆን ቢችልም ‘እንዲያመልከው’ የፈለገው ግን ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ሳይሆን ቃል በቃል መሆን አለበት። (ማቴ. 4:8, 9) ከዚህ በመነሳት ኢየሱስ ከቤተ መቅደሱ እንዲዘል የቀረበለት ፈተና ራሱን ጉዳት ላይ እንዲጥል የሚያደርግ ድርጊት እንዲፈጽም የሚገፋፋ ነበር ማለት እንችላለን፤ ፈተናው የቀረበው በራእይ መልክ ቢሆን ኖሮ ግን ይህን ያህል ክብደት አይኖረውም ነበር።

በዚህ ርዕስ መጀመሪያ ላይ እንደተገለጸው ስለዚህ ጉዳይ እርግጠኛ ሆነን መናገር አንችልም። በመሆኑም ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ በቤተ መቅደሱ አናት ላይ ቆሞ ሊሆን ይችላል። እርግጠኛ ሆነን መናገር የምንችለው ነገር ግን ኢየሱስ በእርግጥ ተፈትኖ እንደነበርና ለእያንዳንዱ ፈተና የማያዳግም መልስ እንደሰጠ ነው።

^ አን.1 ሕዝቅኤል 37:1-14 እና ራእይ 11:7-12 በመንፈሳዊ ሁኔታ መልሶ ስለ መቋቋም ይናገራሉ፤ ይህም በ1919 ተፈጽሟል። ይሁንና የሕዝቅኤል ትንቢት የሚናገረው ሁሉም የአምላክ ሕዝቦች በጣም ረጅም ለሆነ ጊዜ በምርኮ ከቆዩ በኋላ በመንፈሳዊ መልሰው እንደሚቋቋሙ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በራእይ መጽሐፍ ላይ የሚገኘው ትንቢት፣ አመራር ላይ ያሉ ጥቂት ቅቡዓን ወንድሞችን ያቀፈ አንድ ቡድን ለተወሰነ ጊዜ እንቅስቃሴው ታግዶ ከቆየ በኋላ በመንፈሳዊ እንደሚያንሰራራ ይገልጻል።