በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ”

“ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ”

“እነሆም እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።”—ማቴ. 28:20

1. (ሀ) የስንዴውንና የእንክርዳዱን ምሳሌ በአጭሩ ተናገር። (ለ) ኢየሱስ የምሳሌውን ትርጉም ሲያብራራ ምን አለ?

ኢየሱስ ስለ መንግሥቱ ከተናገራቸው ምሳሌዎች መካከል አንዱ ጥሩ የስንዴ ዘር ስለዘራው ገበሬና በኋላም በስንዴው መሃል እንክርዳድ ስለዘራው ጠላት የሚናገረው ነው። በዚህ ምሳሌ ላይ እንደተጠቀሰው ስንዴው በእንክርዳዱ ይሸፈናል፤ ያም ሆኖ ገበሬው ባሪያዎቹን “ተዉት፣ እስከ መከር ጊዜ ድረስ አብሮ ይደግ” አላቸው። በመከር ጊዜ እንክርዳዱ ሲቃጠል ስንዴው ተሰብስቦ ወደ ጎተራ ገባ። ኢየሱስ ይህ ምሳሌ የያዘውን ትርጉም አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥቷል። (ማቴዎስ 13:24-30, 37-43ን አንብብ።) ታዲያ ይህ ምሳሌ ምን ነገር ይገልጥልናል? (“ስንዴውና እንክርዳዱ” የሚለውን ሠንጠረዥ ተመልከት።)

2. (ሀ) በገበሬው እርሻ ላይ የተከናወኑት ነገሮች የሚያመለክቱት ምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ላይ የምንመረምረው የትኛውን የምሳሌው ክፍል ነው?

2 በገበሬው እርሻ ላይ የተከናወኑት ነገሮች ኢየሱስ የስንዴውን ክፍል ማለትም በመንግሥቱ ከእሱ ጋር የሚገዙትን ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከመላው የሰው ዘር መካከል የሚሰበስበው እንዴትና መቼ እንደሆነ ይጠቁማሉ። ዘሩ መዘራት የተጀመረው በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት ነው። የመሰብሰቡ ሥራ የሚጠናቀቀው ደግሞ በዚህ ሥርዓት መጨረሻ ላይ በሕይወት ያሉት ቅቡዓን የመጨረሻው ማኅተም ሲደረግባቸውና ከዚያም ወደ ሰማይ ሲሄዱ ነው። (ማቴ. 24:31፤ ራእይ 7:1-4) አንድ ሰው የተራራ ጫፍ ላይ መቆሙ ዙሪያ ገባውን ለማየት እንደሚያስችለው ሁሉ ይህ ምሳሌም ወደ 2,000 ዓመታት በሚጠጋ ጊዜ ውስጥ የተከናወኑትን ነገሮች በስፋት ለመቃኘት ያስችለናል። ታዲያ እዚህ ምሳሌ ላይ ቆመን ነገሮችን ስንቃኝ ከመንግሥቱ ጋር በተያያዘ የተፈጸሙትን የትኞቹን ክንውኖች ማስተዋል እንችላለን? ምሳሌው ስንዴውና እንክርዳዱ የሚዘሩበት፣ አብረው የሚያድጉበትና የመከር ወቅት እንደሚኖር ይገልጻል። ይህ ርዕስ ግን በዋነኝነት የሚያተኩረው በመከሩ ላይ ነው። *

በኢየሱስ ጥበቃ ሥር መሆን

3. (ሀ) ከመጀመሪያው መቶ ዘመን በኋላ ምን ሁኔታ መከሰት ጀመረ? (ለ) በማቴዎስ 13:28 ላይ እንደተገለጸው ምን ጥያቄ ተነስቶ ነበር? ጥያቄውን ያነሱትስ እነማን ናቸው? (ተጨማሪ መረጃውንም ተመልከት።)

3 በእንክርዳድ የተመሰሉት አስመሳይ ክርስቲያኖች ከሁለተኛው  መቶ ዘመን ዓ.ም. መባቻ አንስቶ፣ በእርሻ በተመሰለው ዓለም ላይ ብቅ ማለት ጀመሩ። (ማቴ. 13:26) በእንክርዳድ የተመሰሉት ክርስቲያኖች ቁጥር በአራተኛው መቶ ዘመን ላይ ከቅቡዓን ክርስቲያኖች በጣም በልጦ ነበር። በምሳሌው ላይ ባሪያዎቹ እንክርዳዱን ለመንቀል እንዲፈቅድላቸው ጌታቸውን ጠይቀውት እንደነበር አስታውስ። * (ማቴ. 13:28) ታዲያ ጌታው ምን ምላሽ ሰጠ?

4. (ሀ) ጌታ ኢየሱስ የሰጠው መልስ ምን ነገር ግልጽ እንዲሆን አስችሏል? (ለ) በስንዴ የተመሰሉት ክርስቲያኖች የተለዩት መቼ ነው?

4 ኢየሱስ ስለ ስንዴውና ስለ እንክርዳዱ ሲናገር “ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ” (አ.መ.ት) ብሏል። ይህ መመሪያ እንደሚያስገነዝበን ከመጀመሪያው መቶ ዘመን አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ በምድር ላይ ምንጊዜም የተወሰኑ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይኖራሉ። ኢየሱስ “እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” በማለት መናገሩ ይህን ያረጋግጥልናል። (ማቴ. 28:20) በመሆኑም ኢየሱስ እስከ ሥርዓቱ ፍጻሜ ድረስ ምንጊዜም ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ጥበቃ ያደርግላቸዋል። ይሁንና ቅቡዓኑ በእንክርዳድ በተመሰሉ ክርስቲያኖች ስለተዋጡ በዚህ ረጅም ጊዜ ውስጥ የስንዴው ክፍል የሆኑት እነማን እንደነበሩ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። የመከሩ ወቅት ከመጀመሩ ከጥቂት አሥርተ ዓመታት በፊት ግን የስንዴው ክፍል የሆኑት እነማን እንደሆኑ መለየት ጀመረ። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?

መልእክተኛው ‘መንገዱን አዘጋጀ’

5. የሚልክያስ ትንቢት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

 5 ኢየሱስ ስለ እንክርዳዱና ስለ ስንዴው ምሳሌ ከመናገሩ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ነቢዩ ሚልክያስ በኢየሱስ ምሳሌ ላይ ከተገለጹት ክንውኖች ጋር የሚመሳሰል ትንቢት እንዲናገር ይሖዋ በመንፈሱ መርቶታል። (ሚልክያስ 3:1-4ን አንብብ።) ‘መንገዱን የሚያዘጋጀው መልእክተኛ’ መጥምቁ ዮሐንስ ነው። (ማቴ. 11:10, 11) ዮሐንስ በ29 ዓ.ም. ሲመጣ የእስራኤል ብሔር የሚፈረድበት ጊዜ ተቃርቦ  ነበር። ሁለተኛው መልእክተኛ ኢየሱስ ነው። ኢየሱስ በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ ሁለት ጊዜ ማለትም በአገልግሎቱ መጀመሪያና መጨረሻ ላይ አንጽቷል። (ማቴ. 21:12, 13፤ ዮሐ. 2:14-17) በመሆኑም ኢየሱስ ያከናወነው የማንጻት ሥራ የተወሰነ ጊዜ ወስዷል።

6. (ሀ) የሚልክያስ ትንቢት ታላቅ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ መንፈሳዊ ቤተ መቅደሱን የመረመረው በየትኛው ጊዜ ውስጥ ነው? (ተጨማሪ መረጃውንም ተመልከት።)

 6 የሚልክያስ ትንቢት ታላቅ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? ከ1914 በፊት ባሉት ጥቂት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ቻርልስ ቴዝ ራስል እና የቅርብ አጋሮቹ ከመጥምቁ ዮሐንስ ጋር የሚመሳሰል ሥራ አከናውነዋል። ይህ ሥራ ተደብቀው የቆዩትን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ይፋ ማድረግ ይጠይቃል። ለምሳሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ያለውን ትክክለኛ ትርጉም ያስተማሩ ከመሆኑም በላይ ገሃነመ እሳት የሐሰት ትምህርት መሆኑን አጋልጠዋል፤ እንዲሁም የአሕዛብ ዘመን የሚያበቃበትን ጊዜ ለሰዎች አውጀዋል። ያም ሆኖ የክርስቶስ ተከታዮች እንደሆኑ የሚናገሩ በርካታ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ነበሩ። በዚህም ምክንያት የሚከተለው አንገብጋቢ ጥያቄ ተነሳ፦ ከእነዚህ ቡድኖች መካከል በስንዴ የተመሰሉት የትኞቹ ናቸው? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ኢየሱስ በ1914 መንፈሳዊ ቤተ መቅደሱን መመርመር ጀመረ። ይህ የምርመራና የማንጻት ሥራ ለተወሰነ ጊዜ ይኸውም ከ1914 እስከ 1919 መጀመሪያ አካባቢ ድረስ ቀጥሎ ነበር። *

የመመርመሩና የማንጻቱ ሥራ የተከናወነባቸው ዓመታት

7. ኢየሱስ በ1914 ምርመራውን ሲያካሂድ ምን አገኘ?

7 ኢየሱስ ምርመራውን ሲያካሂድ ምን ውጤት አገኘ? ጥቂት ቁጥር ያላቸው ቀናተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ከ30 ለሚበልጡ ዓመታት ጉልበታቸውንና ጥሪታቸውን ተጠቅመው ከፍተኛ የስብከት ዘመቻ ሲያካሂዱ ቆይተዋል። * አንጻራዊ በሆነ ሁኔታ ጥቂት ቁጥር ያላቸው እነዚህ ጠንካራ ክርስቲያኖች  በሰይጣን እንክርዳድ ባለመታነቃቸው ኢየሱስና መላእክቱ በጣም እንደተደሰቱ ምንም ጥርጥር የለውም! ያም ቢሆን “ሌዋውያን” ማለትም ቅቡዓን ክርስቲያኖች መንጻት ያስፈልጋቸው ነበር። (ሚል. 3:2, 3፤ 1 ጴጥ. 4:17) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

8. ከ1914 በኋላ ምን ነገሮች ተከናወኑ?

8 በ1914 ማብቂያ ላይ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ወደ ሰማይ ባለመሄዳቸው አዝነው ነበር። ከ1915 እስከ 1916 ባለው ጊዜ ውስጥ ከድርጅቱ ውጪ ያሉ ሰዎች ያደረሱት ተቃውሞ የስብከቱን ሥራ አቀዝቅዞት ነበር። ይባስ ብሎ ወንድም ራስል ጥቅምት 1916 ከሞተ በኋላ ከድርጅቱ ውስጥ ተቃዋሚዎች ተነሱ። የዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ዳይሬክተር ከሆኑት ሰባት ሰዎች መካከል አራቱ ወንድም ራዘርፎርድ ድርጅቱን እንዲመራ መመረጡን በመቃወም ዓመፁ። በወንድሞች መካከል መከፋፈል ለመፍጠር ቢሞክሩም ነሐሴ 1917 ቤቴልን ለቅቀው ወጡ፤ ታዲያ ማንጻት ማለት ይህ አይደል! በተጨማሪም አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በሰው ፍርሃት ተሸንፈው ነበር። ያም ሆኖ በቡድን ደረጃ ኢየሱስ ቅቡዓኑን ለማንጻት የወሰደውን ይህን እርምጃ በመደገፍ ተገቢውን ለውጥ አደረጉ። በዚህም የተነሳ ኢየሱስ በስንዴ የተመሰሉት እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደሆኑ ፈርዶላቸዋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ በሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ያሉትን ጨምሮ ሁሉም አስመሳይ ክርስቲያኖች በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ሳያገኙ ቀርተዋል። (ሚል. 3:5፤ 2 ጢሞ. 2:19) ከዚያስ ምን ሆነ? ይህን ለማወቅ ስለ ስንዴውና ስለ እንክርዳዱ የሚናገረውን ምሳሌ መለስ ብለን እንመልከት።

የመከሩ ወቅት ከጀመረ በኋላ ምን ተከናወነ?

9, 10. (ሀ) ከመከሩ ወቅት ጋር በተያያዘ ምን ነገር እንመረምራለን? (ለ) በመከሩ ወቅት፣ መጀመሪያ የተከናወነው ነገር ምንድን ነው?

9 ኢየሱስ “መከሩ የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” መሆኑን ተናግሯል። (ማቴ. 13:39) የመከሩ ሥራ የጀመረው ደግሞ በ1914 ነው። ኢየሱስ በመከር ወቅት እንደሚፈጸሙ አስቀድሞ የተናገራቸውን አምስት ክንውኖች እስቲ እንመልከት።

10 የመጀመሪያው እንክርዳዱን መሰብሰብ ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “የመከር ወቅት ሲደርስ አጫጆቹን፣ በመጀመሪያ እንክርዳዱን ሰብስቡና . . . በየነዶው እሰሩ፤ . . . እላቸዋለሁ።” ከ1914 በኋላ ግን መላእክት በእንክርዳድ የተመሰሉትን ክርስቲያኖች “የመንግሥቱ ልጆች” ከሆኑት ከቅቡዓን በመለየት ‘ይሰበስቧቸዋል።’—ማቴ. 13:30, 38, 41

11. እስከ ዛሬ ድረስ እውነተኛ ክርስቲያኖችን ከአስመሳይ ክርስቲያኖች የሚለያቸው ምንድን ነው?

11 የመሰብሰቡ ሥራ ወደፊት እየገፋ ሲሄድ በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው ልዩነት ይበልጥ ፍንትው ብሎ መታየት ጀመረ። (ራእይ 18:1, 4) በ1919 ታላቂቷ ባቢሎን እንደወደቀች ግልጽ ሆነ። ለመሆኑ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከአስመሳዮቹ ክርስቲያኖች ይበልጥ እንዲለዩ ያደረጋቸው ነገር ምንድን ነው? የስብከቱ ሥራ ነው። በወቅቱ በኃላፊነት ቦታ ላይ የነበሩ ወንድሞች፣ የመንግሥቱን መልእክት በመስበኩ ሥራ ላይ ሁሉም ክርስቲያኖች መካፈል እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተው መናገር ጀመሩ። ለምሳሌ ያህል፣ ሥራው በኃላፊነት ለተሰጣቸው ሁሉ (እንግሊዝኛ) የተሰኘ በ1919 የታተመ ቡክሌት ሁሉም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከቤት ወደ ቤት በመሄድ እንዲሰብኩ አሳስቦ ነበር። እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ሥራው ሰፊ ቢመስልም የጌታ ሥራ በመሆኑ እሱ በሚሰጠን ኃይል እንወጣዋለን። በዚህ ሥራ የመካፈል መብት አግኝታችኋል።” ታዲያ ምን ምላሽ ተገኘ? የ1922 መጠበቂያ ግንብ እንደገለጸው ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የስብከት እንቅስቃሴያቸውን አጧጧፉት። ብዙም ሳይቆይ ከቤት ወደ ቤት መስበክ የእነዚህ ታማኝ ክርስቲያኖች መለያ ሆነ፤ ይህ የስብከት ዘዴ እስከ ዛሬ ድረስ መለያችን ሆኗል።

12. የስንዴው ክፍል መሰብሰብ የጀመረው ከመቼ ጀምሮ ነው?

12 ሁለተኛው ስንዴውን መሰብሰብ ነው። ኢየሱስ “ስንዴውን ሰብስባችሁ ወደ ጎተራዬ አስገቡ” በማለት መላእክቱን አዝዟቸዋል። (ማቴ. 13:30) ከ1919 ጀምሮ ቅቡዓን ክርስቲያኖች እንደ ገና ወደተቋቋመው የክርስቲያን ጉባኤ ሲሰበሰቡ ቆይተዋል። በዚህ ሥርዓት መጨረሻ ላይ በሕይወት ከሚገኙ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጋር በተያያዘ የመጨረሻው የመሰብሰብ ሥራ የሚካሄደው ወደ ሰማይ በመሄድ  ሽልማታቸውን ሲያገኙ ነው።—ዳን. 7:18, 22, 27

13. ራእይ 18:7 ሕዝበ ክርስትናን ጨምሮ ጋለሞታይቱ ወይም ታላቂቱ ባቢሎን በአሁኑ ጊዜ ያላትን አመለካከት የሚገልጸው እንዴት ነው?

13 ሦስተኛው ማልቀስና ጥርስ ማፋጨት ነው። መላእክቱ እንክርዳዱን በየነዶው ካሰሩ በኋላ ምን ይከናወናል? ኢየሱስ የእንክርዳዱ ክፍል የሆኑት፣ ስለሚገኙበት ሁኔታ ሲናገር “በዚያም ያለቅሳሉ፣ በሐዘንም ጥርሳቸውን ያፋጫሉ” ብሏል። (ማቴ. 13:42) ታዲያ ይህ ሁኔታ በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸመ ነው? በፍጹም። የጋለሞታይቱ ክፍል የሆነችው ሕዝበ ክርስትና ዛሬም “ንግሥት ሆኜ እቀመጣለሁ፤ መበለትም አይደለሁም፤ ሐዘንም ፈጽሞ አይደርስብኝም” ብላ ታስባለች። (ራእይ 18:7) በእርግጥም ሕዝበ ክርስትና ሥልጣን እንዳላት ይሰማታል፤ እንዲያውም በፖለቲካ መሪዎች ላይ ‘እንደተቀመጠች ንግሥት’ አድርጋ ራሷን ትቆጥራለች። በመሆኑም በእንክርዳድ የተመሰሉት ሐሰተኞቹ ክርስቲያኖች በአሁኑ ጊዜ እያለቀሱ ሳይሆን እየተኩራሩ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ የሚለወጥበት ጊዜ ቀርቧል።

ሕዝበ ክርስትና ከፖለቲካ መሪዎች ጋር ያላት ወዳጅነት በቅርቡ ያከትማል (አንቀጽ 13ን ተመልከት)

14. (ሀ) አስመሳይ ክርስቲያኖች ‘ጥርሳቸውን የሚያፋጩት’ መቼ ነው? ለምንስ? (ለ) ማቴዎስ 13:42ን በተመለከተ ያገኘነው አዲሱ መረዳት ከመዝሙር 112:10 ጋር የሚስማማው እንዴት ነው? (ተጨማሪ መረጃውን ተመልከት።)

14 በተደራጀ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የሐሰት ሃይማኖቶች በሙሉ በታላቁ መከራ ወቅት ሲጠፉ እነሱን ሲደግፉ የነበሩ ሁሉ መሸሸጊያ ፍለጋ ይራወጣሉ፤ ሆኖም ለመደበቅ የሚያስችል አስተማማኝ ቦታ ማግኘት አይችሉም። (ሉቃስ 23:30፤ ራእይ 6:15-17) ከጥፋቱ ማምለጥ እንደማይችሉ ሲገነዘቡ ተስፋ በመቁረጥ ያለቅሳሉ፤ በንዴትም “ጥርሳቸውን ያፋጫሉ።” ኢየሱስ ስለ ታላቁ መከራ በተናገረው ትንቢት ላይ እንደተገለጸው ጨለማ በሆነው በዚያ ወቅት “ደረታቸውን ይደቃሉ።” *ማቴ. 24:30፤ ራእይ 1:7

15. እንክርዳዱ ምን ይሆናል? ይህ የሚሆነውስ መቼ ነው?

15 አራተኛው ወደ እቶን እሳት መጣል ነው። በየነዶው የታሰረው እንክርዳድ ምን ይሆናል? መላእክቱ ‘ወደ እቶን እሳቱ ይጥሉታል።’ (ማቴ. 13:42) ይህ ደግሞ ሙሉ በሙሉ መጥፋትን ያመለክታል። በመሆኑም የሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶችን ሲደግፉ የነበሩ ሁሉ በታላቁ መከራ የመጨረሻ ምዕራፍ ማለትም በአርማጌዶን ይጠፋሉ።—ሚል. 4:1

16, 17. (ሀ) ኢየሱስ በምሳሌው ላይ የጠቀሰው የመጨረሻ ክንውን ምንድን ነው? (ለ) ይህ ክንውን የሚፈጸመው ወደፊት ነው የምንለው ለምንድን ነው?

16 አምስተኛው ደግሞ ደምቆ ማብራት ነው። ኢየሱስ ምሳሌውን የደመደመው እንደሚከተለው በማለት ነው፦ “በዚያ ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ደምቀው ያበራሉ።” (ማቴ. 13:43) ይህ የሚሆነው መቼና የት ነው? ይህ ትንቢት የሚፈጸመው ገና ወደፊት ነው። ኢየሱስ እዚህ ላይ የገለጸው በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ እየተከናወነ ያለን ነገር ሳይሆን ወደፊት በሰማይ ላይ የሚፈጸምን ነገር ነው። * እዚህ መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ ያደረጉንን ሁለት ምክንያቶች እስቲ እንመልከት።

17 በመጀመሪያ “መቼ” ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት እንሞክር። ኢየሱስ “በዚያ ጊዜ ጻድቃን  . . . ደምቀው ያበራሉ” ብሏል። “በዚያ ጊዜ” የሚለው ሐረግ የሚያመለክተው ከዚህ ጥቅስ በፊት የተናገረውን ይኸውም ‘እንክርዳዱ ወደ እቶን እሳት የሚጣልበትን’ ጊዜ እንደሆነ የተረጋገጠ ነው። ይህ የሚሆነው ደግሞ በታላቁ መከራ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ነው። እንግዲያው ቅቡዓኑ ‘ደምቀው የሚያበሩትም’ ከላይ በተጠቀሰው ጊዜ ላይ መሆን ይኖርበታል። ሁለተኛው ጥያቄ “የት” የሚለው ነው። ኢየሱስ ጻድቃን በአምላክ “መንግሥት እንደ ፀሐይ ደምቀው ያበራሉ” ብሏል። ይህ ምን ማለት ነው? የታላቁ መከራ የመጀመሪያ ምዕራፍ ካለፈ በኋላ በምድር ላይ የሚገኙት ሁሉም ታማኝ ቅቡዓን ወዲያውኑ የመጨረሻው ማኅተም ይደረግባቸዋል። ከዚያም ኢየሱስ ስለ ታላቁ መከራ በተናገረው ትንቢት ላይ እንደገለጸው ቅቡዓኑ ወደ ሰማይ ይሰበሰባሉ። (ማቴ. 24:31) በዚያም “በአባታቸው መንግሥት” ደምቀው ያበራሉ፤ ከአርማጌዶን ጦርነት ብዙም ሳይቆይ ‘በበጉ ሠርግ’ ላይ ደስተኛ የኢየሱስ ሙሽራ ሆነው ይቀርባሉ።—ራእይ 19:6-9

የምናገኘው ጥቅም

18, 19. ኢየሱስ ስለ ስንዴውና ስለ እንክርዳዱ የተናገረው ምሳሌ በግለሰብ ደረጃ የሚጠቅመን በየትኞቹ መንገዶች ነው?

18 የዚህን ምሳሌ ዙሪያ ገባ መቃኘታችን በግለሰብ ደረጃ የሚጠቅመን እንዴት ነው? እስቲ ሦስት መንገዶችን እንመልከት። አንደኛ፣ አመለካከታችንን ያሰፋዋል። ምሳሌው ይሖዋ ክፋት እንዲኖር የፈቀደበትን ወሳኝ ምክንያት ያስገነዝበናል። “ለጥፋት የተዘጋጁትን የቁጣ ዕቃዎች” የታገሠው ‘የምሕረት ዕቃዎችን’ ማለትም የስንዴውን ክፍል ለማዘጋጀት ነው። * (ሮም 9:22-24) ሁለተኛ፣ በይሖዋ ላይ ያለንን ትምክህት ይጨምርልናል። መጨረሻው እየቀረበ ሲመጣ ጠላቶቻችን በእኛ ላይ የሚሰነዝሩት ጥቃት እየጨመረ መሄዱ አይቀርም፤ ያም ሆኖ ‘አያሸንፉንም።’ (ኤርምያስ 1:19ን አንብብ።) ይሖዋ ባለፉት ዘመናት ለስንዴው ክፍል ጥበቃ ሲያደርግ እንደቆየ ሁሉ የሰማዩ አባታችን በኢየሱስና በመላእክቱ አማካኝነት “ሁልጊዜ” ከእኛ ጋር ይሆናል።—ማቴ. 28:20

19 ሦስተኛ፣ ምሳሌው በስንዴ የተመሰሉትን ክርስቲያኖች ማንነት ለመለየት ይረዳናል። ይህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በስንዴ የተመሰሉትን ክርስቲያኖች ለይተን ማወቃችን ኢየሱስ መጨረሻውን ቀን አስመልክቶ በተናገረው ዝርዝር ሐሳቦችን በያዘው ትንቢት መደምደሚያ ላይ ላነሳው ጥያቄ መልስ ለማግኘት ይረዳናል። ኢየሱስ “ታማኝና ልባም ባሪያ በእርግጥ ማን ነው?” ብሏል። (ማቴ. 24:45) የሚቀጥሉት ሁለት ርዕሶች ለዚህ ጥያቄ አጥጋቢ መልስ ይሰጣሉ።

 

^ አን.2 አንቀጽ 2፦ ሌሎቹ የምሳሌው ክፍሎች ያላቸውን ትርጉም ማስታወስ እንድትችል ‘ጻድቃን እንደ ፀሐይ ደምቀው ያበራሉ’ የሚለውን ርዕስከ መጋቢት 15, 2010 መጠበቂያ ግንብ ላይ እንድታነብ እናበረታታሃለን።

^ አን.3 አንቀጽ 3፦ የኢየሱስ ሐዋርያት ሞተው ስላለቁ እንዲሁም በምድር ላይ ያሉት ቅቡዓን ቀሪዎች የተመሰሉት በባሪያዎቹ ሳይሆን በስንዴው ስለሆነ ባሪያዎቹ የሚያመለክቱት መላእክትን ነው። በኋላም ኢየሱስ ምሳሌውን ሲያብራራ እንክርዳዱን የሚያጭዱት መላእክት እንደሆኑ ተናግሯል።—ማቴ. 13:39

^ አን.6 አንቀጽ 6፦ ይህ ሐሳብ ቀደም ሲል የነበረንን መረዳት የሚያስተካክል ነው። ከዚህ ቀደም ኢየሱስ ምርመራውን ያካሄደው በ1918 እንደሆነ እናምን ነበር።

^ አን.7 አንቀጽ 7፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ከ1910 እስከ 1914 ባሉት ዓመታት 4,000,000 ገደማ የሚሆኑ መጻሕፍትን እና ከ200,000,000 የሚበልጡ ትራክቶችንና ቡክሌቶችን አሰራጭተዋል።

^ አን.14 አንቀጽ 14፦ ይህ ሐሳብ ማቴዎስ 13:42ን አስመልክቶ ከዚህ በፊት የነበረንን መረዳት የሚያስተካክል ነው። ቀደም ሲል በጽሑፎቻችን ላይ “የመንግሥቱ ልጆች” የአስመሳይ ክርስቲያኖችን ማንነት ስላጋለጡ ይኸውም “የክፉው ልጆች” መሆናቸውን ስለመሠከሩ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት እያለቀሱና ጥርሳቸውን እያፋጩ እንደነበረ ተገልጾ ነበር። (ማቴ. 13:38) ይሁንና ጥርስን ማፋጨት ከጥፋት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ማስተዋል ይገባናል።—መዝ. 112:10

^ አን.16 አንቀጽ 16፦ ዳንኤል 12:3 “ጥበበኞች [ቅቡዓን ክርስቲያኖች] እንደ ሰማይ ጸዳል፣ . . . ለዘላለም ይደምቃሉ” ይላል። ቅቡዓኑ በምድር ላይ እያሉ ይህን የሚያደርጉት በስብከቱ ሥራ በመካፈል ነው። ይሁንና ማቴዎስ 13:43 የሚገልጸው በአምላክ መንግሥት ውስጥ በሰማይ ደምቀው ስለሚያበሩበት ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም ሁለቱም ጥቅሶች ስለ አንድ ነገር ይኸውም ስለ ስብከቱ ሥራ እንደሚያመለክቱ አድርገን እናስብ ነበር።

^ አን.18 አንቀጽ 18፦ ወደ ይሖዋ ቅረብ የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 288-289 ተመልከት።