በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሙዚቃ ፊልሞችን በመመልከት ረገድ መራጭ መሆን የምችለው እንዴት ነው?

የሙዚቃ ፊልሞችን በመመልከት ረገድ መራጭ መሆን የምችለው እንዴት ነው?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

የሙዚቃ ፊልሞችን በመመልከት ረገድ መራጭ መሆን የምችለው እንዴት ነው?

“ገና ዘፈኑ ሲተዋወቅ መጥፎ ዝና ያተረፈ ቡድን ወይም ዘፈን እንደሚቀርብ ካወቅሁ ወዲያው ጣቢያውን እቀይረዋለሁ።”​—ኬሲ

በርካታ ወጣቶች የሙዚቃ ፊልሞችን መመልከት በጣም ያስደስታቸዋል። ሆኖም ቀደም ሲል በዚሁ አምድ ሥር የወጣው ርዕስ እንደጠቆመው አብዛኞቹ የሙዚቃ ፊልሞች አስጸያፊ በሆኑ የጾታ ብልግናዎችና ዘግናኝ በሆኑ የዓመጽ ድርጊቶች የተሞሉ ናቸው። * አንድ ክርስቲያን አምላክ የሚያወግዘውን ድርጊት የሚያንጸባርቅ ማንኛውንም ዓይነት መዝናኛ መመልከት እንደሌለበት ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ሁሉም የሙዚቃ ፊልሞች የሥነ ምግባር ብልግናን በግልጽ ያሳያሉ ማለት አይደለም። በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አንዳንዶቹ ይህን ያህል የብልግና ወይም የዓመጽ ድርጊት የማይታይባቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ያም ሆኖ ከአምላክ ቃል ጋር የሚጋጭ አንድ ዓይነት ስውር መልእክት ሊያስተላልፉ ይችላሉ።

ወላጆችህ የሙዚቃ ፊልሞችን እንድትመለከት ከፈቀዱልህ መራጭ መሆን እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ የሰለጠነ ‘የማስተዋል ችሎታህን’ በመጠቀም ተገቢ የሆነውንና ያልሆነውን ፊልም መለየት ይኖርብሃል። (ዕብራውያን 5:14 NW ) በዚህ ረገድ የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሊረዱህ ይችላሉ? ቀጥሎ የቀረቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ሐሳቦች ሊረዱህ ይችላሉ።

ምሳሌ 4:23:- “አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፣ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና።” በጣም የምትሳሳለት የስፖርት ዕቃ ወይም የሙዚቃ መሣሪያ አለህ? ይህን ዕቃ ጥሩ አድርገህ እንደምትይዘውና በጥንቃቄ እንደምታስቀምጠው ምንም ጥርጥር የለውም። እንዳይበላሽብህ ወይም እንዳይሰረቅብህ ስለምትፈራ በምንም ዓይነት ለጊዜውም እንኳን ቢሆን አልባሌ ቦታ አትተወውም። ከዚያ ይልቅ በጥንቃቄ ትጠብቀዋለህ። በተመሳሳይም ጤናማ ያልሆነ መዝናኛ በመመልከት ለአጭር ጊዜም እንኳን ቢሆን ልብህን ለአደጋ ላለማጋለጥ ቆራጥ መሆን ይኖርብሃል።

ኤፌሶን 2:1, 2:- “በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፣ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፣ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፣ በፊት ተመላለሳችሁባቸው።” አየር የተባለው የዓለም መንፈስ ሲሆን ይህም አምላካዊ ያልሆነ ባሕርይን የሚያስፋፋው አስተሳሰብና አመለካከት ነው። ይህ መንፈስ በአብዛኞቹ የሙዚቃ ፊልሞች ውስጥ የሚንጸባረቅ ከመሆኑም በላይ እንደ ደስታ፣ ሰላም እና ራስን መግዛት ያሉትን ፍሬዎች ከሚያፈራው የአምላክ መንፈስ ጋር ይጋጫል።​—⁠ገላትያ 5:22, 23

2 ጢሞቴዎስ 2:22 አ.መ.ት:- “ከወጣትነት ክፉ ምኞት ሽሽ።” ለቅጽበትም እንኳ ቢሆን የብልግና ድርጊቶችን የሚያሳዩ ፊልሞችን መመልከት የጾታ ስሜትን እንደሚያነሳሳ የታወቀ ነው። ብዙ ወጣቶች እንደዚህ ዓይነቱ ድርጊት በአእምሮአቸው ውስጥ ተቀርጾ እንደሚቀርና እንዲያውም በአእምሯቸው እየተመላለሰ እንደሚያስቸግራቸው አምነዋል። ዴቭ የተባለ አንድ ወጣት የጾታ ስሜት የሚቀሰቅስ ፊልም በመመልከቱ የተሰማውን ሲናገር “ያንን ፊልም ከተመለከትኩ በኋላ ሙዚቃውን በሰማሁ ቁጥር ትርዒቱ ወደ አእምሮዬ ይመጣል” ብሏል። እንደዚህ ዓይነት ፊልሞችን መመልከት የጾታ ብልግና የመፈጸም ፍላጎት ሊያሳድርብህ ይችላል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 6:18፤ ቆላስይስ 3:5

ምሳሌ 13:20:- “የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል።” ‘ዓመፀኞችን፣ መናፍስታዊ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎችን፣ ሰካራሞችን ወይም ልቅ የጾታ ሥነ ምግባር ያላቸውን ሰዎች ወደ ቤቴ እጋብዛለሁን?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። በቴሌቪዥን አማካኝነት ከእንደዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች ጋር መገናኘት እነርሱን ወደ ቤትህ ከመጋበዝ ተለይቶ አይታይም። እንደዚህ ማድረግ ‘መከራ እንዲደርስብህ’ ሊያደርግ ይችላል? ኪምበርሊ የተባለች ወጣት “በአንዳንድ ግብዣዎች ላይ ልጃገረዶች በቅርቡ በፊልም ያዩትን አለባበስ ወይም የጾታ ስሜት የሚቀሰቅስ ዳንስ ለመኮረጅ ሲሞክሩ ተመልክቻለሁ” ብላለች። አንተም ተመሳሳይ ነገር ታዝበህ ይሆናል። እነዚህ ወጣቶች ለአምላካዊ ሥርዓቶች አክብሮት የሌላቸውን ሰዎች በመምሰል ‘መከራ እንዲደርስባቸው’ እየፈቀዱ ነው። እንግዲያው ከማንኛውም ዓይነት “ክፉ ባልንጀርነት” ራቅ።​—⁠1 ቆሮንቶስ 15:33

መዝሙር 11:5:- “እግዚአብሔር ጻድቅንና ኀጥእን ይመረምራል፤ ዓመፃን የወደዳት ግን ነፍሱን ጠልቶአል።” ጭካኔ የተሞላባቸው የዓመጽ ድርጊቶችን የሚያሳዩ ፊልሞች የምንመለከት ከሆነ ሌሎች ሰዎች ‘ዓመፃን እንደምንወድ’ አድርገው ሊያስቡ አይችሉምን?

መራጭ መሆን ተፈታታኝ ነው

‘ዓለም በሞላው በክፉው ስለተያዘ’ በዓለም አስተሳሰብና ዝንባሌ ያልተበከለ መዝናኛ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል። (1 ዮሐንስ 5:19) አንዳንድ የሙዚቃ ፊልም ጣቢያዎች መጥፎ ነገሮችን በገፍ ያቀርባሉ። ፕሮግራሙ የሥነ ምግባር ብልግናን ወይም የዓመጽ ድርጊትን በገሃድ ባያሳይም እንኳ አብዛኛውን ጊዜ የዓለምን መንፈስ ማንጸባረቁ አይቀርም። አንድ የሙዚቃ ባለሙያ ታዋቂ ስለሆነ አንድ የሙዚቃ ፊልም ጣቢያ ሲናገሩ “የሙዚቃ ጣቢያ መሆኑ ቀርቶ ‘አንድ ዓይነት የአኗኗር ዘይቤ’ የሚያስፋፋ ጣቢያ ሆኗል” ብለዋል።

ቀላሉ መፍትሔ አንድ ፊልም መጥፎ ከሆነ ጣቢያውን መቀየር ሊመስል ይችላል። ችግሩ ግን ሌሎች የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን በምትከታተልበት ጊዜም የዚያኑ ያህል ጠንቃቃ መሆን ያስፈልግሃል። ምክንያቱም ዛሬ የሚቀርቡት አብዛኞቹ ፕሮግራሞች ዓመጽ፣ ብልግና ወይም ወራዳ ሥነ ምግባር ያላቸውን ሰዎች የሚያሳዩ ናቸው። እርግጥ ነው፣ በአንድ በኩል ለመዝናናት እየፈለጉ በሌላ በኩል ደግሞ መጥፎ ነገር በታየ ቁጥር ጣቢያ መቀያየሩ በራሱ የሚያበሳጭና ተስፋ አስቆራጭ ሊሆን እንደሚችል አይካድም። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ጣቢያውን እስክንቀይር ድረስ ርካሽ የሆኑ ምስሎች በአእምሯችን ይቀረጻሉ። ያም ቢሆን ግን ይሖዋ አምላክ ልብህን ለመጠበቅ የምታደርገውን ጥረት እንደሚባርክልህ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ።​—⁠2 ሳሙኤል 22:21

ጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ ሌሎች እርምጃዎችም አሉ። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ኬሲ ጠቃሚ ሆኖ ያገኘውን ነጥብ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “ብዙውን ጊዜ የቡድኑ ስምና የሙዚቃው ርዕስ የሚተዋወቀው ገና ፊልሙ ሲጀምር ነው። የሙዚቃ ባንዶች ካተረፉት ስም በመነሳት የትኞቹ ቡድኖችና የትኞቹ ሙዚቃዎች መጥፎ እንደሆኑ ማወቅ ይቻላል። በመሆኑም ገና ዘፈኑ ሲተዋወቅ መጥፎ ዝና ያተረፈ ቡድን ወይም ዘፈን እንደሚቀርብ ካወቅሁ ወዲያው ጣቢያውን እቀይረዋለሁ።”

‘በልብህ እውነትን ተናገር’

የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሚገባ ብታውቅም እንኳ ራስህን ለማሳመን ሰበብ አስባብ በመፍጠር መጥፎ የሆነውን ነገር በቸልታ መመልከት ልትጀምር ትችላለህ። (ያዕቆብ 1:22) መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ወዳጅ የሚሆነው “በልቡ እውነትን የሚናገር” ሰው እንደሆነ ይገልጻል። (መዝሙር 15:2) እንግዲያው ራስህን በሐቀኝነት መርምር። ፈጽሞ ራስህን አታታልል። የምትመለከተው ነገር ተገቢ ባይሆንም ሰበብ የመፍጠር አዝማሚያ እንዳለህ ከተገነዘብክ ‘ይሖዋ እንደዚህ ዓይነቱን ነገር መመልከቴን ይደግፈዋልን?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። አብዛኛውን ጊዜ ከባድ የሚሆነው ትክክልና ስሕተት የሆነውን ለይቶ ማወቅ ሳይሆን ትክክል የሆነውን ለማድረግ እርምጃ መውሰድ መሆኑን አስታውስ! ከይሖዋ ጋር ያለህን ዝምድና ከማንኛውም ዓይነት መዝናኛ ይበልጥ ከፍ አድርገህ ልትመለከተው ይገባል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 6:17, 18

ብዙውን ጊዜ መራጭ ለመሆን በግማሽ ልብ ውሳኔ ማድረግ ብቻ በቂ አይሆንም። ውሳኔህ ቁርጠኝነት የታከለበት ካልሆነ ብዙም ሳይቆይ አቋምህን ልታላላ ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስ ኢዮብ የተባለው ፈሪሃ አምላክ የነበረው ሰው ለሚስቱ ታማኝ ለመሆን ስላደረገው ቁርጥ ውሳኔ ይናገራል። ኢዮብ “ከዓይኔ ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ፤ እንግዲህስ ቈንጆይቱን እንዴት እመለከታለሁ?” ብሎ ነበር። (ኢዮብ 31:1) እስቲ አስበው! ኢዮብ በሚመለከተው ነገር ረገድ ገደብ ለማበጀት ከራሱ ጋር ቃል ኪዳን ገብቶ ነበር። አንተም እንደዚሁ ማድረግ ትችላለህ። መጥፎ የሆኑ ነገሮችን ላለመመልከት ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ለራስህ ገደብ አብጅ። እንዲሁም ስለ ጉዳዩ ጸልይ። ከዚያም ለራስህ የገባኸውን ቃል ለመጠበቅ ሞክር፤ ውሳኔህን በጽሑፍ ማስፈርም ሊረዳህ ይችላል። ተጨማሪ እርዳታ ማግኘት ከፈለግህ ደግሞ ከአንድ የምትተማመንበት ትልቅ ሰው፣ ለምሳሌ ከወላጆችህ ጋር ተወያይበት።

አንዳንድ ወጣቶች የሙዚቃ ፊልሞችን መመልከት የሚያስከትለውን አደጋ በማጤን እስከ ጭራሹ እንደዚህ ዓይነት ፊልሞችን ላለመመልከት ወስነዋል። በዚህ ረገድ የምታደርገው ውሳኔ ምንም ይሁን ምን የማስተዋል ችሎታህን ተጠቀምበት። ንጹህ ሕሊና ይኑርህ። ጤናማና የሚያድሱ መዝናኛዎችን ብቻ በመምረጥ ራስህን ከጉዳት ከመጠበቅህም በላይ ከይሖዋ ጋር ያለህ ወዳጅነት እንዳይበላሽ ማድረግ ትችላለህ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 በመጋቢት 2003 የንቁ! እትማችን ላይ የወጣውን “የወጣቶች ጥያቄ . . . የሙዚቃ ፊልሞችን ብመለከት ምን ጉዳት አለው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሥነ ምግባር ብልግናን በገሃድ የማያሳዩ ፊልሞችም እንኳን ጎጂ ሐሳቦችን ያስተላልፋሉ

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ የሚጠላቸውን ነገሮች ላለመመልከት ቁርጥ ውሳኔ አድርግ