በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

አሸርባሸር ምግቦችን ለሕፃናት ማስተዋወቅ

በርካታ የምግብ ጥናት ባለሙያዎች “የሕፃናትን አመጋገብ ልማድ በማዛባት ከልክ በላይ እንዲወፍሩ የሚያደርግ የታሰበበት የማስታወቂያ ዘመቻ” የሚያካሂዱ የታሸጉ ምግቦችን የሚያመርቱ ኩባንያዎችን እየከሰሱ ነው ሲል አይ ኤች ቲ አሳሂ ሺምቡን የተሰኘው የቶኪዮ ጋዜጣ ዘግቧል። ዘገባው “ሕፃናት ምርቶቹን እንዲገዙ ለመገፋፋት ዋነኛ የማስተዋወቂያ መሣሪያ ሆኖ የተገኘው ቴሌቪዥን” እንደሆነ ይገልጻል። ይሁን እንጂ የምግብ አምራች ኩባንያዎች “ምርቶቻቸውን ለሕፃናት ለማስተዋወቅ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።” ፊልሞች፣ ጨዋታዎች፣ የኢንተርኔት ድህረ ገጾች፣ የሂሣብ መጻሕፍትና ልዩ ልዩ ዓይነት አሻንጉሊቶች ሁሉ የምግብ ፋብሪካዎች ማስታወቂያዎች አሉባቸው። ለሕፃናት የሚያስተዋውቁት ግን ለምንድን ነው? “ያለው ትልቁ ገበያ እሱ ነው” በማለት በቴክሳስ ኤ ኤንድ ኤም ዩኒቨርሲቲ የማስታወቂያ ሥራዎች ፕሮፌሰር የሆኑት ጄምስ ማክኒል ይገልጻሉ። ይሁን እንጂ የሃርቫርድ የማኅበረሰብ ጤና ትምህርት ቤት ፕሮፌሰር የሆኑት ዎልተር ዊሌት “የምግብ አምራች ኩባንያዎች ከሚሸጡት ነገር ውስጥ አብዛኛው አሸርባሸር ነው። ለመሆኑ ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችን በተደጋጋሚ ሲያስተዋውቁ ያያችሁበት አጋጣሚ አለ?” ሲሉ ተናግረዋል።

የሙዚቃ ትምህርትና የማስታወስ ችሎታ

በቅርቡ የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳመለከተው “ሙዚቃ የሚማሩ ልጆች ከማይማሩት የበለጠ የማስታወስ ችሎታና የተሻለ የቃላት እውቀት ይኖራቸዋል” ሲል የካናዳው ግሎብ ኤንድ ሜይል ጋዜጣ አትቷል። በሆንግ ኮንግ የቻይና ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር አግኔስ ቻን እንደሚሉት ከሆነ ሙዚቃ መማር በስተ ግራ በኩል ያለውን የአንጎል ክፍል በማነቃቃት መላው አንጎል ይበልጥ ቀልጣፋ እንዲሆንና ቃላትን እንደ መማር ባሉ ሌሎች ተግባሮች ረገድ የተሻለ ብቃት እንዲኖረው አስተዋጽኦ ያደርጋል። ከ6 እስከ 15 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ 90 ተማሪዎች ቃላትንና የሚታዩ ነገሮችን ምን ያህል ማስታወስ እንደሚችሉ ለመመዘን የሚያስችል ግምገማ ተካሂዶ ነበር። የሙዚቃ ሥልጠና ያገኙ ልጆች ሥልጠናውን ካላገኙት ይበልጥ ብዙ ቃላትን ማስታወስ ችለዋል። የሙዚቃ ሥልጠናቸውን ለረዥም ጊዜ በቀጠሉ መጠን በዚያው ልክ ቃላትን የመማር ቅልጥፍናቸው የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል። ዶክተር ቻን እንደገለጹት የሙዚቃ ሥልጠናው የሚያስገኘው ጥቅም በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንደማለት ነው። ቻን እንደሚያምኑት ሙዚቃ የሚማሩ ልጆች “በትምህርት ቤት የሚሰጠው ትምህርት ቀላል ሳይሆንላቸው አይቀርም።”

ንፋስ የቀነሰ ጎማ

“በአውራ ጎዳናዎች ላይ ከሚከሰቱ 17 ከባድ የመኪና አደጋዎች ውስጥ አንዱ በጎማ ላይ ከሚፈጠር ችግር ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው” በማለት ቫሎር አክትዌል የተሰኘ የፈረንሳይ መጽሔት ገልጿል። በሚቸሊን የጎማ ፋብሪካ የተካሄዱ ጥናቶች እንዳመለከቱት “በ2002 ከ3 ተሽከርካሪዎች ውስጥ 2ቱ ቢያንስ አንዱ ጎማቸው ንፋስ ቀንሶ ተገኝቷል።” ፒዬር ሜኔንዴስ የተባሉት የሚቸሊን ጎማ ፋብሪካ የቴክኒካዊ ግንኙነት ዳይሬክተር እንደሚሉት ከሆነ “አሽከርካሪዎች የመኪና ጎማዎቻቸው ንፋስ ከበዛባቸው እንደሚፈነዱና ይህ ደግሞ በጣም ትንሽ ንፋስ ሲኖር ከሚያጋጥመው አደጋ የበለጠ አደገኛ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ይሁን እንጂ እውነታው የዚህ ተቃራኒ ነው።” የጎማ ንፋስ ከሚገባው በላይ ሲቀንስ ፍሬን ለመያዝ የሚያስቸግር ከመሆኑም በላይ ጎማዎቹ መንገዱን ቆንጥጠው ስለማይዙ “አሽከርካሪው በኩርባ ላይ በድንገት ለመታጠፍ ሲሞክር መኪናው ከቁጥጥር ውጭ ሊሆንበት ይችላል” በማለት ዘገባው ገልጿል። ከዚህም በላይ የጎማው ንፋስ በቀነሰ መጠን ጎማው ቅርጹን ይለውጣል። ይህም የጎማው ክፍሎች እንዲግሉ ስለሚያደርግ በድንገት ጎማው ሙሉ በሙሉ ሊተነፍስ ይችላል።

ከዋክብትና የባሕር አሸዋ

“በምሽት በሰማይ ላይ የሚታዩት ከዋክብት በመላው ዓለም ባሉ በረሃዎችና የባሕር ዳርቻዎች ሁሉ ካለው አሸዋ በ10 እጥፍ ይበልጣሉ” በማለት የለንደኑ ዘ ዴይሊ ቴሌግራፍ ዘግቧል። “የከዋክብት ተመራማሪዎች በመሬት ላይ ሆነን [በአጉሊ መነጽር] ልናያቸው የምንችል 70 ሺህ ሚሊዮን፣ ሚሊዮን፣ ሚሊዮን (ከ7 በኋላ 22 ዜሮዎች ያሉት ቁጥር) ከዋክብት እንዳሉ አስልተዋል።” ከአሜሪካ፣ ከአውስትራሊያና ከስኮትላንድ የተውጣጡት የከዋክብት ተመራማሪዎች “ለምድር ቅርብ በሆነ አንድ ትንሽ የአጽናፈ ዓለም ክልል ውስጥ ያሉትን ሁሉንም የከዋክብት ረጨቶች ከቆጠሩ” በኋላ እያንዳንዱ የከዋክብት ረጨት ምን ያህል ከዋክብትን እንደያዘ ገምተዋል። ከዚያም ከዚህ ግምት በመነሣት በቀሪው ሰማይ ላይ የሚገኙትን ከዋክብት ቁጥር ለመገመት ሞክረዋል። “ይህም ቢሆን በጽንፈ ዓለም ውስጥ ያሉት ከዋክብት ቁጥር ሳይሆን አጉሊ መነጽራችን ሊደርስበት በሚችለው ርቀት ላይ ያሉት ከዋክብት ቁጥር ነው” በማለት የተመራማሪዎቹ ቡድን መሪ የሆኑት አውስትራሊያዊው ዶክተር ሳይመን ድራይቨር ተናግረዋል። “ይህ ቁጥር ትልልቅ ቁጥሮችን ማስላት ለሚችል በሙያው የተካነ የከዋክብት ተመራማሪም እንኳ ለመረዳት የሚያዳግት ነው።” መብራት በሌለበት አካባቢ ማታ በጨለማ ያለ አጉሊ መነጽር ሊታዩ የሚችሉት ከዋክብት ብዛት ጥቂት ሺህ ብቻ ሲሆን የኤሌክትሪክ መብራት በሚበዛባቸው ትልልቅ ከተሞች ደግሞ ሊታዩ የሚችሉት ከዋክብት ከ100 አይበልጡም።