በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተራራው ማቱሳላ

የተራራው ማቱሳላ

የተራራው ማቱሳላ

በምዕራብ ዩናይትድ ስቴትስ ከባሕር ወለል በላይ 3,000 ሜትር ከፍታ ባላቸው ዋይት ማውንቴይንስ ተብለው በሚጠሩት ተራሮች ላይ የዓለማችን አንጋፋ ዛፍ እንደሆነ የሚነገርለት ማቱሳላ ወይም ሽማግሌው ሰው የሚባል የብሪስልኮን ዝርያ የሆነ ጥድ አለ። * ከ4,700 ዓመታት በላይ ዕድሜ እንዳለው የሚገመተው ይህ ዛፍ የማቱሳላ ጫካ በመባል ከሚታወቁት ጥንታዊ የብሪስልኮን ጥዶች መካከል በዕድሜ አንጋፋው ነው።

እነዚህ ዛፎች ይህን ያህል ዘመን የሚኖሩት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁመው ነው። ኒው ሳይንቲስት በተባለ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ዘገባ እንደሚለው “የዓመቱ አማካይ የዝናብ መጠን ከ30 ሴንቲ ሜትር ያነሰ ሲሆን ይህም በአብዛኛው በበረዶ መልክ የሚወርድ ስለሆነ የአካባቢው እርጥበት በጣም አነስተኛ ነው። እንዲሁም ዛፎቹ ያደጉት እምብዛም ንጥረ ነገሮች በሌሉት በሃ ድንጋይ ላይ ነው።” ይባስ ብሎ “አካባቢው ከፍተኛ ሙቀት ያለው ሲሆን ኃይለኛ ነፋስም ይነፍስበታል።”

ይሁን እንጂ እነዚህ ሁኔታዎች ለዛፎቹ ረጅም ዕድሜ መኖር አስተዋጽኦ ሳያበረክቱ አይቀሩም። ኒው ሳይንቲስት መጽሔት እንዲህ ይላል:- “አየሩ በጣም ደረቅ በመሆኑ ቫይረሶችና ባክቴሪያዎች እንኳ በዚህ አካባቢ መኖር አይችሉም። እንዲሁም [የብሪስልኮን ጥድ] እንጨት ጠንካራና ሙጫነት ያለው ስለሆነ በተባይ አይጠቃም። ትልቁ ስጋት መብረቅ ቢሆንም ዛፎቹ ተራርቀው የበቀሉ መሆናቸው እሳት እንዳይዛመት ያደርጋል።”

ዛፎቹ በዓመት ውስጥ የሚያድጉት ለ45 ቀናት ብቻ ነው። ይህ አዝጋሚ እድገታቸው የሚያገኙትን ውስን ምግብ እንዲቆጥቡ ይረዳቸዋል። ውፍረታቸው በመቶ ዓመት ውስጥ የሚጨምረው 25 ሚሊ ሜትር ብቻ ሲሆን ቅጠሎቻቸው ሳይረግፉ እስከ 30 ዓመት ይቆያሉ። ረጅም የሚባለው ዛፍ 18 ሜትር ገደማ የሚደርስ ርዝመት አለው። ተመራማሪዎች አንጋፋዎቹ ጥዶች ወደፊት ለተጨማሪ 500 ዓመታት ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገምታሉ።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሰውን ዕድሜ ለማራዘም የሚፈልጉ ሰዎች የብሪስልኮን ጥድ ረጅም ዘመን ለመኖር የቻለበት ምስጢር ምን እንደሆነ ለማወቅ ምርምር ማድረግ ጀምረዋል። ይሁን እንጂ ረጅም ዕድሜ መኖር የሚቻልበትን ምስጢር ለማወቅ ተራራ ወጥቶ በአንድ ያረጀ ዛፍ ላይ ምርምር ማድረግ ሳያስፈልግ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል። የዓለማችን ጥንታዊ መጽሐፍ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።” (ዮሐንስ 17:3) ማንኛውም ሰው ይህን እውቀት ማግኘት ይችላል። አንተስ ይህን እውቀት ለማግኘት ለምን አትመረምርም?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 የኖኅ አያት የነበረው ማቱሳላ 969 ዓመት የኖረ ሲሆን ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተመዘገቡት ዕድሜዎች ሁሉ ረጅሙ ነው።—ዘፍጥረት 5:27፤ ሉቃስ 3:36, 37

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በማቱሳላ ጫካ ውስጥ ከሚገኙት የብሪስልኮን ጥዶች መካከል አንዱ