በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥንዚዛ መርዝ የምትረጭበት መንገድ

ጥንዚዛ መርዝ የምትረጭበት መንገድ

ንድፍ አውጪ አለው?

ጥንዚዛ መርዝ የምትረጭበት መንገድ

▪ ቦምብ ጣይ የምትባለው ጥንዚዛ ቁመቷ ከ2 ሴንቲ ሜትር ያነሰ ቢሆንም ልዩ በሆነው የመከላከያ ዘዴዋ የታወቀች ናት። ይህች ሦስት አጽቄ አደጋ ሲደቀንባት በፊንጢጣዋ በኩል መጥፎ ጠረን ያለው ትኩስ ፈሳሽና እንፋሎት ስለምትረጭ ሸረሪቶችን፣ ወፎችንና እንቁራሪቶችን ጭምር ታባርራለች።

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ጥንዚዛዋ “በሆድ ዕቃዋ ጫፍ ላይ የሚከፈቱ ሁለት ዕጢዎች” አሏት። እነሱም እያንዳንዳቸው አሲድነት ያለው ውሕድና ሃይድሮጂን ፐሮክሳይድ የሚይዝ ማጠራቀሚያ እንዲሁም በውኃ የሟሙ ኤንዛይሞች የሞሉበት ማብላያ ክፍል አላቸው። ጥንዚዛዋ ራሷን ለመከላከል የሚያስችላትን ኬሚካላዊ ውህድ ለመፍጠር ከማጠራቀሚያዎቹ ውስጥ ፈሳሹን ጨምቃ በማውጣት ወደ ማብላያ ክፍሎቹ ትልከዋለች። ውጤቱ ምንድን ነው? አንድ መቶ ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሙቀት ያለው የሚገማ ኬሚካል፣ ውኃና እንፋሎት በአጥቂው ላይ ይረጫል። ማብላያ ክፍሎቹ ርዝመታቸው ከ1 ሚሊ ሜትር ያነሰ ቢሆንም ጥንዚዛዋ የምትረጨውን መርዛማ ንጥረ ነገር ፍጥነት፣ አቅጣጫና ይዘት መለዋወጥ ትችላለች።

ተመራማሪዎች ይበልጥ ውጤታማና በሥነ ምሕዳር ላይ ጉዳት የማያስከትል የመርጫ ዘዴ መሥራት የሚችሉበትን መንገድ ለማግኘት ሲሉ ቦምብ ጣይ በምትባለው ጥንዚዛ ላይ ጥናት ሲያካሂዱ ቆይተዋል። ተመራማሪዎቹ ይህች ጥንዚዛ ኬሚካሎች ወደ ማብላያ ክፍሎቹ እንዲያልፉ የሚያስችልና ለማስገባት ብቻ የሚያገለግል የፈሳሽ ዝውውር መቆጣጠሪያ ብቻ ሳይሆን ኬሚካሎቹን የምታስወጣበት የማስተንፈሻ መቆጣጠሪያ ጭምር እንዳላት ደርሰውበታል። መሐንዲሶች የመኪና ሞተሮችን፣ የእሳት ማጥፊያዎችን እንዲሁም በማሽተት መድኃኒቶችን ወደ ሰውነት የሚያስገቡ መሣሪያዎችን ንድፍ ለማውጣት ቦምብ ጣይ ጥንዚዛን መሠረት ያደረገ የመንፊያ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ተስፋ ያደርጋሉ። እንግሊዝ ውስጥ የሊድስ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር አንዲ ማክኧንታሽ “ከፊዚክስና ከምሕንድስና አንፃር ጥንዚዛን የእኛን ያህል ያጠና ሰው የለም። እኛም ብንሆን ይህን ያህል ብዙ ነገር ከእሷ እንማራለን ብለን አልጠበቅንም ነበር” ብለዋል።

ታዲያ ምን ይመስልሃል? ቦምብ ጣይ ጥንዚዛ ያላት ውስብስብ የሆነ የፈሳሽ መቆጣጠሪያ፣ ማፍያው እና የምትረጨው ንጥረ ነገር በአጋጣሚ የመጣ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Oxford Scientific/photolibrary