በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምን ለውጥ መምጣት አለበት?

ምን ለውጥ መምጣት አለበት?

ምን ለውጥ መምጣት አለበት?

“መንግሥት ለችግሮቻችን መፍትሔ አይሆንም፤ መንግሥት ራሱ ችግር ነው።”​—ሮናልድ ሬገን የዩናይትድ ስቴትስ 40ኛው ፕሬዚዳንት ሆነው ሲሾሙ ካደረጉት ንግግር ላይ የተወሰደ።

ሮናልድ ሬገን ይህን ከተናገሩ ከሠላሳ የሚበልጡ ዓመታት አልፈዋል። በወቅቱ ዩናይትድ ስቴትስ ከባድ ፈተና ተጋርጦባት ነበር፤ ሬገን ይህንን ሁኔታ “መጠነ ሰፊ ጉዳት ያስከተለ የኢኮኖሚ ችግር” በማለት ገልጸውታል። ሁኔታውን ቀጥለው ሲያስረዱ “በአገራችን ታሪክ የአሁኑን ያህል ለረጅም ጊዜ የዘለቀና ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለ የዋጋ ግሽበት አጋጥሞን አያውቅም” ብለዋል። አክለውም እንዲህ በማለት ተናግረዋል፦ “ላለፉት አሥርተ ዓመታት በዕዳ ላይ ዕዳ በማከማቸት ጊዜያዊ ጥቅም ለማግኘት ስንል በእኛም ሆኖ በልጆቻችን የወደፊት ሕይወት ላይ ችግር የሚፈጥር እርምጃ ስንወስድ ቆይተናል። በዚህ ሁኔታ ከቀጠልን ከፍተኛ የሆነ ማኅበራዊ፣ ባሕላዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ እንደምንገባ ምንም ጥርጥር የለውም።”

ምንም እንኳ ሬገን፣ ከሰጡት አስተያየት ጨለምተኛ መስለው ቢታዩም ጨርሶ ተስፋ አልቆረጡም። ሬገን እንዲህ በማለት ተናግረዋል፦ “የኢኮኖሚው ችግር ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ይዘነው የቆየን በሽታ ነው። በቀናት፣ በሳምንታት ወይም በወራት ውስጥ አይወገድም፤ ነገር ግን መወገዱ አይቀርም።”​—በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።

ታዲያ ዛሬ ሁኔታው ተሻሽሏል? የዩናይትድ ስቴትስ የቤቶችና የከተማ ልማት ቢሮ በ2009 ያወጣው አንድ ሪፖርት እንዲህ ይላል፦ “ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ በርካታ ሰዎች . . . መሠረተ ልማቶች ከተጠቃሚው ቁጥር ጋር ባለመመጣጠናቸው፣ በመኖሪያ ቤት እጥረትና የጤና አገልግሎቱ ወቅቱን የጠበቀ ባለመሆኑ ሳቢያ ችግር ላይ ወድቀዋል። እንዲያውም [በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር የሚንቀሳቀሰው] ዩ ኤን ሃቢታት የተባለው ድርጅት በሠላሳ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከሦስት ሰዎች አንዱ፣ ወደፊት ፈጽሞ ሊሻሻል የማይችል ሕይወት እንደሚመራ ተንብዩዋል፤ በሌላ አባባል እነዚህ ሰዎች፣ የሚኖሩበት ሁኔታ የንጽሕና አጠባበቅ ደረጃው የወረደ ይሆናል፤ የንጹሕ ውኃ እጥረት ያጋጥማቸዋል እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ለሚመጡ ችግሮች ይጋለጣሉ፤ ይህ ደግሞ ለበሽታዎች ምናልባትም ለወረርሽኝ መስፋፋት ምክንያት ይሆናል።”

መላውን ዓለም የሚነካ ስጋት

የምትኖረው የትም ይሁን የት እስቲ በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ለማሰብ ሞክር፦

● ከአሥር ዓመት በፊት የነበረህን ሁኔታ ከአሁኑ ጋር ስታነጻጽረው በገንዘብ ረገድ ያለብህ ስጋት እንደቀነሰ ይሰማሃል?

● አንተም ሆነ ቤተሰብህ የምታገኙት የጤና አገልግሎት በቂ ነው የሚል እምነት አለህ?

● ምድራችን ይበልጥ ጽዱና የተሻሻለች እንደሆነች ይሰማሃል?

● ስለ ወደፊቱ ጊዜ ስታስብ ከ10፣ ከ20 ወይም ከ30 ዓመት በኋላ ሁኔታዎች የሚሻሻሉ ይመስልሃል?

ማኅበራዊ ግዴታ

ብዙ መንግሥታት “ማኅበራዊ ግዴታ” ብለው የሚጠሩት ውል አላቸው፤ ይህ ውል በመንግሥትና በዜጎች መካከል የሚደረግ በጽሑፍ የሰፈረ አሊያም በልማድ የሚታወቅ ስምምነት ሲሆን በሁለቱም ወገን ያለውን መብትና ግዴታ በዝርዝር ይይዛል። ለምሳሌ ዜጎች የአገራቸውን ሕግ የማክበር፣ ግብር የመክፈልና ለአካባቢያቸው ደኅንነት አስተዋጽኦ የማበርከት ግዴታ አለባቸው። መንግሥታት ደግሞ በበኩላቸው ብዙ ጊዜ ቃል እንደሚገቡት በቂ የሆነ የጤና አገልግሎት የመስጠት፣ እኩልነትን የማስፈንና አስተማማኝ የሆነ ኢኮኖሚ የመገንባት ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።

ታዲያ መንግሥታት በእነዚህ ሦስት መስኮች ምን ውጤት አስገኝተዋል? በሚቀጥሉት ሦስት ገጾች ላይ የሰፈሩትን መረጃዎች ልብ በል።

በቂ የሆነ የጤና አገልግሎት

የሰዎች ፍላጎት፦ ውጤታማ የሆነ ሕክምና እንደ ልብ ማግኘት።

እውነታው፦

● የዓለም ባንክ ከንጽሕናና ከጤና አጠባበቅ ጋር በተያያዘ ያወጣው አንድ ሪፖርት እንደሚያሳየው “በንጽሕናና በጤና አጠባበቅ ጉድለት እንዲሁም በተበከለ ውኃ ምክንያት በሚመጡ በሽታዎች የተነሳ በየቀኑ 6,000 ሕፃናት ሕይወታቸውን ያጣሉ። በተቅማጥ በሽታ ብቻ በየ20 ሴኮንዱ አንድ ሕፃን ይሞታል።”

● የዓለም የጤና ድርጅት “በበለጸጉና በድሃ አገሮች” ውስጥ በሚሰጡት የጤና አገልግሎቶች ላይ በ2008 ባካሄደው ከፍተኛ ጥናት መሠረት ከጤና አገልግሎት ጋር በተያያዘ በድሃና በሀብታም አገሮች መካከል ያለው “ልዩነት ከፍተኛ” መሆኑን እንዲሁም “ማኅበረሰቡ የሚጠብቀውን ማለትም የሕዝቡን ፍላጎት ያገናዘበ፣ ሁሉንም በእኩል ደረጃ ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ አቅምን ግምት ውስጥ ያስገባና ውጤታማ የሆነ የጤና አገልግሎት መስጠት እንዳልተቻለ” አረጋግጧል።

ይህ ጥናት ከተካሄደ ከሁለት ዓመት በኋላ የዓለም የጤና ድርጅት እንደተናገረው ከሆነ “በመላው ዓለም ያሉ መንግሥታት ለጤና አገልግሎት የሚያስፈልገውን ወጪ መሸፈን እያቃታቸው ነው። የአረጋውያንና ሥር በሰደዱ በሽታዎች የሚሠቃዩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በሄደ መጠን እንዲሁም አዲስና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ የሕክምና ዓይነቶች በመጡ ቁጥር ለጤና አገልግሎት የሚያስፈልገው ወጪም በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀቡ አይቀርም።”

● ከሕክምና ጋር በተያያዘ የሰዎችን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ለየት ያለ ችግር ተከስቷል፤ ይኸውም በፈዋሽነታቸው ጉድ የተሰኘላቸው መድኃኒቶች የማዳን ኃይላቸው አጠያያቂ ሆኗል። በ1940ዎቹ ዓመታት አንቲባዮቲኮች በመገኘታቸው ከዓመታት በፊት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ይገድሉ የነበሩት እንደ ሥጋ ደዌና ሳንባ ነቀርሳ ያሉ በባክቴሪያ አማካኝነት የሚመጡ በሽታዎች በቁጥጥር ሥር ሊውሉ ችለው ነበር። አሁን ግን ወርልድ ሄልዝ ዴይ 2011 በተባለው የዓለም የጤና ድርጅት ሪፖርት መሠረት “መድኃኒት የማይበግራቸው በሽታ አምጪ ተሕዋስያን እየተፈጠሩ ከመሆኑም በላይ በፍጥነት እየተስፋፉ ነው። የመፈወስ ኃይላቸውን የሚያጡ በጣም አስፈላጊ የሆኑ መድኃኒቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። መድኃኒቶች በሽታን የመዋጋት አቅማቸው እየተዳከመ መጥቷል።”

ምን ለውጥ መምጣት አለበት? ሰዎች “ታምሜአለሁ” የማይሉበት ዘመን እንደሚመጣ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መፈጸም አለበት።​—ኢሳይያስ 33:24

ፍትሕና እኩልነት

የሰዎች ፍላጎት፦ አናሳ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች አለምክንያት የማይጠሉበት፣ በሴቶች ላይ በደል የማይፈጸምበት እንዲሁም ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል የሚኖርበት ሥርዓት ሰፍኖ ማየት።

እውነታው፦

● ሊደርሺፕ ኮንፈረንስ ኦን ሲቪል ራይትስ ኤጁኬሽን ፈንድ የተባለ ተቋም ባወጣው አንድ ሪፖርት ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ዘርን፣ ሃይማኖትን፣ ፆታን፣ የትውልድ አገርን መሠረት ባደረገ አጉል ጥላቻ ምክንያት በግለሰቦች፣ በአምልኮ ስፍራዎችና በማኅበራዊ ተቋማት ላይ የሚፈጸመው ጥቃት በአሜሪካ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ከመሆኑም በላይ ጉዳዩ አሳሳቢ እየሆነ ሄዷል።”

● የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ፕሮግረስ ኦቭ ዘ ወርልድስ ዊሜን፦ ኢን ፐርስዩት ኦቭ ጀስቲስ በሚል ጭብጥ በተዘጋጀ ሪፖርት ላይ ተመሥርቶ ያወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ “በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሴቶች በቤታቸው፣ በሥራ ቦታቸውና በአደባባይ ላይ የሚፈጸምባቸው ግፍ፣ ዓመፅና መድልዎ ዛሬም እንደቀጠለ” ይገልጻል። ለምሳሌ በአፍጋኒስታን 85 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች በወሊድ ወቅት የሕክምና እርዳታ አያገኙም። በየመን ደግሞ የቤት ውስጥ ጥቃቶችን የሚከለክል ሕግ የለም። በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክም ቢሆን በአማካይ በየቀኑ ከአንድ ሺህ የሚበልጡ ሴቶች ተገድደው ይደፈራሉ።

● የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ባን ኪሙን በጥቅምት ወር 2011 እንዲህ ብለው ነበር፦ “ዓለማችን ተቃራኒ ሁኔታዎች የሚታይበት ግራ የሚያጋባ ስፍራ ሆኗል። የተትረፈረፈ ምግብ እያለ በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይራባሉ። ጥቂቶች የተንደላቀቀ ሕይወት ሲመሩ በጣም ብዙ ሰዎች ግን በድህነት ይማቅቃሉ። በሕክምናው መስክ ከፍተኛ እድገት ቢታይም እናቶች በየቀኑ በወሊድ ወቅት ይሞታሉ። . . . ሰዎችን ለመጠበቅ ሳይሆን ለመግደል በቢልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለጦር መሣሪያ ይውላል።”

ምን ለውጥ መምጣት አለበት? አናሳ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችና ሴቶች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መያዝ አለባቸው፤ ‘ለተጨቆነው ሕዝብ ፍትሕ የሚያዛቡ’ ሰዎች መወገድ ይኖርባቸዋል።​—ኢሳይያስ 10:1, 2

አስተማማኝ የሆነ ኢኮኖሚ

የሰዎች ፍላጎት፦ ሁሉም ሰው የሥራ ዕድል የሚያገኝበትና በገንዘብ ረገድ ያለ ስጋት የሚኖርበት ሥርዓት ሰፍኖ ማየት።

እውነታው፦

● ወርልድዎች የተባለው ተቋም ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው ከሆነ “ኢኮኖሚውን ሊያሳድጉ የሚችሉ ብዙ ሠራተኞች ቢኖሩም ለእነዚህ ሁሉ የሚሆን ሥራ ማግኘት ግን አልተቻለም። የዓለም የሥራ ድርጅት (አይ ኤል ኦ) አሁን ባለው የኢኮኖሚ ውድቀት ምክንያት በ2010 የሥራ አጦች ቁጥር 205 ሚልዮን ደርሶ ሊሆን እንደሚችል ገምቷል።”

● “ከሥራ ማጣት ጋር በተያያዘ የዓለም ኢኮኖሚ በዓይነቱ አዲስና አሳሳቢ የሆነ ችግር ውስጥ ለመግባት አፋፍ ላይ መድረሱንና ይህ ደግሞ ሕዝባዊ ዓመፅ ሊያስከትል እንደሚችል የዓለም የሥራ ድርጅት አስጠንቅቋል” ሲል ቢቢሲ ዘግቧል። የዜና ዘገባው ሲቀጥል እንዲህ ይላል፦ “ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኢኮኖሚው እድገት እያሽቆለቆለ መምጣቱ ለሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር የተቻለው፣ ከሚያስፈልገው ውስጥ ለግማሽ ያህሉ ብቻ እንደሚሆን ያሳያል። . . . በተጨማሪም ድርጅቱ፣ ሥራ ማጣት ሰዎችን ምን ያህል እንደሚያበሳጭ እንዲሁም ቀውሱን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት አንዳንዶች ሸክሙን ለመጋራት ፈቃደኛ አለመሆናቸው ሌሎችን ምን ያህል እንደሚያስቆጣ አጥንተዋል። በርካታ አገሮች በተለይም የአውሮፓ ኅብረት አባል በሆኑና በአረብ አገሮች ውስጥ ሕዝባዊ ዓመፅ ሊነሳ እንደሚችል ገልጿል።”

● በ2009 የታተመው ዘ ናርሲሲዝም ኤፒዴሚክ የተባለው መጽሐፍ እንደተናገረው ከሆነ በዩናይትድ ስቴትስ “በአሁኑ ጊዜ በአማካይ የአንድ ሰው የክሬዲት ካርድ ዕዳ ከ11,000 ዶላር በላይ የደረሰ ሲሆን በ1990 ከነበረው በሦስት እጥፍ ጨምሯል።” የመጽሐፉ አዘጋጆች ከደረሱበት መደምደሚያ መገንዘብ እንደሚቻለው ብዙ ሰዎች ዕዳ ውስጥ የሚገቡት ሀብታም መስለው ለመታየት ሲሉ ብቻ ነው። ይኸው መጽሐፍ አክሎ እንዲህ ብሏል፦ “አሜሪካውያን የቅንጦት መኪናና ልብስ ያላቸውን ሰዎች ሲመለከቱ ሰዎቹ ሀብታም እንደሆኑ አድርገው ያስባሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን እነዚህ ሰዎች ዕዳ ውስጥ የተዘፈቁ እንደሆኑ አድርጎ ማሰቡ በአብዛኛው የተሻለ ነው።”

ምን ለውጥ መምጣት አለበት? ሁሉም ሰው የራሱ ሥራ ሊኖረው ይገባል፤ እንዲሁም ከገንዘብ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ሚዛኑን የጠበቀ አመለካከት ማዳበር አለበት። መጽሐፍ ቅዱስ “ገንዘብ ጥላ ከለላ እንደ ሆነ” ይናገራል፤ በሌላ በኩል ደግሞ “የገንዘብ ፍቅር የብዙ ዓይነት ጎጂ ነገሮች ሥር” እንደሆነ ያስጠነቅቃል።​—መክብብ 7:12፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:10

ከገጽ 4 እስከ 8 ላይ የቀረበውን ሐሳብ ስንመለከት የወደፊቱ ጊዜ የተሻለ እንደሚሆን ማሰብ ሊከብድ ይችላል። ይሁን እንጂ የዓለም ሁኔታ ተስፋ የሌለው አይደለም። ዓለማችን ወደፊት የተሻለ ስፍራ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም፤ ይሁን እንጂ ይህ የሚሆነው በሰብዓዊ መንግሥታት ጥረት አይደለም።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሰንጠረዥ]

ታዳጊ የሆኑ ወጣቶች በዓለም ላይ ምን ዓይነት ለውጦችን ማምጣት እንደሚፈልጉ ቢጠየቁ ምን መልስ ይሰጣሉ? www.4children.org የተባለው ድረ ገጽ እንደገለጸው ከሆነ በብሪታንያ ከ4 እስከ 14 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ 2,000 በሚያህሉ ልጆች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት ልጆቹ የሚከተሉትን ነገሮች ማድረግ እንደሚፈልጉ ጠቁሟል፦

[ሰንጠረዥ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

100%

ረሃብን ማጥፋት

ጦርነትን ማስቀረት

ድህነትን ማስወገድ

75%

እኩልነት የሰፈነበት ሥርዓት ማምጣት

የምድር ሙቀት እንዳይጨምር መከላከል

50%

25%

0%

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሰንጠረዥ]

ቤርተልስማን ፋውንዴሽን የተባለ ድርጅት በ2009 ጀርመን ውስጥ ያካሄደው ጥናት፣ ዕድሜያቸው ከ14 እስከ 18 የሆኑ 500 የሚያህሉ ወጣቶች ከሁሉ በላይ የሚያሳስባቸው ነገር ምን እንደሆነ ይፋ አድርጓል።

ወጣቶቹ ብዙም ቦታ ካልሰጧቸው ችግሮች መካከል አሸባሪነትና የሕዝብ ቁጥር መጨመር ይገኙበታል። የኢኮኖሚው ቀውስ ሳይቀር፣ ዝቅተኛ ደረጃ ከሰጧቸው ችግሮች ተርታ መድበውታል። ቤርተልስማን ፋውንዴሽን በደረሰበት ድምዳሜ መሠረት ወጣቶቹ ለእነዚህ ጉዳዮች ቦታ ያልሰጡት ችግሮቹ በሕይወታቸው ውስጥ ስላልገጠሟቸው ነው።

[ሰንጠረዥ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

100%

75%

ድህነት

የአየር ንብረት ለውጥና የአካባቢ መበላሸት

የምግብ እና የመጠጥ ውኃ እጥረት

ዓለም አቀፍ ወረርሽኞችና በሽታዎች

50%

25%

0%