በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ጣሊያን

በ2011 በጣሊያን የብስክሌቶች ሽያጭ ከመኪኖች ሽያጭ በልጦ ተገኝቷል። ለዚህ ምክንያት እንደሆኑ ከሚታሰቡት ነገሮች መካከል የኢኮኖሚው መውደቅ እንዲሁም የነዳጅ ዋጋ እና ለመኪኖች የሚወጣው የጥገና ወጪ መጨመር ይገኙበታል። በሌላ በኩል ግን ብስክሌቶች ለጥገና ብዙ ወጪ የማይጠይቁ ከመሆኑም ሌላ ለአጠቃቀም ምቹና ቀላል ናቸው።

አርሜንያ

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት፣ የአርሜንያ መንግሥት የ17 የይሖዋ ምሥክር ወጣቶችን መብት ተጋፍቷል የሚል ብይን ሰጥቷል፤ እነዚህ ወጣቶች በወታደራዊ አገልግሎት ምትክ የሚሰጠውን ከጦር ሠራዊት ጋር የተያያዘ አገልግሎት ለመፈጸም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ታስረው ነበር። መንግሥት ለ17ቱ ወጣቶች የጉዳት ካሳ እንዲከፍልና ከፍርድ ቤት ጋር በተያያዘ ያወጡትን ወጪ እንዲሸፍን ፍርድ ቤቱ ወስኗል።

ጃፓን

በማኅበራዊ ድረ ገጾች በመጠቀም ወንጀል የሚፈጽሙ ሰዎች ጥቃት ካደረሱባቸው ልጆች መካከል 63 በመቶ የሚሆኑት፣ ሊያጋጥማቸው ስለሚችለው አደጋ ከወላጆቻቸው ምንም ዓይነት ማስጠንቀቂያ አልተሰጣቸውም። ምርመራ በተካሄደባቸው 599 ጉዳዮች ላይ እንደታየው ከተከሳሾቹ መካከል 74 በመቶ የሚሆኑት በእነዚህ ድረ ገጾች የሚጠቀሙበት ዓላማ ትናንሽ ልጆችን ማስነወር እንደሆነ አምነዋል።

ቻይና

በዋና ዋና ከተሞች ያለውን የትራፊክ መጨናነቅ ለመቀነስ ሲባል በአዳዲስ መኪኖች ምዝገባ ላይ ገደብ እየተጣለ ነው። ለምሳሌ በቤጂንግ በዓመት ከ240,000 መኪኖች በላይ ላለመመዝገብ ተወስኗል። በነሐሴ 2012 የምዝገባ ፈቃድ ለማግኘት ዕጣ ካወጡ 1,050,000 ሰዎች መካከል ዕጣው የደረሳቸው 19,926 ብቻ ናቸው፤ ይህም ከ53 አመልካቾች መካከል ዕጣ የወጣለት አንድ ሰው ብቻ ነው ማለት ነው።