በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ጉልበተኞች ቢያስቸግሩኝ ምን ላድርግ?

ጉልበተኞች ቢያስቸግሩኝ ምን ላድርግ?

 ጉልበተኞች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ እንደ ቀላል የሚታይ ነገር አይደለም። በብሪታንያ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው፣ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ሕይወታቸውን እንዳጠፉ ከዘገቧቸው ወጣቶች መካከል ከ40 በመቶ በላይ የሚሆኑት ይህን እርምጃ እንዲወስዱ ምክንያት ከሆኗቸው ነገሮች ውስጥ የጉልበተኞች ጥቃት ተጠቃሽ ነው።

 ጉልበተኞች ሌሎችን የሚያስቸግሩት በየትኞቹ መንገዶች ነው?

 ጉልበተኞች የሚያደርሱት ጥቃት አካላዊ ብቻ አይደለም። የሚከተሉትን ነገሮችም ሊጨምር ይችላል።

  •   መጥፎ ንግግር። የ20 ዓመቷ ሴሊን እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ሴቶች ልጆች በጣም የሚጎዳ ነገር ይናገራሉ። ይሰድቡኝና ይናገሩኝ የነበረውን ነገር መቼም አልረሳውም። ዋጋ ቢስ፣ የማልፈለግና የማልረባ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ አድርገውኛል። ከዚህ ሁሉ ቢመቱኝ ይሻለኝ ነበር።”

  •   ማግለል። የ18 ዓመቷ ሄሊ እንዲህ ብላለች፦ “አብረውኝ የሚማሩት ልጆች ያገልሉኝ ጀመር። ምሳ ሰዓት ላይ ከእነሱ ጋር ተቀምጬ እንዳልበላ ሲሉ ጠረጴዛው ላይ ያለው ቦታ ሁሉ እንደተያዘ ያስመስላሉ። ዓመቱን ሙሉ ብቻዬን ለመብላት የተገደድኩ ሲሆን በዚህ የተነሳ አለቅስ ነበር።”

  •   ሳይበርቡሊ። a የ14 ዓመቱ ዳንኤል እንዲህ ብሏል፦ “ኮምፒውተር ላይ ጥቂት ቃላትን በመጻፍ ብቻ! የአንድን ሰው ስም ማጥፋት አልፎ ተርፎም ሕይወቱን ማበላሸት ይቻላል። ነገሩ የተጋነነ ቢመስልም እንኳ እውነታው ይኸው ነው” ሳይበርቡሊ የሚያደርጉ ሰዎች በሞባይል ስልክ አማካኝነትም ጎጂ የሆኑ ፎቶግራፎችን ወይም የጽሑፍ መልእክቶችን ሊልኩ ይችላሉ።

 ጉልበተኞች ሌሎችን የሚያስቸግሩት ለምንድን ነው?

 ከዋነኞቹ ምክንያቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል።

  •   እነሱ ራሳቸው በሌሎች ጉልበተኞች ጥቃት ደርሶባቸዋል። “እኩዮቼ የሆኑ ልጆች ያስቸግሩኝ ነበር፤ ነገሩ በጣም ስላንገሸገሸኝ ተቀባይነት ለማግኘት ስል ብቻ እኔም ሌሎችን ማስቸገር ጀመርኩ” በማለት አንቶኒዮ የተባለ ወጣት ተናግሯል። “ከጊዜ በኋላ ነገሩን መለስ ብዬ ሳስበው ግን ያደረግሁት ነገር ስህተት መሆኑን ተገነዘብኩ!”

  •   ጥሩ አርዓያ የሚሆናቸው ሰው አላገኙም። ጄይ መግሮው ላይፍ ስትራቴጂስ ፎር ዲሊንግ ዊዝ ቡሊስ በተባለው መጽሐፉ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ጉልበተኛ የሆኑ ትናንሽ ልጆች አብዛኛውን ጊዜ በሌሎች ላይ የሚያደርጉት . . . ወላጆቻቸው፣ ታላላቅ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ወይም ሌሎች የቤተሰባቸው አባላት ሲያደርጉ ያዩትን ነገር ነው።”

  •   የሌሎች የበላይ እንደሆኑ ለማሳየት ቢሞክሩም በራሳቸው አይተማመኑም። “በሌሎች ላይ ጉልበተኛ የሚሆኑት ስሜታቸውን የሚጎዳ ነገር ያጋጠማቸው ወይም የበታችነት ስሜት የሚሰማቸው ልጆች ናቸው፤ ይህንን ስሜታቸውን ለመሸፈን ሲሉ በሌሎች ላይ ጉልበተኛ በመሆን የበላይ መስለው ለመታየት ይጥራሉ” በማለት ባርብራ ኮሎሮሶ ዘ ቡሊ፣ ዘ ቡሊድ ኤንድ ዘ ባይስታንደር በተባለው መጽሐፏ ላይ ተናግራለች።

 ጉልበተኞች ብዙውን ጊዜ የሚያጠቁት እነማንን ነው?

  •   ብቸኛ የሆኑ ልጆችን። አንዳንድ ወጣቶች ከሌሎች ጋር መቀላቀል ስለሚቸግራቸው ብቻቸውን ይሆናሉ፤ በመሆኑም ጉልበተኞች በቀላሉ ያጠቋቸዋል።

  •   ከእኩዮቻቸው ለየት ብለው የሚታዩ ልጆችን። አንዳንድ ልጆች በጉልበተኞች ጥቃት የሚደርስባቸው በመልካቸው፣ በዘራቸው፣ በሃይማኖታቸው ሌላው ቀርቶ የአካል ጉዳተኛ በመሆናቸው ምክንያት ነው፤ ጉልበተኛው በእነሱ ላይ ለማሾፍ ሰበብ የሚሆነውን ማንኛውንም ምክንያት ይጠቀማል።

  •   በራሳቸው የማይተማመኑ ልጆችን። ጉልበተኞች ራሳቸውን ዝቅ አድርገው የሚመለከቱ ልጆችን ማወቅ አይቸግራቸውም። እንደዚህ ያሉት ልጆች ጥቃት ሲሰነዘርባቸው ብዙውን ጊዜ ዝም ስለሚሉ በቀላሉ ለጉልበተኞች ጥቃት ይጋለጣሉ።

 ጉልበተኞች የሚያስቸግሩህ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ?

  •   ችላ ብለህ እለፈው። “ጉልበተኞች ስለ ራሳችሁ መጥፎ እንዲሰማችሁ ማድረግ እንደቻሉ ሲያውቁ ደስ ይላቸዋል” በማለት ካይሊ የተባለች ወጣት ተናግራለች። “የሚያደርጉትን ነገር ችላ ብላችሁ የምታልፉት ከሆነ እናንተን ማስቸገር ይሰለቻቸዋል።” መጽሐፍ ቅዱስ “አስተዋዮች ግን በትዕግሥት ቍጣቸውን ይገታሉ” ይላል።​—ምሳሌ 29:11 የ1980 ትርጉም

  •   ብድር አትመልስ። መበቀል ችግሩን ያባብሰው ይሆናል እንጂ መፍትሔ አይሆንም። መጽሐፍ ቅዱስ “ለማንም በክፉ ፋንታ ክፉ አትመልሱ” ይላል።​—ሮም 12:17፤ ምሳሌ 24:19

  •   ጥቃት እንዲደርስብህ የሚያደርግ ሁኔታ ውስጥ ላለመግባት ተጠንቀቅ። ከጉልበተኞች እንዲሁም እንዲህ ያሉ ልጆች እንዲያስቸግሩህ መንገድ ከሚከፍቱ ሁኔታዎች በተቻለ መጠን ለመራቅ ጥረት አድርግ።​—ምሳሌ 22:3

  •   እነሱ ያልጠበቁትን ምላሽ ስጣቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “የለዘበ መልስ ቍጣን ያበርዳል” ይላል።​—ምሳሌ 15:1

  •   ቀልደህ ለማለፍ ሞክር። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ጉልበተኛ በውፍረትህ ቢያሾፍብህ፣ ከመበሳጨት ይልቅ “እንዲያውም አስታወስከኝ፤ ሰሞኑን ስፖርት ልጀምር አስቤያለሁ” ልትለው ትችላለህ።

  •   ምንም ምላሽ አትስጥ። የ19 ዓመቷ ኖራ እንዲህ ብላለች፦ “ነገሩን በዝምታ ማለፋችሁ ብስለት እንዳላችሁና ከሚያስቸግራችሁ ሰው የበለጠ ጠንካራ እንደሆናችሁ የሚጠቁም ነው። ከጉልበተኛው በተለየ እናንተ ራሳችሁን መቆጣጠር እንደምትችሉ እያሳያችሁ ነው።”

  •   በራስ የመተማመን መንፈስ ለማዳበር ጥረት አድርግ። “ጉልበተኞች እንደፈራህ በቀላሉ ማወቅ ይችላሉ፤ ይህን ሲመለከቱ ደግሞ በራስ የመተማመን ስሜትህን ይበልጥ ማዳከም ይፈልጋሉ” በማለት ሪታ የተባለች ወጣት ተናግራለች።

  •   ጉዳዩን ለሌላ ሰው ተናገር። አንድ ጥናት እንደሚያሳየው፣ ጉልበተኞች በኢንተርኔት ከሚያስቸግሯቸው ልጆች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሚደርስባቸውን ነገር ለማንም አይናገሩም፤ ከመናገር ወደኋላ የሚሉት ጉዳዩ ስለሚያሳፍራቸው (በተለይ ወንዶች ልጆች) ወይም ቢናገሩ የባሰ እንደሚሆንባቸው ስለሚፈሩ ነው። ይሁን እንጂ ጉዳዩን በሚስጥር መያዝህ ለጉልበተኞቹ እንደሚመቻቸው አትርሳ። ጥቃቱ እንዲያቆምልህ ከፈለግህ ልትወስደው የሚገባው የመጀመሪያ እርምጃ ስለ ጉዳዩ ለሌሎች መናገር ነው።

a በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የተጠቀሱት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።