በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ትንባሆ እና የኤሌክትሮኒክ ሲጋራ ስለማጨስ ምን ማወቅ ይኖርብኛል?

ትንባሆ እና የኤሌክትሮኒክ ሲጋራ ስለማጨስ ምን ማወቅ ይኖርብኛል?

 “እኔ በምኖርበት አካባቢ ትንባሆ ወይም የኤሌክትሮኒክ ሲጋራ አጭሶ የማያውቅ ከ25 ዓመት በታች ያለ ሰው ማግኘት ከባድ ነው።”—ጁሊያ

በዚህ ርዕስ ውስጥ

 ልታውቀው የሚገባ ነገር

  •   ሲጋራ ገዳይ ነው። የትንባሆ ዋነኛ ግብአት የሆነው ኒኮቲን የተባለው ንጥረ ነገር ከፍተኛ ሱስ የማስያዝ አቅም ያለው መርዛማ ንጥረ ነገር ነው። የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል እንደገለጸው “በዓለም ዙሪያ ሰዎችን ለበሽታ እየዳረጉና ያለዕድሜያቸው እየቀጩ ካሉ በቀላሉ ልንከላከል የምንችላቸው ጎጂ ነገሮች መካከል ዋነኛው ትንባሆ ነው።”

     “የምሠራው በሕክምናው መስክ የአልትራሳውንድ ባለሙያ ሆኜ ነው፤ ማጨስ በታማሚዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል በአልትራሳውንድ ምስሎቹ ላይ በግልጽ አይቻለሁ። አጫሽ በነበሩ ሰዎች የደም ሥር ላይ ምን ያህል ግግር እንደሚለጠፍ ስታዩ ትገረማላችሁ። ለሰውነቴ ከፍተኛ አክብሮት ስላለኝ፣ ሲጋራ ማጨስ መሞከር እንኳ የማልፈልገው ነገር ነው።”—ቴሪሳ

     ይህን ታውቅ ነበር? በሲጋራ ውስጥ 7,000 ገደማ ኬሚካሎች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ መርዛማ ናቸው። በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ትንባሆ ከማጨስ ጋር ተያይዘው በሚመጡ በሽታዎች ይሞታሉ።

  •   የኤሌክትሮኒክ ሲጋራ የሚያጨሱ ሰዎች ለመርዛማ ኬሚካሎች ይጋለጣሉ። የኤሌክትሮኒክ ሲጋራ ማጨስ የሳንባ ጉዳት ወይም ሞት ሊያስከትል እንደሚችል ተደርሶበታል። ደግሞም እንደ ትንባሆ ሁሉ ብዙዎቹ የኤሌክትሮኒክ ሲጋራ ምርቶችም ኒኮቲን አላቸው። በኤሌክትሮኒክ ሲጋራ ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንደገለጸው ኒኮቲን በጣም ሱስ የሚያስይዝ ንጥረ ነገር ስለሆነ “ወጣቶች ለሌሎች ዕፆችም ሱሰኛ እንዲሆኑ አእምሯቸውን ሊያላምደው ይችላል።”

     “የጥጥ ከረሜላ እና የኢንጆሪ ጣዕም የሚል ስም ያላቸው የኤሌክትሮኒክ ሲጋራዎች ደስ የሚል ቃና አላቸው፤ ይህም በተለይ ልጆችንና በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶችን ይማርካል። ጣዕሙ፣ ጎጂነቱን እንዳያስቡ ያደርጋቸዋል።”—ሚራንዳ

     ይህን ታውቅ ነበር? ከኤሌክትሮኒክ ሲጋራዎች የሚወጣው ተን፣ ውኃ ብቻ አይደለም። መርዛማ ቅንጣቶችን የያዙ ጎጂ ንጥረ ነገሮች ያሉት ሲሆን እነዚህ ንጥረ ነገሮች ወደ ሳንባ ይገባሉ።

 ትንባሆና የኤሌክትሮኒክ ሲጋራ ከማጨስ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች

  1.  (1) ታዳጊ በሆኑ ልጆች አእምሮ ላይ የመረዳትና ትኩረትን የመሰብሰብ ችግር እንዲሁም የስሜት መዋዠቅ

  2.  (2) የድድ መቆጣትና የጥርስ መበላሸት

  3.  (3) ሥር የሰደደ የሳንባ መቆጣትና የልብ ሕመም

     እየተባባሰ የሚሄድ የአስም በሽታ

     የሆድ ዕቃ መታወክና ማቅለሽለሽ

 ምን ማድረግ ትችላለህ?

  •   መረጃ ይኑርህ። የምትሰማውን ሁሉ አትመን፤ ለምሳሌ የኤሌክትሮኒክ ሲጋራ ማጨስ ምንም ጉዳት እንደሌለው ወይም ውጥረትን ለማቅለል የሚረዳ ጥሩ ዘዴ እንደሆነ ልትሰማ ትችላለህ። የራስህን ምርምር አድርገህ በእውቀት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ አድርግ።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ተላላ ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን አንድ በአንድ ያጤናል።”—ምሳሌ 14:15

     “ታዋቂ ሰዎች ወይም እኩዮችህ ትንባሆና የኤሌክትሮኒክ ሲጋራ ሲያጨሱ ስታይ ምንም ጉዳት የሌለው ‘መዝናኛ’ ሊመስልህ ይችላል፤ እንዲህ ማድረግ ስለሚያስከትለው መጥፎ ውጤት ስታስብ ግን እውነታው ከዚህ የተለየ እንደሆነ ትገነዘባለህ።”—ኤቫን

     ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ በእርግጥ ትንባሆና የኤሌክትሮኒክ ሲጋራ የሚያጨሱ ወጣቶች ከማያጨሱት የበለጠ ደስተኛ ናቸው? አሁንም ሆነ ወደፊት በሕይወታቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ውጥረት የሚፈጥሩ ነገሮች ለመጋፈጥ ከሌሎች ይበልጥ ዝግጁ ናቸው? ወይስ በራሳቸው ላይ የከፋ ችግር እያመጡ ነው?

  •   ውጥረትን ለመቋቋም የሚረዱ ውጤታማ ዘዴዎችን ፈልግ። ውጥረትን ለመቀነስ ከሚያስችሉ ጥሩ ዘዴዎች መካከል ስፖርት እንደ መሥራት፣ እንደ ማንበብ ወይም ከሚያበረታቱህ ጓደኞች ጋር ጥሩ ጊዜ እንደ ማሳለፍ ያሉ ጤናማ እንቅስቃሴዎች ይገኙበታል። በእነዚህ እንቅስቃሴዎች ስትካፈል ልታተኩርበት የምትችል ብዙ ጥሩ ነገር ስለምታገኝ ለማጨስ አትፈተንም።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “በሰው ልብ ውስጥ ያለ ጭንቀት ልቡ እንዲዝል ያደርገዋል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል።”—ምሳሌ 12:25

     “ሰዎች ትንባሆና የኤሌክትሮኒክ ሲጋራ ማጨስ ውጥረትን ለማቅለል እንደሚረዳ ይሰማቸዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን እነዚህ ነገሮች ጊዜያዊ እፎይታ ብቻ አስገኝተው ዘላቂ መዘዝ ጥለው ያልፋሉ። ውጥረትን መቋቋም የሚቻልባቸው የተሻሉ መንገዶች አሉ።”—አንጄላ

     ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ውጥረትን በተሻለ መንገድ ለመቋቋም አንተን ሊረዱህ የሚችሉ አንዳንድ ዘዴዎች የትኞቹ ናቸው? በዚህ ረገድ እርዳታ ከፈለግክ “የወጣቶች ጥያቄ” በሚለው ዓምድ ሥር የወጣውን “ጭንቀትን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።

ጭንቀትን ለመቋቋም ሱስ የሚያስይዙ ነገሮችን መጠቀም ከዝናብ ሸሽቶ ባሕር ውስጥ እንደ መግባት ነው፤ ችግሩን ከማባባስ ውጭ የሚፈይደው ነገር የለም!

  •   የእኩዮችን ተጽዕኖ ለመቋቋም ተዘጋጅ። ይህ ተጽዕኖ አብረውህ ከሚማሩ ልጆች፣ ብሎም ከምትዝናናባቸው ነገሮች ሊመጣ ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ፊልሞች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና ማኅበራዊ ሚዲያ ትንባሆና የኤሌክትሮኒክ ሲጋራ ማጨስ የዘመናዊነት መገለጫና ዘና የሚያደርግ ነገር እንደሆነ አድርገው ያቀርባሉ።

     ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ “የማስተዋል ችሎታቸውን በማሠራት [ያሠለጠኑ] ጎልማሳ ሰዎች [ናቸው]።”—ዕብራውያን 5:14

     “ተማሪ ሳለሁ ብዙ እኩዮቼ ላለማጨስ ባደረግኩት ውሳኔ ያከብሩኝ ነበር። አቋሜን ግልጽ ካደረግኩ በኋላ ጥብቅና ጭምር ይቆሙልኝ ነበር። ስለዚህ፣ ላይመስላችሁ ቢችልም አቋማችሁን ግልጽ ማድረጋችሁ ጥበቃ ሊሆንላችሁ ይችላል።”—አና

     ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ የእኩዮችን ተጽዕኖ በመቋቋም ረገድ ምን ያህል ተሳክቶልሃል? የእኩዮችን ተጽዕኖ የተቋቋምክባቸው አጋጣሚዎች ትዝ ይሉሃል? በዚህ ረገድ እርዳታ ካስፈለገህ ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2፣ ምዕራፍ 15 ላይ የሚገኘውን “የእኩዮችን ተጽዕኖ መቋቋም” የሚለውን የመልመጃ ሣጥን ተመልከት።

  •   ጓደኞችህን በጥንቃቄ ምረጥ። ትንባሆና የኤሌክትሮኒክ ሲጋራ ስለማጨስ ያለህን አቋም ጓደኞችህም የሚጋሩ ከሆነ ለማጨስ እምብዛም ላትፈተን ትችላለህ።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ከጥበበኞች ጋር የሚሄድ ጥበበኛ ይሆናል፤ ከሞኞች ጋር የሚገጥም ግን ጉዳት ይደርስበታል።”—ምሳሌ 13:20

     “ራሳቸውን ከሚገዙና በአቋማቸው ከሚጸኑ ሰዎች ጋር ጓደኛ መሆን በጣም ይረዳል። እንዲህ ማድረጋቸው ምን ያህል እንደጠቀማቸው ስታዩ እናንተም እንደ እነሱ ለመሆን ትነሳሳላችሁ።”—ካልቪን

     ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ የቅርብ ጓደኞችህ ንጹሕና ጤናማ ሕይወት ለመምራት ባደረግከው ውሳኔ ይደግፉሃል? ወይስ ውሳኔህን እንድታላላ ተጽዕኖ ያደርጉብሃል?

 ማሪዋናን በተመለከተስ ምን ማወቅ ይኖርብሃል?

 ብዙ ሰዎች ማሪዋና ምንም ጉዳት እንደሌለው ይናገራሉ። ሆኖም ይህ ውሸት ነው!

  •   ማሪዋና የሚጠቀሙ ወጣቶች ሱሰኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ማሪዋና የማሰብ ችሎታ መቀነስን ጨምሮ በአእምሮ ላይ ዘላቂ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።

  •   የዩናይትድ ስቴትስ የዕፅ ሱስና የአእምሮ ጤንነት አገልግሎቶች አስተዳደር እንደገለጸው “ማሪዋና የሚያጨሱ ሰዎች ከማያጨሱ ሰዎች አንጻር ሲታዩ ከሌሎች ጋር ያላቸው ግንኙነት መጥፎ እንደሚሆን እንዲሁም የትምህርት ውጤታቸው፣ በሥራቸው የሚያገኙት ስኬት እንዲሁም ከሕይወት የሚያገኙት እርካታ ዝቅተኛ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ።”

     “ማሪዋና ለማጨስ የተፈተንኩበት ዋነኛው ምክንያት ከጭንቀቴ እፎይታ ማግኘት ስለፈለግኩ ነበር። ሆኖም የሚያመጣብኝን ሱስ፣ ለዚያ ስል የማወጣውን ገንዘብና በጤንነቴ ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ሳስብ ማሪዋና ማጨስ ጭንቀቴን ከማባባስ ውጭ የሚፈይድልኝ ነገር እንደሌለ ተረዳሁ።”—ጁዳ