በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ልጠመቅ?—ክፍል 3፦ ያገደኝ ምንድን ነው?

ልጠመቅ?—ክፍል 3፦ ያገደኝ ምንድን ነው?

 ራስህን ለይሖዋ ስለመወሰንና ስለ መጠመቅ ስታስብ ፍርሃት ፍርሃት ይልሃል? ከሆነ ይህ ርዕስ ፍርሃትህን ለማሸነፍ ይረዳሃል።

በዚህ ርዕስ ውስጥ

 ከተጠመቅኩ በኋላ ከባድ ስህተት ብሠራስ?

 አሳሳቢ የሆነው ለምንድን ነው? ከባድ ኃጢአት በመሥራቱ የተነሳ ከጉባኤ የተወገደ ሰው ታውቅ ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 5:11-13) በመሆኑም አንተም ተመሳሳይ ነገር እንዳያጋጥምህ ትፈራ ይሆናል።

 “መጀመሪያ ላይ ስለ መጠመቅ ሳስብ ‘ጥፋት ባጠፋስ’ የሚለው ጉዳይ ያስፈራኝ ነበር። እንዲህ ባደርግ ወላጆቼን በጣም እንደማሳፍራቸው ይሰማኝ ነበር።”—ሬቤካ

 ቁልፍ ጥቅስ፦ “ክፉ ሰው መንገዱን . . . ይተው፤ ምሕረት ወደሚያሳየው አምላካችን ወደ ይሖዋ ይመለስ፤ ይቅርታው ብዙ ነውና።”—ኢሳይያስ 55:7

 እስቲ አስበው፦ ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞች ከጉባኤ እንደሚወገዱ አይካድም፤ ሆኖም ይሖዋ በትሕትና ንስሐ ለሚገቡና የተሰጣቸውን እርማት ለሚቀበሉ ሰዎች ምሕረት ያሳያል።—መዝሙር 103:13, 14፤ 2 ቆሮንቶስ 7:11

 በዚያ ላይ አንድ እውነታ አትዘንጋ፦ ፍጹም ባትሆንም እንኳ በአምላክ እርዳታ ፈተናን መቋቋም ትችላለህ። (1 ቆሮንቶስ 10:13) ደግሞስ ምን እንደምታደርግ የሚወስነው ማን ነው? አንተ ራስህ ነህ? ወይስ ሌላ ሰው?

 “ከተጠመቅኩ በኋላ ከባድ ስህተት ልሠራ እንደምችል በማሰብ እፈራ ነበር፤ በኋላ ግን ከመጠመቅ ወደኋላ ማለት ራሱ ስህተት እንደሆነ ተገነዘብኩ። ነገ ምን ይሆናል የሚለውን በማሰብ ዛሬ ማድረግ ያለብኝን ነገር ከማድረግ ወደኋላ ማለት እንደሌለብኝ አስተዋልኩ።”—ካረን

 ዋናው ነጥብ፦ አንተ እስከመረጥክ ድረስ ከባድ ኃጢአት ከመፈጸም መቆጠብ ትችላለህ፤ አብዛኞቹ የይሖዋ አገልጋዮች እንዲህ አድርገዋል።—ፊልጵስዩስ 2:12

 ተጨማሪ ሐሳብ ማግኘት ትፈልጋለህ?ፈታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።

 ጥምቀት የሚያስከትለው ኃላፊነት ቢያስፈራኝስ?

 አሳሳቢ የሆነው ለምንድን ነው? ምናልባትም አገልግሎታቸውን ለማስፋት ሲሉ ከቤተሰባቸውና ከጓደኞቻቸው ርቀው የሄዱ ወጣቶችን ታውቅ ይሆናል። በመሆኑም ሰዎች አንተም ተመሳሳይ ነገር እንድታደርግ እንደሚጠብቁብህ በማሰብ ትጨነቅ ይሆናል።

 “የተጠመቁ ክርስቲያኖች ተጨማሪ ኃላፊነት የመቀበል አጋጣሚ አላቸው፤ ግን አንዳንዶች ራሳቸውን በዚህ መልኩ ለማቅረብ ዝግጁ ላይሆኑ ይችላሉ፤ ወይም ደግሞ ሁኔታቸው ላይፈቅድላቸው ይችላል።”—መሪ

 ቁልፍ ጥቅስ፦ “እያንዳንዱ ሰው የራሱን ተግባር ይመርምር፤ ከዚያም ራሱን ከሌላ ሰው ጋር ሳያወዳድር ከራሱ ጋር ብቻ በተያያዘ እጅግ የሚደሰትበት ነገር ያገኛል።”—ገላትያ 6:4

 እስቲ አስበው፦ ራስህን ከሌሎች ጋር ከማወዳደር ይልቅ ማርቆስ 12:30 እንደሚለው “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ” ለመውደድ ጥረት ብታደርግ የተሻለ አይሆንም?

 ይሖዋ ማገልገል ያለብህ በሙሉ ልብህ እንጂ በሌላ ሰው ልብ እንዳልሆነ አስታውስ። ይሖዋን ከልብህ የምትወደው ከሆነ ለእሱ ምርጥህን መስጠት የምትችልባቸው መንገዶች ማግኘትህ አይቀርም።

 “ጥምቀት በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው እርምጃ ቢሆንም ከባድ ሸክም አይደለም። ጥሩ ጓደኞች ካሉህ እነሱ ያግዙሃል። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ቀስ በቀስ ተጨማሪ ኃላፊነቶችን መሸከም ይበልጥ ደስተኛ ያደርግሃል። ከመጠመቅ ወደኋላ ብትል ብዙ ነገር ይቀርብሃል።”—ጁልያ

 ዋናው ነጥብ፦ ይሖዋ ላሳየህ ፍቅር አድናቆት አዳብር። ይህም በምላሹ ለእሱ ምርጥህን ለመስጠት ያነሳሳሃል።—1 ዮሐንስ 4:19

 ተጨማሪ ሐሳብ ማግኘት ትፈልጋለህ?ኃላፊነት የሚሰማው ሰው ነኝ?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።

 ይሖዋን ለማገልገል ብቁ እንዳልሆንኩ ቢሰማኝስ?

 አሳሳቢ የሆነው ለምንድን ነው? ይሖዋ የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ ነው። ከእሱ አንጻር ሰው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም! በመሆኑም ይሖዋ ከነመፈጠርህ እንኳ የሚያውቅህ መሆኑን ትጠራጠር ይሆናል።

 “ወላጆቼ የይሖዋ ምሥክሮች ስለሆኑ ከይሖዋ ጋር ያለኝ ወዳጅነት ከእነሱ ‘የወረስኩት’ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር፤ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደሳበኝ አይሰማኝም ነበር።”—ናታሊ

 ቁልፍ ጥቅስ፦ “የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል ሰው የለም።”—ዮሐንስ 6:44

 እስቲ አስበው፦ ስለ ጥምቀት እያሰብክ መሆኑ በራሱ ይሖዋ ወደ እሱ ይበልጥ እንድትቀርብ እየሳበህ መሆኑን የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ግብዣውን ልትቀበል አይገባም?

 ደግሞም ይሖዋ የሚስባቸውን ሰዎች በተመለከተ መሥፈርት የሚያወጣው እሱ ራሱ እንጂ አንተም ሆንክ ሌላ ሰው እንዳልሆነ አትዘንጋ። መጽሐፍ ቅዱስም ‘ወደ አምላክ ከቀረብክ እሱም ወደ አንተ እንደሚቀርብ’ ዋስትና ይሰጣል።—ያዕቆብ 4:8

 “ይሖዋን ማወቅህና ወደ እሱ መቅረብህ በራሱ እሱ እንደሚወድህ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ስለዚህ አእምሮህ ይሖዋን ለማገልገል ብቁ እንዳልሆንክ በሚነግርህ ጊዜ ይሖዋ እንደዚያ እንደማይሰማው አስታውስ። ይሖዋ ደግሞ አይሳሳትም።”—ሰሊና

 ዋናው ነጥብ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የጥምቀት ብቃት ካሟላህ ይሖዋን ለማምለክ ብቁ ነህ ማለት ነው። ደግሞም ይሖዋ አምልኮህ ይገባዋል።—ራእይ 4:11

 ተጨማሪ ሐሳብ ማግኘት ትፈልጋለህ?መጸለይ ጥቅም አለው?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።