በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ምስሎች

ምስሎች

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አምልኮ ለማቅረብ ምስሎችን ይጠቀማሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለውን ልማድ ይደግፋል? አምላክንስ ያስደስተዋል?

በጥንት ዘመን የነበሩት ታማኝ አይሁዳውያን ምስሎችን ለአምልኮ ይጠቀሙ ነበር?

“በላይ በሰማይ ወይም በታች በምድር ካለው ወይም በውሃ ውስጥ ከሚኖሩት ነገሮች በማናቸውም ምስል ለራስህ ጣዖትን አታብጅ። አትስገድላቸው፤ አታምልካቸውም።”—ዘፀአት 20:4, 5

ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም በተለምዶ ብሉይ ኪዳን ተብለው በሚጠሩት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተወገዘ ድርጊት ነው

አንዳንዶች ምን ይላሉ?

ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደሚናገረው አይሁዳውያን ከአምልኳቸው ጋር የተያያዙ በርካታ ምስሎች የነበሯቸው ሲሆን “እነዚህን ምስሎች ያከብሯቸው፣ እንደ ቅዱስ ነገር አድርገው ይመለከቷቸው እንዲሁም ለአምልኮ ይጠቀሙባቸው ነበር።” ኢንሳይክሎፒዲያው ለዚህ እንደ ምሳሌ የጠቀሰው በኢየሩሳሌም የነበረውን ቤተ መቅደስ ያስጌጡ የነበሩትን የፍራፍሬ፣ የአበቦችና የእንስሳት ቅርጾች ነው።—1 ነገሥት 6:18፤ 7:36

ልታውቀው የሚገባህ ነገር፦

ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒድያ ከሚለው በተቃራኒ ታማኝ አይሁዳውያን በቤተ መቅደሱ የነበረን ማንኛውም ቅርጽ ወይም ምስል ለአምልኮ ተጠቅመው አያውቁም። እንዲያውም የትኛውም ታማኝ እስራኤላዊ ምስሎችን ለአምልኮ እንደተጠቀመ የሚገልጽ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አናገኝም።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

አምላክ “ክብሬን ለሌላ፣ ምስጋናዬንም ለጣዖት አልሰጥም” በማለት በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል ተናግሯል።—ኢሳይያስ 42:8

የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ምስሎችን ለአምልኮ ይጠቀሙ ነበር?

‘የአምላክ ቤተ መቅደስ ከጣዖታት ጋር ምን ስምምነት አለው? ስለዚህ ርኩስ የሆነውን ነገር መንካት አቁሙ።’—2 ቆሮንቶስ 6:16, 17

“የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ምስሎችን በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ስለ መጠቀም ማሰቡ ብቻ እንኳ ይዘገንናቸው ነበር፤ እንዲሁም ለምስሎች መስገድን ወይም ለእነሱ መጸለይን ከጣዖት አምልኮ ለይተው አይመለከቱትም ነበር።”—ሂስትሪ ኦቭ ዘ ክርስቺያን ቸርች

አንዳንዶች ምን ይላሉ?

ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ “በጥንት ክርስቲያኖች አምልኮ ውስጥ ምስሎችን የመጠቀም ልማድ እንደነበረ በአሁኑ ጊዜ በፍጹም አያጠያይቅም” ይላል። “ከመሬት በታች የተቆፈሩ የጥንት ክርስቲያኖች የመቃብር ቦታዎች (ካታኮምብ) እነዚህ ክርስቲያኖች ይጠቀሙባቸው የነበሩ ምስሎችን በትክክል የሚያሳዩ ናቸው። . . . በአፈ ታሪክ ብቻ የሚታወቁ ነገሮች ምስሎች እንኳ በእነዚህ ስፍራዎች በሚገኙ የአምልኮና የመቃብር ክፍሎች ውስጥ ይታያሉ።” *

ልታውቀው የሚገባህ ነገር፦

ካታኮምብ በሚባሉት ከመሬት በታች እንደ መተላለፊያ ሆነው በተሠሩ የመቃብር ቦታዎች ውስጥ ከተገኙት ምስሎች መካከል እጅግ ጥንታዊ የሚባለው እንኳ የተሠራው በሦስተኛው መቶ ዘመን ነው። ይህ ደግሞ ኢየሱስ ከሞተ ከ200 ዓመት በኋላ መሆኑ ነው። ስለዚህ ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ ‘የጥንት ክርስቲያኖች አምልኮ’ በማለት የጠራው ጥንታዊውን ክርስትና አይደለም፤ ጥንታዊው ክርስትና በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ይከተሉት የነበረው እንዲሁም በተለምዶ አዲስ ኪዳን ተብለው በሚጠሩት መጻሕፍት ውስጥ የተገለጸው ክርስትና ነው። በመቃብር ስፍራዎቹ ውስጥ እንደነዚህ ያሉት ምስሎች መገኘታቸው በሦስተኛው መቶ ዘመን የነበሩ የክርስትና ተከታዮች ነን የሚሉ ሰዎች ምናልባትም አረማውያንን ወደ ክርስትና ለመሳብ ብለው የእነሱን ልማድ በመከተል ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም እንደጀመሩ የሚጠቁም ነው። *

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

“ከጣዖት አምልኮ ሽሹ።”—1 ቆሮንቶስ 10:14

በምስሎች አማካኝነት አምልኮ ማቅረብ ተገቢ ነው?

“ራሳችሁን ከጣዖቶች ጠብቁ።”—1 ዮሐንስ 5:21

ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ የሌለው ሃይማኖታዊ ልማድ ነው። በዚህ ምክንያት የይሖዋ ምሥክሮች ምስሎችን ለአምልኮ አይጠቀሙም፤ እንዲሁም በቤታቸውም ሆነ በአምልኮ ቦታቸው ሃይማኖታዊ ምስሎች የሏቸውም

አንዳንዶች ምን ይላሉ?

ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል፦ “አንድን ምስል በመጠቀም የሚቀርበው አምልኮ የሚደርሰው ምስሉ ለሚወክለው አካል ነው፤ ስለዚህ ለዚህ አካል መቅረብ የሚገባውን አምልኮ አካሉ ለሚወከልበት ምስል መስጠት ይቻላል።”

ልታውቀው የሚገባህ ነገር፦

ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዴት መጸለይ እንዳለባቸው ባስተማራቸው ወቅት በምስሎች እንዲጠቀሙ አልነገራቸውም። እውነተኛውን አምላክ በምስል ተጠቅሞ ማምለክ ተገቢ እንደሆነ የሚያሳይ ሐሳብ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ አይገኝም።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

“ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ፤ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ።”—ማቴዎስ 4:10

^ አን.13 ምስሎች የሚለው ቃል በዚህ አገባቡ ሥዕሎችን፣ ሐውልቶችን፣ አርማዎችን እንዲሁም ሰዎች ለአምልኮ የሚጠቀሙባቸውን ነገሮች በሙሉ ያመለክታል።

^ አን.14 ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም ሕንድን፣ ግሪክንና ግብፅን ጨምሮ በብዙዎቹ የጥንት ባሕሎች ዘንድ የተለመደ ነው።