በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | እውነተኛ ስኬት ምንድን ነው?

እውነተኛ ስኬት ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?

እውነተኛ ስኬት ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ስኬት ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖረን ያበረታታናል። ስኬት ጥቂት ዕድለኛ ሰዎች ብቻ የሚያገኙት ነገር እንደሆነ አያስተምርም። በሌላ በኩል ደግሞ በተረት መጻሕፍት ላይ የሚንጸባረቀውን ‘ልብህ የሚልህን ከተከተልክ የምትፈልገውን ሁሉ ታገኛለህ’ የሚለውን ሐሳብ አይደግፍም። ልጆች ከሕፃንነታቸው ጀምሮ የሚነገራቸው ይህ ሐሳብ ብዙ ጊዜ እውን ስለማይሆን ውሎ አድሮ ለብስጭት ሊዳረጉ ይችላሉ።

እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ማንኛውም ሰው እውነተኛ ስኬት ሊያገኝ ይችላል፤ ይሁንና ጥረት ማድረግ አለበት። ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡትን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች እንመልከት፦

  • መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

    “ገንዘብን የሚወድ፣ ገንዘብ አይበቃውም፤ ብልጽግናም የሚወድ፣ በትርፉ አይረካም።”—መክብብ 5:10

    ይህ ምን ማለት ነው? ሀብትና ንብረትን በማካበት ላይ ያተኮረ ሕይወት እርካታ ለማግኘት ዋስትና አይሆንም። እንዲያውም ውጤቱ የተገላቢጦሽ ሊሆን ይችላል። ዶክተር ጂን ትዌንጂ የተባለች አንዲት ጸሐፊ ጀነሬሽን ሚ በተባለ መጽሐፏ ላይ እንዲህ ብላለች፦ “በሕይወታቸው ውስጥ ለገንዘብ ዋነኛ ቦታ የሚሰጡ ሰዎች ከሌሎች ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረትን ከፍ አድርገው ከሚመለከቱ ሰዎች ጋር ሲነጻጸሩ የበለጠ ጭንቀትና ውጥረት ይሰማቸዋል። . . . በርካታ ጥናቶች ገንዘብ ደስታ ሊያስገኝ እንደማይችል አረጋግጠዋል፤ መሠረታዊ ነገሮችን ለማግኘት የሚበቃ ገቢ እስካላችሁ ድረስ የገቢያችሁ መጠን በሚኖራችሁ እርካታ ላይ ያን ያህል ለውጥ አይኖረውም።”

    ምን ማድረግ ትችላለህ? ሀብትና ንብረት ከማካበት የተሻለ እርካታ የሚያስገኝ ግብ አውጣ። ኢየሱስ “አንድ ሰው ሀብታም ቢሆንም እንኳ ሕይወቱ በንብረቱ ላይ የተመካ ስላልሆነ ተጠንቀቁ፤ ከመጎምጀትም ሁሉ ተጠበቁ” ብሏል።—ሉቃስ 12:15

  • መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

    “ትዕቢት ጥፋትን፣ የእብሪት መንፈስም ውድቀትን ትቀድማለች።”—ምሳሌ 16:18

    ይህ ምን ማለት ነው? ከፍ ያለ ቦታ ለማግኘት መቋመጥ እውነተኛ ስኬት ለማግኘት አይረዳህም። እንዲያውም ጉድ ቱ ግሬት የተባለው መጽሐፍ ለረጅም ጊዜ ስኬታማ ስለሆኑ የድርጅት ኃላፊዎች ሲናገር “ትሑት፣ ልታይ ልታይ የማይሉ እንዲሁም የተለየ ትኩረት እንዲሰጣቸው የማይፈልጉ ናቸው” ብሏል። አክሎም “በአንጻሩ ደግሞ ጥሩ የድርጅት ኃላፊ ሆነው ካልተገኙት ሰዎች መካከል ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ራሳቸውን ከልክ በላይ ከፍ አድርገው ስለሚመለከቱ ለድርጅታቸው ውድቀት ወይም እድገት አለማግኘት ምክንያት ሆነዋል” ብሏል። ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ራስን ከፍ አድርጎ መመልከት ከስኬት ይልቅ ውድቀት ያስከትላል።

    ምን ማድረግ ትችላለህ? ለራስህ ክብርና ማዕረግ ከመፈለግ ይልቅ ትሕትናን አዳብር። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “አንድ ሰው ራሱን ከፍ አድርጎ የሚመለከትበት ምንም ነገር ሳይኖረው ራሱን ከፍ አድርጎ የሚመለከት ከሆነ ራሱን እያታለለ ነው።” ይህ ደግሞ ስኬት ሊባል አይችልም።—ገላትያ 6:3

  • መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

    “ሰው . . . ተግቶ በመሥራት እርካታ ከማግኘት የሚሻለው ነገር የለም።”—መክብብ 2:24 NW

    ይህ ምን ማለት ነው? ጥሩ የሥራ ባሕል ካዳበርክ ሥራህን ይበልጥ ትወደዋለህ። ዶክተር ማደሊን ለቫይን ቲች ዩር ችልድረን ዌል በተባለ መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “በአንድ ነገር ስኬት እንዳገኘን የሚሰማን ያንን ነገር ጥሩ አድርገን ማከናወን ስንችል ነው፤ አንድን ነገር ጥሩ አድርጎ የመሥራት ችሎታ የሚገኘው ደግሞ በጥረትና ተስፋ ባለመቁረጥ ነው።” ይህ ደግሞ አልፎ አልፎ ባይሳካልህም እንኳ ሁኔታውን ተቋቁመህ ማለፍን ይጠይቃል።

    ምን ማድረግ ትችላለህ? በሥራህ የተዋጣልህ እንድትሆን በርትተህ ሥራ፤ እንዲሁም እንቅፋት ሲያጋጥምህ ተስፋ አትቁረጥ። ልጆች ካሉህ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በራሳቸው እንዲወጡ (ዕድሜያቸውንና አቅማቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት) አጋጣሚ ስጣቸው። የሚያጋጥማቸውን ችግር በሙሉ ጣልቃ ገብተህ ለመፍታት አትቸኩል። ልጆች በሕይወታቸው እውነተኛ እርካታ የሚኖራቸው እንዲሁም አዋቂ ሲሆኑ የሚጠቅማቸውን ሥልጠና የሚያገኙት ችግሮችን ተቋቁሞ የማለፍ ችሎታ ካዳበሩ ነው።

  • መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

    “በሕይወት ያለ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላል።”—መክብብ 9:4

    ይህ ምን ማለት ነው? ራስህን ለማስተዳደር የምትሠራው ሥራ የሕይወትህ አንድ ክፍል እንጂ መላው ሕይወትህ መሆን የለበትም። እውነቱን ለመናገር፣ ጤንነትህን ወይም የቤተሰብህን አክብሮት አጥተህ በሥራህ ትልቅ ደረጃ ላይ ብትደርስ ስኬታማ እንደሆንክ ሊሰማህ ይችላል? ለሥራቸው፣ ለጤንነታቸውና ለቤተሰብ ሕይወታቸው ተገቢውን ቦታ የሚሰጡ ሰዎች እውነተኛ ስኬት ያገኛሉ።

    ምን ማድረግ ትችላለህ? ራስህን ተንከባከብ። በቂ እረፍት አድርግ። ጤንነትን፣ ቤተሰብንና ወዳጆችን ሠውቶ ሙሉ በሙሉ በሥራ በመጠመድ የሚገኘው ጥቅም ከንቱ ነው፤ ምክንያቱም ይህ እውነተኛ ያልሆነ ስኬት ነው።

  • መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

    “በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ ደስተኞች ናቸው።”—ማቴዎስ 5:3

    ይህ ምን ማለት ነው? መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በውስጡ የሚገኙትን መመሪያዎች ሥራ ላይ ማዋል ለእውነተኛ ስኬት አስፈላጊ ነው። እንዲያውም በሚሊዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ መስጠታቸው ስለ ቁሳዊ ነገሮች ብዙ እንዳይጨነቁ እንደረዳቸው ተገንዝበዋል።—ማቴዎስ 6:31-33

    ምን ማድረግ ትችላለህ? መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ ስኬት ለማግኘት ሊረዳህ የሚችለው እንዴት እንደሆነ ተማር። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ከፈለግህ በአካባቢህ ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች ማናገር ወይም www.ps8318.com የተባለውን ድረ ገጽ መመልከት ትችላለህ።