በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቤተሰብ | ወጣቶች

ቁጣን መቆጣጠር የሚቻልበት መንገድ

ቁጣን መቆጣጠር የሚቻልበት መንገድ

ተፈታታኙ ነገር

“በእህቴ ላይ በመጮኽ በሩን በኃይል ስወረውረው እጀታው ግድግዳው ውስጥ ተቀረቀረ። ግድግዳው ላይ ያለውን ቀዳዳ ባየሁት ቁጥር ያን ዕለት ምን ያህል የሕፃን ሥራ እንደሠራሁ ይታወሰኛል።”—ዲያን *

“‘ክፉ አባት ነህ!’ ብዬ ጮኽኩኝና በሩን በኃይል ዘጋሁት። በሩ ከመዘጋቱ በፊት ግን አባቴ በሁኔታው እንዳዘነ ከፊቱ ላይ ስመለከት፣ ምነው ወደኋላ መመለስና የተናገርኩትን መዋጥ ብችል ብዬ ተመኘሁ።”—ሎረን

አንተስ እንደ ሎረን እና እንደ ዲያን ተሰምቶህ ያውቃል? ከሆነ ይህ ርዕስ ሊረዳህ ይችላል።

ማወቅ የሚኖርብህ ነገር

በቁጣ መገንፈል ስምህን ያጠፋዋል። “የቁጡነት ባሕርዬን ሌሎች ሊቀበሉት ይገባል የሚል አስተሳሰብ ነበረኝ” በማለት የ21 ዓመቷ ብሪያና ተናግራለች። “ሰዎች ራሳቸውን መቆጣጠር ሲያቅታቸው እንደ ሞኝ እንደሚታዩ ማስተዋል ስጀምር ግን፣ ለካ እኔም በሌሎች ዘንድ የምታየው እንዲሁ ነው ብዬ አሰብኩ!”

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ግልፍተኛ ሰው የቂል ተግባር ይፈጽማል።”—ምሳሌ 14:17

ሰዎች እሳተ ገሞራ ሲፈነዳ ከአካባቢው እንደሚሸሹ ሁሉ በቁጣ ከሚገነፍሉ ሰዎችም ይርቃሉ

ቁጡ መሆንህ ሰዎች እንዲርቁህ ሊያደርግ ይችላል። የ18 ዓመቱ ዳንኤል፣ “በቁጣ መገንፈልህ ሌሎች ለአንተ ያላቸው ጥሩ ግምትም ሆነ አክብሮት እንዲቀንስ ያደርጋል” ብሏል። የ18 ዓመቷ ኢሌይንም በዚህ ትስማማለች። እንዲህ ብላለች፦ “በቁጣ መገንፈል ደስ አይልም። ትርፉ ሰዎች እንዲፈሩህ ማድረግ ነው።”

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ከግልፍተኛ ጋር ወዳጅ አትሁን፤ በቀላሉ ቱግ ከሚልም ሰው ጋር አትወዳጅ።”—ምሳሌ 22:24

ማሻሻል ትችላለህ። የ15 ዓመቷ ሣራ እንዲህ ብላለች፦ “ሁኔታዎች በአንተ ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድሩ መከላከል አትችል ይሆናል፤ ስሜትህን የምትገልጽበትን መንገድ ግን መቆጣጠር ትችላለህ። ግዴታ በቁጣ መገንፈል የለብህም።”

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ታጋሽ ሰው ከጦረኛ፣ ስሜቱን የሚገዛም ከተማን በጕልበቱ ከሚይዝ ይበልጣል።”—ምሳሌ 16:32

ምን ማድረግ ትችላለህ?

ግብ አውጣ። “በቃ እኔ እንዲህ ነኝ” ከማለት ይልቅ ጊዜ ወስነህ ምናልባትም በስድስት ወራት ውስጥ ባሕሪህን ለማሻሻል ጥረት አድርግ። በዚህ ጊዜ ውስጥ የምታደርገውን መሻሻል መዝግብ። ስሜትህን መቆጣጠር ባቃተህ ቁጥር (1) ያጋጠመህን ነገር፣ (2) ምላሽ የሰጠህበትን መንገድ እንዲሁም (3) የተሻለ የሚሆነው ምን ብታደርግ እንደነበረና እንዲህ ያልክበትን ምክንያት በጽሑፍ አስፍር። ከዚያም ሌላ ጊዜ የሚያናድድ ነገር ሲገጥምህ የተሻለ ነበር ያልከውን ምላሽ ለመጠቀም ግብ አውጣ። በተጨማሪም እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ስኬት ስታገኝም መዝግብ! ራስህን በመግዛትህ ምን ጥሩ ስሜት እንደተሰማህ ጻፍ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ቆላስይስ 3:8

ምላሽ ለመስጠት አትቸኩል። አንድ ሰው ወይም አንድ ነገር ሲያናድድህ መጀመሪያ ወደ አፍህ የመጣውን ነገር አትናገር። ከዚህ ይልቅ ታገሥ። አስፈላጊ ከሆነ በረጅሙ ተንፍስ። የ15 ዓመቱ ኤሪክ “በረጅሙ መተንፈሴ በኋላ ላይ ሊጸጽተኝ የሚችል ነገር ከማድረጌ ወይም ከመናገሬ በፊት ለማሰብ ጊዜ ይሰጠኛል” ብሏል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ምሳሌ 21:23

ነገሮችን ሰፋ አድርገህ ተመልከት። አንዳንድ ጊዜ የምትናደደው ጉዳዩን ከአንድ ወገን ብቻ በማየትህ ማለትም አንተ ላይ ተጽዕኖ ባደረገው ሁኔታ ላይ ብቻ በማተኮርህ ሊሆን ይችላል። የጉዳዩን ሌላ ገጽታ ጭምር ለማየት ጣር። ጀሲካ የተባለች ወጣት “ሰዎች በግልጽ ሥርዓት የጎደለው ነገር ቢያደርጉም አብዛኛውን ጊዜ ችግራቸውን በመጠኑም ቢሆን እንድረዳላቸው የሚያስችል ምክንያት አገኛለሁ” ብላለች።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ምሳሌ 19:11

አስፈላጊ ከሆነ ትተህ ሂድ። መጽሐፍ ቅዱስ “ጠብ ከመጫሩ በፊት ከነገር ራቅ” ይላል። (ምሳሌ 17:14) ከጥቅሱ መረዳት እንደምንችለው ለቁጣ የሚጋብዝ ሁኔታ ሲያጋጥም አንዳንድ ጊዜ ከሁሉ የተሻለው መፍትሔ ከአካባቢው መራቅ ነው። ከዚያም በጉዳዩ ላይ በማብሰልሰል ንዴትህ እንዲባባስ ከመፍቀድ ይልቅ በሥራ ተጠመድ። “የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረጌ ውጥረቴን ቀለል የሚያደርግልኝ ከመሆኑም ሌላ ስሜቴን እንድቆጣጠር ይረዳኛል” በማለት ዳንየል የምትባል አንዲት ወጣት ተናግራለች።

ችለህ ማሳለፍን ተማር። መጽሐፍ ቅዱስ “ተቆጡ፤ ሆኖም ኃጢአት አትሥሩ። የምትናገሩትን . . . በልባችሁ ተናገሩ፤ ጸጥም በሉ” ይላል። (መዝሙር 4:4 NW) የቁጣ ስሜት የተሰማህ መሆኑ በራሱ ምንም ስህተት የለበትም። ጥያቄው ‘ከዚያ በኋላ ምን ታደርጋለህ?’ የሚለው ነው። “ሌሎች የሚያደርጉት ነገር በቁጣ እንድትገነፍል የሚያደርግህ ከሆነ ያበሳጩህ ሰዎች አንተን እንዲቆጣጠሩህ እየፈቀድህ ነው” በማለት ሪቻርድ የሚባል አንድ ወጣት ተናግሯል። “ታዲያ እንደበሰለ ሰው በማሰብ ጉዳዩን ችላ ብለህ ለማለፍ ለምን አትሞክርም?” እንዲህ ካደረግክ ቁጣው አንተን እንዲቆጣጠርህ ከመፍቀድ ይልቅ ቁጣህን ትቆጣጠረዋለህ።

^ አን.4 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።