በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አገሮችና ሕዝቦች

ኮስታ ሪካን እንጎብኝ

ኮስታ ሪካን እንጎብኝ

ከአምስት መቶ ዓመታት በፊት ወደዚህ አካባቢ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጡት ስፔናውያን ናቸው። ስፔናውያን ብዙ ወርቅ እንደሚያገኙ በማሰብ ይህን አካባቢ ኮስታ ሪካ (ባለጸጋ የባሕር ዳርቻ) ብለው ሰየሙት፤ ሆኖም ፍለጋው ‘ላም አለኝ በሰማይ’ ሆኖባቸዋል። ይህ አገር በዛሬው ጊዜ የሚታወቀው በከበሩ ማዕድናት ሳይሆን በዓለማችን ላይ ካሉ እጅግ የበለጸገ ብዝሃ ሕይወት ካላቸው አገራት አንዱ በመሆኑ ነው።

ኮስታ ሪካውያን ቲኮዎች በመባል ይታወቃሉ፤ ይህ አጠራር የመጣው ኮስታ ሪካውያን አንድን ነገር በጣም ማሳነስ ሲፈልጉ በቃላት መጨረሻ ላይ ኢኮ የሚል ቅጥያ የመጨመር ልማድ ስላላቸው ነው። ለምሳሌ ያህል፣ “ኡን ሞሜንቶ” (አንዴ ቆየኝ) በማለት ፈንታ “ኡን ሞሜንቲኮ” (አንዴ ትንሽ ቆየኝ) ይላሉ። በዕለታዊ ንግግራቸው ውስጥ አድናቆታቸውን ወይም ስምምነታቸውን ሲገልጹ አሊያም ሲገናኙና ሲሰነባበቱ ብዙውን ጊዜ “ፑራ ቪዳ!” (ንጹሕ ሕይወት!) ይላሉ።

የኮስታ ሪካ ደኖች የተለያዩ አስገራሚ ዕፀዋትና እንስሳት አሏቸው፤ ከእነዚህ መካከል ይህ ባለቀይ ዓይኑ የዛፍ እንቁራሪት (አጋሊቺንስ ካሊድርያስ) ይገኝበታል

ከኮስታ ሪካ ተወዳጅ ምግቦች አንዱ ጋሎ ፒንቶ (ቃል በቃል “ገብስማ አውራ ዶሮ” ማለት ነው) ይባላል፤ ይህ ምግብ የሚዘጋጀው መጀመሪያ ሩዝና ቦሎቄ ለየብቻ ከተቀቀሉ በኋላ ከተለያዩ ማጣፈጫዎች ጋር አብረው እንዲበስሉ በማድረግ ነው። ጋሎ ፒንቶ ቁርስ፣ ምሳ ወይም ራት ላይ ሊቀርብ ይችላል። ባሕላዊው መጠጥ ደግሞ ካፌ ኮሪያዶ የሚባል ሲሆን ብዙውን ጊዜ ከእንጨት በተሠራ ዕቃ ላይ በተንጠለጠለ የጨርቅ ከረጢት ውስጥ የቡና ዱቄት ከተጨመረ በኋላ የፈላ ውኃ በማፍሰስ የሚዘጋጅ ነው።

ኮስታ ሪካ ውስጥ 450 የሚያህሉ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች አሉ። ስብሰባዎቻቸው የሚካሄዱት የኮስታ ሪካን ምልክት ቋንቋ እንዲሁም ብሪብሪ እና ካቤካር የሚባሉትን አገር በቀል ቋንቋዎች ጨምሮ በአሥር ቋንቋዎች ነው።

ይህን ታውቅ ነበር? ኮስታ ሪካ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ልቅም ተደርገው የተጠረቡ ድቡልቡል ድንጋዮች ተገኝተዋል። ከእነዚህ ትልቁ ዳያሜትሩ 2.4 ሜትር ነው። አንዳንዶቹ ከ1,400 ዓመታት በላይ ዕድሜ እንዳላቸው ይገመታል። ድቡልቡል ድንጋዮቹ ለምን ዓላማ እንደተሠሩ በእርግጠኝነት አይታወቅም።

ድቡልቡል ድንጋዮች