በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥሩ ሃይማኖት ሰዎች እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ ያስተምራል

ጥሩ ሃይማኖት ሰዎች እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ ያስተምራል

መጽሐፍ ቅዱስ “ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፣ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና” በማለት ይናገራል። (1 ዮሐንስ 4:8 የ1954 ትርጉም) በመሆኑም ጥሩ ሃይማኖት ሰዎች እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ ማስተማር ይኖርበታል።

ብዙ ሃይማኖቶች የታመሙ ሰዎችን፣ አረጋውያንንና ድሆችን በመንከባከብ የሚያስመሰግን ሥራ ያከናውናሉ። ሐዋርያው ዮሐንስ እንደሚከተለው በማለት የጻፈውን ምክር እንዲሠሩበት አባሎቻቸውን ያበረታታሉ፦ “ማንም ሀብት እያለው፣ ወንድሙ ሲቸገር አይቶ ባይራራለት፣ የእግዚአብሔር ፍቅር እንዴት በእርሱ ይኖራል? ልጆች ሆይ፤ በተግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ።”—1 ዮሐንስ 3:17, 18 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

ይሁንና በሁለት አገሮች መካከል ጦርነት በሚነሳበት ጊዜ እነዚህ ሃይማኖቶች ምን አቋም ይይዛሉ? “ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለውን የአምላክ ትእዛዝ መጠበቅ ያለብን በሰላሙ ጊዜ ብቻ ነው? ወይስ አንድ የፖለቲካ መሪ ወይም ንጉሥ ከጎረቤት አገር ጋር እንድንዋጋ በሚያዘን ጊዜም ጭምር?—ማቴዎስ 22:39 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።” (ዮሐንስ 13:35 የ1954 ትርጉም) ከዚህ በታች ለቀረቡት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት በምትሞክርበት ጊዜ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘እኔ የማውቀው ሃይማኖት አባላት፣ በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም ጭምር ለሁሉም ዓይነት ሰዎች በማንኛውም ጊዜ ፍቅር ያሳያሉ?’

ርዕሰ ጉዳይ፦ ጦርነት።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል? ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ የሚረግሙአችሁን መርቁ፤ ለሚጠሉአችሁ በጎ አድርጉ” በማለት አዟቸዋል።—ማቴዎስ 5:44 የታረመው የ1980 ትርጉም

ወታደሮች ኢየሱስን ለመያዝ በመጡ ጊዜ ሐዋርያው ጴጥሮስ እሱን ለማስጣል ሲል ሰይፉን መዝዞ ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “በል ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ፤ ሰይፍን የሚመዝዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” አለው።—ማቴዎስ 26:52 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

ሐዋርያው ዮሐንስ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል፦ “የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች ተለይተው የሚታወቁት በዚህ ነው፦ ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ አይደለም። ከመጀመሪያ የሰማችሁት መልእክት ‘እርስ በርሳችን እንፋቀር’ የሚል ነው። የሰይጣን ወገን እንደነበረውና ወንድሙን እንደገደለው እንደ ቃየል መሆን አይገባንም።”—1 ዮሐንስ 3:10-12 የታረመው 1980 ትርጉም

ጥያቄ፦ አንተ የምታውቀው ሃይማኖት አባላቱ በጦርነት እንዲካፈሉ ያበረታታል?

ርዕሰ ጉዳይ፦ ፖለቲካ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል? አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስ ተአምር የመፈጸም ችሎታ እንዳለው ከተመለከቱ በኋላ በፖለቲካ ውስጥ እንዲገባ ለማድረግ ፈልገው ነበር። ኢየሱስ በዚህ ጊዜ ምን አደረገ? “ኢየሱስም ሰዎቹ መጥተው በግድ ሊያነግሡት እንዳሰቡ ዐውቆ እንደ ገና ብቻውን ወደ ተራራ ገለል አለ።”—ዮሐንስ 6:15 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

ኢየሱስ በመንግሥት ላይ እንዲያምጹ ሰዎችን አነሳስቷል ተብሎ በሐሰት በተወነጀለ ጊዜ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለም፤ ቢሆንማ ኖሮ አይሁድ እንዳይዙኝ ሎሌዎቼ በተከላከሉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለም።”—ዮሐንስ 18:36 የ1954 ትርጉም

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን አስመልክቶ ወደ አምላክ በጸለየ ጊዜ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “እኔ ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ እነርሱም ከዓለም አይደሉም፤ ስለዚህ ዓለም ጠላቸው።”—ዮሐንስ 17:14 የታረመው የ1980 ትርጉም

ጥያቄ፦ አንተ የምታውቀው ሃይማኖት አባላት በፖለቲካ ውስጥ አለመግባታቸው በአንዳንድ ፖለቲከኞች እንዲጠሉ እንደሚያደርጋቸው ቢያወቁም ከፖለቲካ ገለልተኛ በመሆን የኢየሱስን ምሳሌ ይከተላሉ?

ርዕሰ ጉዳይ፦ ጭፍን ጥላቻ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል? አይሁዳዊ ያልሆኑ ያልተገረዙ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ክርስቲያን በሆኑበት ወቅት ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ተናግሮ ነበር፦ “እግዚአብሔር ለማንም እንደማያዳላ በእርግጥ ተረድቻለሁ፤ ነገር ግን እርሱን የሚፈሩትንና ጽድቅን የሚያደርጉትን ሁሉ ከየትኛውም ወገን ቢሆኑ ይቀበላቸዋል።”—የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

ያዕቆብ ለመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ወንድሞቼ ሆይ፣ በክብር ጌታ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን እምነት ለሰው ፊት በማድላት አትያዙ። የወርቅ ቀለበት ያደረገና የጌጥ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ጉባኤአችሁ ቢገባ፣ እድፍ ልብስም የለበሰ ድሀ ሰው ደግሞ ቢገባ፣ የጌጥ ልብስም የለበሰውን ተመልክታችሁ፦ አንተስ በዚህ በመልካም ስፍራ ተቀመጥ ብትሉት፣ ድሀውንም፦ አንተስ ወደዚያ ቁም ወይም ከእግሬ መረገጫ በታች ተቀመጥ ብትሉት፣ ራሳችሁን መለያየታችሁ አይደለምን? ክፉ አሳብ ያላቸውም ዳኞች መሆናችሁ አይደለምን?”—ያዕቆብ 2:1-4 የ1954 ትርጉም

ጥያቄ፦ አንተ የምታውቀው ሃይማኖት ሰዎች ሁሉ በአምላክ ዓይን እኩል እንደሆኑና አባላቱ ዘር ወይም ሀብት ተመልክተው ለማንም እንዳያዳሉ ያስተምራል?

አባላቱ በፖለቲካ፣ በዘር እንዲሁም በሀብት እንዳይከፋፈሉ የሚያስተምረው የትኛው ሃይማኖት ነው?