በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መንፈሳዊ ፍጥረታት ሊጠቅሙን ወይም ሊጎዱን ስለሚችሉበት መንገድ

መንፈሳዊ ፍጥረታት ሊጠቅሙን ወይም ሊጎዱን ስለሚችሉበት መንገድ

ከኢየሱስ ምን እንማራለን?

መንፈሳዊ ፍጥረታት ሊጠቅሙን ወይም ሊጎዱን ስለሚችሉበት መንገድ

ኢየሱስ “ዓለም ከመመሥረቱ በፊት” ከአባቱ ጋር በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ይኖር ነበር። (ዮሐንስ 17:5) በመሆኑም ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ሊሰጠን ይችላል።

መላእክት ስለ እኛ ያስባሉ?

ኢየሱስ ከተናገረው ሐሳብ መገንዘብ እንደምንችለው መላእክት የእኛ ጉዳይ በጥልቅ ያሳስባቸዋል። ኢየሱስ “ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በአምላክ መላእክት ዘንድ ደስታ ይሆናል” ብሏል።—ሉቃስ 15:10

ኢየሱስ፣ የአምላክ አገልጋዮች ከአምላክ ጋር ያላቸውን ዝምድና እንዲጠብቁ የመርዳት ኃላፊነት ለመላእክት እንደተሰጠ ጠቁሟል። በመሆኑም ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ሌሎችን እንዳያሰናክሉ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ “በሰማይ ያሉት መልአኮቻቸው ዘወትር በሰማይ ያለውን የአባቴን ፊት ስለሚያዩ ከእነዚህ ከታናናሾቹ መካከል አንዱንም እንዳትንቁ ተጠንቀቁ” ብሏል። (ማቴዎስ 18:10) ኢየሱስ ይህን ሲናገር እያንዳንዱ የእሱ ተከታይ ጠባቂ መልአክ ይኖረዋል ማለቱ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ከአምላክ ጋር የሚሠሩ መላእክት ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ትኩረት እንደሚሰጡ መግለጹ ነበር።

ዲያብሎስ ሊጎዳን የሚችለው እንዴት ነው?

ኢየሱስ፣ ሰዎች ስለ አምላክ ትክክለኛውን ነገር እንዳያውቁ ሰይጣን ጥረት እንደሚያደርግ ተከታዮቹን አስጠንቅቋቸዋል። “አንድ ሰው የመንግሥቱን ቃል ሰምቶ የማያስተውል ከሆነ ክፉው መጥቶ በልቡ ውስጥ የተዘራውን ዘር ይነጥቀዋል” ብሏል።—ማቴዎስ 13:19

ኢየሱስ በእርሻው ላይ የስንዴ ዘር ስለዘራው ሰው የሚገልጸውን ምሳሌ በተናገረ ጊዜ ሰይጣን ሰዎችን የሚያታልልበትን አንዱን መንገድ ጠቁሟል። ዘሪው ኢየሱስን የሚወክል ሲሆን ስንዴው ደግሞ ከኢየሱስ ጋር በሰማይ የሚገዙትን እውነተኛ ክርስቲያኖች ያመለክታል። ይሁንና ጠላት መጥቶ “በስንዴው ላይ እንክርዳድ ዘርቶ” እንደሄደ ኢየሱስ ተናግሯል። እንክርዳዱ ሐሰተኛ ክርስቲያኖችን ያመለክታል። “እንክርዳዱን የዘራው ጠላት፣ ዲያብሎስ ነው።” (ማቴዎስ 13:25, 39) እንክርዳድ ከስንዴ ቡቃያ ጋር ሊመሳሰል እንደሚችል ሁሉ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎችም እውነተኛ ክርስቲያኖች መስለው ይታዩ ይሆናል። የሐሰት ትምህርቶችን የሚያስተምሩ ሃይማኖቶች በትምህርታቸው ሰዎችን ስለሚያስቱ አምላክን እንዳይታዘዙ ያደርጓቸዋል። ሰይጣን፣ ሰዎች ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት እንዳይመሠርቱ ለማድረግ በሐሰት ሃይማኖት ይጠቀማል።

ሰይጣን እንዳይጎዳን ምን ማድረግ እንችላለን?

ኢየሱስ ሰይጣንን “የዚህ ዓለም ገዥ” ብሎ ጠርቶታል። (ዮሐንስ 14:30) ኢየሱስ፣ ከሰይጣን ጥቃት ጥበቃ ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ወደ አምላክ ባቀረበው ጸሎት ላይ ገልጿል። ደቀ መዛሙርቱን አስመልክቶ በሰማይ ለሚገኘው አባቱ እንዲህ ብሎ ጸልዮአል፦ “የምለምንህ . . . ከክፉው የተነሳ እንድትጠብቃቸው ነው። እኔ የዓለም ክፍል እንዳልሆንኩ ሁሉ እነሱም የዓለም ክፍል አይደሉም። በእውነት ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው።” (ዮሐንስ 17:15-17) ከአምላክ ቃል የሚገኘው እውቀት፣ ሰይጣን የሚገዛው የሰው ዘር ዓለም ከሚያሳድርብን ተጽዕኖ ሊጠብቀን ይችላል።

መላእክት በዛሬው ጊዜ ሊጠቅሙን የሚችሉት እንዴት ነው?

ኢየሱስ “በዚህ ሥርዓት መደምደሚያ . . . መላእክት ሄደው ክፉዎችን ከጻድቃን ይለያሉ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 13:49) በአሁኑ ጊዜ የምንኖረው ‘በዚህ ሥርዓት መደምደሚያ’ ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለአምላክ መንግሥት ምሥራች በጎ ምላሽ እየሰጡ ነው።—ማቴዎስ 24:3, 14

ይሁን እንጂ የአምላክን ቃል ማጥናት የጀመረ ሁሉ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል ማለት አይደለም። መላእክት የይሖዋ አገልጋዮች የሚያከናውኑትን ሥራ የሚመሩ ሲሆን ለአምላክ እውነተኛ ፍቅር ያላቸው ሰዎች የተማሩትን ነገር በሥራ ላይ ለማዋል ከማይፈልጉ ሰዎች ተለይተዋል። ኢየሱስ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ ሰዎችን አስመልክቶ “ቃሉን በመልካምና በጥሩ ልብ ሰምተው በውስጣቸው በማኖር በጽናት ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው” በማለት ተናግሯል።—ሉቃስ 8:15

ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ምዕራፍ 10 ተመልከት።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መላእክት እውነትን የሚፈልጉ ቅን ልቦና ያላቸው ሰዎችን በመርዳቱ ሥራ ድርሻ አላቸው