በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዘመናዊቷ የእስራኤል መንግሥት ትንቢት ይናገራል?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዘመናዊቷ የእስራኤል መንግሥት ትንቢት ይናገራል?

በዛሬው ጊዜ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ሁኔታ ዓለምን ስጋት ላይ ጥሎታል። የሮኬት ድብደባ፣ በታጠቁ ኃይሎች መካከል የሚነሱ ግጭቶችና አሸባሪዎች የሚያደርሱት የቦምብ ፍንዳታ በዚህ አካባቢ የተለመዱ ነገሮች ናቸው። በዚህ ላይ ደግሞ የኑክሌር መሣሪያ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችልበት አጋጣሚ አለ። የመካከለኛው ምሥራቅ ሁኔታ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎችን የሚያሳስብ መሆኑ ምንም አያስደንቅም!

በ1948 በግንቦት ወርም ዓለም የመካከለኛውን ምሥራቅ ሁኔታ በጭንቀት ይከታተል ነበር። በዚያን ጊዜ ይኸውም የዛሬ 62 ዓመት፣ ብሪታንያ በወቅቱ ፓለስቲና የሚባለውን አካባቢ በሞግዚትነት የምታስተዳድርበት ጊዜ እያበቃ የነበረ ሲሆን የጦርነት ዳመና እያንዣበበ ነበር። ይህ ከመሆኑ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ብሪታንያ ከምታስተዳድረው ከዚህ አካባቢ ከፊሉ ለአይሁዳውያን እንዲሰጥና ነፃ የአይሁድ መንግሥት እንዲቋቋም ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር። በአካባቢው የነበሩት የዓረብ አገራት ግን ይህን ዕቅድ ለማክሸፍ ማንኛውንም መሥዋዕትነት ከመክፈል እንደማይመለሱ ዛቱ። እንዲያውም የዓረብ ሊግ፣ አዲስ በተቋቋመው የእስራኤል መንግሥትና በዓረብ አገራት መካከል ያለው “ድንበር የጦርነት አውድማ” እንደሚሆን አስጠነቀቀ።

ዕለቱ ዓርብ፣ ግንቦት 14, 1948 ሲሆን ከቀኑ 10:00 ነበር። የብሪታንያ ሞግዚትነት ሊያከትም የቀሩት ጥቂት ሰዓታት ብቻ ናቸው። በሚስጥር የተደረገላቸውን ጥሪ አክብረው በቴል አቪቭ ሙዚየም ውስጥ የተገኙት 350 ሰዎች ዘመናዊቷ የእስራኤል መንግሥት መቋቋሟን በይፋ የሚያበስረውን ማስታወቂያ ለመስማት በጉጉት እየተጠባበቁ ነው። አዲስ የሚመሠረተው መንግሥት በርካታ ጠላቶች፣ ሂደቱን እንዳያደናቅፉት ሲባል በአካባቢው ከፍተኛ ጥበቃ እየተደረገ ነው።

ዴቪድ ቤን-ጉሪዮን፣ ግንቦት 14, 1948

የእስራኤል ብሔራዊ ምክር ቤት መሪ የሆኑት ዴቪድ ቤን-ጉሪዮን፣ የእስራኤል መንግሥት ምሥረታ አዋጅ የተባለውን መግለጫ አነበቡ። መግለጫው በከፊል እንዲህ ይላል፦ “እኛ የኢረጽ-እስራኤል የአይሁድ ማኅበረሰብ ተወካዮች የሆንን የአገሪቱ ምክር ቤት አባላት . . . ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መብታችንን እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ያስተላለፈውን ውሳኔ መሠረት በማድረግ በኢረጽ-እስራኤል የአይሁዳውያን አገር መቋቋሙን አውጀናል፤ ይህች አገር የእስራኤል መንግሥት ተብላ ትጠራለች።”

የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ ነው?

አንዳንድ የኢቫንጀሊካን ፕሮቴስታንቶች፣ የዘመናዊቷ የእስራኤል መንግሥት መቋቋም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ እንደሆነ ያምናሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ጆን ሄጊ የተባሉ አንድ ቄስ ጀሩሳሌም ካውንትዳውን በተሰኘው መጽሐፍ ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “ነቢዩ ኢሳይያስ ‘አገር በአንድ ጀምበር ይፈጠራል’ በማለት ይህን ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን ክንውን አስመልክቶ ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ኢሳይያስ 66:8⁠ን ተመልከት።) . . . ይህ በሃያኛው መቶ ዘመን ከተፈጸሙት ትንቢቶች ሁሉ የላቀው ነው። ይህ ሁኔታ የእስራኤል አምላክ አሁንም እንዳለ ለሁሉም ሰው የሚያረጋግጥ ሕያው ማስረጃ ነው።”

ይህ አባባል ትክክል ነው? ኢሳይያስ 66:8 ስለ ዘመናዊቷ የእስራኤል መንግሥት መቋቋም የሚገልጽ ትንቢት ነው? በእርግጥ ግንቦት 14, 1948 “በሃያኛው መቶ ዘመን ከተፈጸሙት ትንቢቶች ሁሉ የላቀው” ትንቢት የተፈጸመበት ወቅት ነው? ዘመናዊቷ የእስራኤል መንግሥት አምላክ የመረጠው ብሔር ከሆነች እንዲሁም አምላክ በዚህ ብሔር ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እንዲፈጸሙ የሚያደርግ ከሆነ በእርግጥም ይህ በየትኛውም ቦታ የሚኖሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ነው።

የኢሳይያስ ትንቢት እንዲህ ይላል፦ “እንዲህ ያለ ነገር ማን ሰምቶ ያውቃል? እንዲህ ያለ ነገርስ ማን አይቶ ያውቃል? አገር በአንድ ጀምበር ይፈጠራልን? ወይስ ሕዝብ በቅጽበት ይገኛል? ጽዮንን ምጥ ገና ሲጀምራት፣ ልጆቿን ወዲያውኑ ትወልዳለች።” (ኢሳይያስ 66:8) ይህ ጥቅስ አንድ አገር በአንድ ቀን የተወለደ ያህል በድንገት እንደሚፈጠር በግልጽ ይናገራል። ይህ እንዲሆን የሚያደርገው ማን ነው? ቀጣዩ ቁጥር እንዲህ የሚል ፍንጭ ይሰጠናል፦ “‘ሊወለድ የተቃረበውን፣ እንዳይወለድ አደርጋለሁን?’ ይላል እግዚአብሔር። ‘በሚገላገሉበት ጊዜስ፣ ማሕፀን እዘጋለሁን?’ ይላል አምላክሽ።” ይሖዋ አምላክ ይህ ብሔር ተአምራዊ በሆነ መንገድ እንዲወለድ የሚያደርገው እሱ እንደሆነ በግልጽ ተናግሯል።

ዘመናዊቷ የእስራኤል መንግሥት የምትተዳደረው፣ ሃይማኖት መንግሥታዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ መግባቱን በማይቀበል ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ሲሆን ይህ መንግሥት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጠቀሰው አምላክ ላይ እንደሚታመን ገልጾ አያውቅም። እስራኤላውያን በ1948 መንግሥታቸውን እንዲያቋቁሙ ያስቻላቸው ይሖዋ አምላክ እንደሆነ ተናግረው ነበር? በፍጹም። የእስራኤልን መንግሥት መቋቋም በሚያበስረው አዋጅ የመጀመሪያ ሰነድ ላይ የአምላክ ስም ሌላው ቀርቶ “አምላክ” የሚለው ቃል እንኳ ፈጽሞ አልተጠቀሰም። ግሬት ሞመንትስ ኢን ጁዊሽ ሂስትሪ የተባለው መጽሐፍ የዚህን አዋጅ የመጨረሻ ቅጂ አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “የብሔራዊ ምክር ቤቱ አባላት ከቀኑ 7:00 ላይ በተገናኙበት ጊዜም እንኳ የመንግሥቱን መቋቋም በሚገልጸው አዋጅ ላይ የሚካተተውን ሐሳብ በተመለከተ ስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም ነበር። . . . ሃይማኖተኛ የሆኑት አይሁዳውያን ‘የእስራኤል አምላክ’ የሚል ሐረግ አዋጁ ውስጥ እንዲካተት ፈልገው ነበር። ሃይማኖት መንግሥታዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ መግባት እንደሌለበት የሚሰማቸው ወገኖች ደግሞ ይህን ሐሳብ ተቃወሙት። ቤን-ጉሪዮን ሁለቱን ወገኖች ለማስታረቅ ሲሉ ‘አምላክ’ በሚለው ቃል ፋንታ ‘ዓለት’ የሚል ቃል እንዲካተት አደረጉ።”

ዛሬም ቢሆን ለዘመናዊቷ የእስራኤል መንግሥት ሕልውና መሠረት የሆነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያሳለፈው ውሳኔና የአይሁድ ሕዝቦች ያላቸው ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መብት እንደሆነ ይገለጻል። ታዲያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው አምላክ፣ በ20ኛው መቶ ዘመን ከተፈጸሙት ሁሉ የላቀው ትንቢታዊ ተአምር ለእሱ ምንም ዓይነት እውቅና ባልሰጡ ሰዎች ላይ እንዲፈጸም ያደርጋል ብሎ መጠበቅ ምክንያታዊ ይመስልሃል?

ዘመናዊቷ የእስራኤል መንግሥት የተቋቋመችበት መንገድ ከጥንቱ ጋር ሲወዳደር

በዘመናዊቷ እስራኤል ውስጥ የሚታየው ሃይማኖት መንግሥታዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ መግባት የለበትም የሚለው አመለካከት በ537 ዓ.ዓ. ከነበረው ፈጽሞ የተለየ ነው። የእስራኤል ሕዝብ በባቢሎናውያን ድል ተነስተው በግዞት ከተወሰዱ ከ70 ዓመት በኋላ በ537 ዓ.ዓ. የተከናወነው ሁኔታ በአንድ ቀን ‘በድጋሚ የተወለዱ’ ያህል ነበር። ባቢሎንን ድል ያደረጋት የፋርሱ ንጉሥ ታላቁ ቂሮስ፣ በዚያን ጊዜ አይሁዳውያን ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ ትእዛዝ ሲያስተላልፍ ኢሳይያስ 66:8 በሚያስገርም ሁኔታ ፍጻሜውን አግኝቷል።—ዕዝራ 1:2

የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ በ537 ዓ.ዓ. የተከናወነው ነገር የይሖዋ እጅ እንዳለበት የተገነዘበ ሲሆን ሕዝቡም ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት የይሖዋን አምልኮ እንደገና ለማቋቋምና ቤተ መቅደሱን መልሰው ለመገንባት ነበር። ዘመናዊቷ የእስራኤል መንግሥት ግን እንዲህ ዓይነት ፍላጎትም ሆነ ዕቅድ እንዳላት በይፋ ገልጻ አታውቅም።

አሁንም አምላክ የመረጠው ብሔር ነው?

በ33 ዓ.ም. ሥጋዊ እስራኤላውያን፣ የይሖዋ ልጅ የሆነውን መሲሕ ለመቀበል አሻፈረኝ ባሉበት ወቅት የአምላክ ምርጥ ብሔር የመሆን መብታቸውን አጡ። መሲሑ ራሱ ሁኔታውን እንዲህ በማለት ገልጾታል፦ “ኢየሩሳሌም፣ ኢየሩሳሌም፣ ነቢያትን የምትገድል፣ ወደ እሷ የተላኩትንም በድንጋይ የምትወግር፤ . . . እነሆ፣ ቤታችሁ ለእናንተ የተተወ ይሆናል።” (ማቴዎስ 23:37, 38) በ70 ዓ.ም. የሮማውያን ሠራዊት ኢየሩሳሌምን፣ ቤተ መቅደሷንና የክህነት ሥርዓቱን ሲያጠፋ ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት በትክክል ተፈጽሟል። ይሁንና አምላክ ‘ከአሕዛብ ሁሉ የተወደደ ርስት እንዲሁም የመንግሥት ካህናትና የተቀደሰ ሕዝብ’ እንዲኖረው የነበረው ዓላማ የሚፈጸመው እንዴት ነው?—ዘፀአት 19:5, 6

በትውልድ አይሁዳዊ የሆነው ሐዋርያው ጴጥሮስ ከአሕዛብም ሆነ ከአይሁድ ለመጡ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሰጥቷል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “[እናንተ] ‘የተመረጠ ዘር፣ ንጉሣዊ ካህናት፣ ቅዱስ ብሔር፣ ልዩ ንብረት እንዲሆን የተለየ ሕዝብ’ ናችሁ። ምክንያቱም እናንተ በአንድ ወቅት አንድ ሕዝብ አልነበራችሁም፣ አሁን ግን የአምላክ ሕዝብ ናችሁ፤ ቀደም ሲል ምሕረት ያልተደረገላችሁ ሰዎች ነበራችሁ፣ አሁን ግን ምሕረት የተደረገላችሁ ሰዎች ናችሁ።”—1 ጴጥሮስ 2:7-10

በመሆኑም በአምላክ መንፈስ የተመረጡ ክርስቲያኖች የመንፈሳዊው ብሔር አባላት ሲሆኑ የዚህ ብሔር አባላት መሆናቸው በዘራቸው ወይም በሚኖሩበት አካባቢ ላይ የተመካ አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ ጉዳዩን እንዲህ በማለት ገልጾታል፦ “መገረዝም ሆነ አለመገረዝ ምንም አይጠቅምም፤ ከዚህ ይልቅ የሚጠቅመው አዲስ ፍጥረት መሆን ነው። ይህን የሥነ ምግባር መሥፈርት በመከተል በሥርዓት በሚመላለሱ ሁሉ ይኸውም በአምላክ እስራኤል ላይ ሰላምና ምሕረት ይሁን።”—ገላትያ 6:15, 16

ዘመናዊቷ የእስራኤል ብሔር በትውልድ አይሁዳዊ ለሆነ ወይም ወደ ይሁዲነት ለተለወጠ ማንኛውም ሰው ዜግነት የምትሰጥ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ‘የአምላክ እስራኤል’ ብሎ በሚጠራው ብሔር ውስጥ ግን ዜግነት የሚሰጠው “ለኢየሱስ ክርስቶስ ታዛዥ ለሚሆኑትና በደሙ ለሚረጩት” ሰዎች ብቻ ነው። (1 ጴጥሮስ 1:1, 2) ጳውሎስ የአምላክ እስራኤል አባላትን ወይም መንፈሳዊ አይሁዳውያንን በተመለከተ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እውነተኛ አይሁዳዊነት በውጫዊ ገጽታ የሚገለጽ አይደለም፤ ግርዘቱም አካላዊ ግርዘት አይደለም። ከዚህ ይልቅ በውስጡ አይሁዳዊ የሆነ እሱ አይሁዳዊ ነው፤ ግርዘቱም በተጻፈ ሕግ ሳይሆን በመንፈስ የሆነ የልብ ግርዘት ነው። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ምስጋና የሚቀበለው ከሰው ሳይሆን ከአምላክ ነው።”—ሮም 2:28, 29

ይህ ጥቅስ ጳውሎስ የተናገረውን አወዛጋቢ ሐሳብ ለመረዳት ያስችለናል። ጳውሎስ ለሮም ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ ላይ በትውልድ አይሁዳዊ ሆነው አማኝ ያልሆኑት ሰዎች ከምሳሌያዊ የወይራ ዛፍ ላይ እንደተሰበሩ ቅርንጫፎች እንደሆኑና ‘በዱር ወይራ ቅርንጫፎች’ የተመሰሉት አሕዛብ በወይራ ዛፉ ላይ እንደተጣበቁ ገልጿል። (ሮም 11:17-21) ጳውሎስ ምሳሌውን ሲደመድም እንዲህ ብሏል፦ “የአሕዛብ ቁጥር እስኪሞላ ድረስ ከእስራኤላውያን መካከል ከፊሉ ደንዝዘዋል፤ በዚህም መንገድ እስራኤል ሁሉ ይድናል።” (ሮም 11:25, 26) ጳውሎስ ይህንን ሲል በሆነ ጊዜ ላይ አይሁዳውያን በሙሉ ክርስትናን እንደሚቀበሉ ትንቢት መናገሩ ነበር? በግልጽ ማየት እንደሚቻለው እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ አልተከሰተም።

ጳውሎስ ስለ ወይራ ዛፍ የተናገረው ምሳሌ ምን ያመለክታል?

ጳውሎስ “እስራኤል ሁሉ” ሲል ሁሉንም የመንፈሳዊ እስራኤል አባላት ይኸውም በመንፈስ ቅዱስ የተመረጡትን ክርስቲያኖች ማመልከቱ ነበር። አምላክ የሚያፈሩ ቅርንጫፎች ያሉት መንፈሳዊ ‘የወይራ ዛፍ’ እንዲኖረው ያወጣው ዓላማ ሥጋዊ እስራኤላውያን መሲሑን ለመቀበል አሻፈረን በማለታቸው ሊጨናገፍ እንደማይችል መግለጹ ነበር። ይህ ደግሞ ኢየሱስ፣ ራሱን በወይን ተክል በመመሰል የማያፈሩ ቅርንጫፎቹ ተቆርጠው እንደሚጣሉ ከተናገረው ምሳሌ ጋር ይስማማል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እኔ እውነተኛው የወይን ተክል ነኝ፤ ገበሬው ደግሞ አባቴ ነው። በእኔ ላይ ያለውን ፍሬ የማያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ ቆርጦ ይጥለዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ ደግሞ ይበልጥ እንዲያፈራ ያጠራዋል።”—ዮሐንስ 15:1, 2

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ትንቢቶች ስለ ዘመናዊቷ እስራኤል መቋቋም ባይናገሩም ስለ መንፈሳዊው የእስራኤል ብሔር መቋቋም እንደተናገሩ ግን ጥርጥር የለውም! አንተም በዛሬው ጊዜ ያለውን ይህን መንፈሳዊ ብሔር ማወቅና ከዚህ ብሔር ጋር መተባበር ከቻልክ ዘላለማዊ የሆኑ በረከቶችን ታገኛለህ።—ዘፍጥረት 22:15-18፤ ገላትያ 3:8, 9