በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአምላክ ቃል ተማር

የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ ማክበር ያለብን እንዴት ነው?

የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ ማክበር ያለብን እንዴት ነው?

ይህ ርዕስ በአእምሮህ ሊመላለሱ የሚችሉ ጥያቄዎችን በማንሳት መልሶቹን መጽሐፍ ቅዱስህ ውስጥ የት ቦታ ላይ ማግኘት እንደምትችል ይጠቁምሃል። የይሖዋ ምሥክሮች ለጥያቄዎቹ በተሰጡት መልሶች ላይ ከአንተ ጋር ለመወያየት ፈቃደኞች ናቸው።

1. የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ መከበር ያለበት እንዴት ነው?

ኢየሱስ፣ ቂጣና ወይን በመጠቀም የሞቱን መታሰቢያ እንዲያከብሩ ለተከታዮቹ ነግሯቸዋል። ቂጣው የኢየሱስን ሥጋ የሚያመለክት ሲሆን ወይኑ ደግሞ ደሙን ይወክላል።​—ሉቃስ 22:19, 20ን አንብብ።

ኢየሱስ የተጠቀመበት ቂጣ ያልቦካ ወይም እርሾ ያልገባበት ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እርሾ አብዛኛውን ጊዜ ኃጢአትን ያመለክታል። ስለሆነም ኃጢአት የሌለበት የኢየሱስ ሥጋ በቂጣ መወከሉ ተገቢ ነው። ኢየሱስ ሥጋዊ አካሉን መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል፤ ይህ ደግሞ በሙሴ ሕግ ሥር ይቀርብ የነበረው የእንስሳት መሥዋዕት እንዲቀር አድርጓል። (ዕብራውያን 10:5, 9, 10) ወይኑ ደግሞ ኃጢአታችንን ለማስተሰረይ መሥዋዕት ሆኖ የፈሰሰውን የኢየሱስን ክቡር ደም ያመለክታል።​—1 ጴጥሮስ 1:19⁠ን፤ 2:24⁠ን፤ 3:18ን አንብብ።

2. የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ መከበር ያለበት መቼ ነው?

ኢየሱስ የሞተው ኒሳን 14 ይኸውም ፋሲካ በተከበረበት ዕለት ነበር። የአይሁዳውያን አዲስ ቀን የሚጀምረው ፀሐይ ስትጠልቅ ነው። ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ ከሐዋርያቱ ጋር የፋሲካን በዓል ያከበረ ሲሆን ከዚያም ሞቱን ለማስታወስ የሚያስችል አዲስ በዓል አቋቁሟል።​—ሉቃስ 22:14, 15ን አንብብ።

በዛሬው ጊዜ የአምላክ ሕዝቦች ይህን በዓል ሲያከብሩ የሚያስቡት፣ አምላክ መላውን ዓለም ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ለማውጣት በኢየሱስ አማካኝነት ስላደረገው ዝግጅት ነው። (ዘፀአት 12:5-7, 13, 17) የፋሲካ በዓል በዓመት አንድ ጊዜ ይከበር እንደነበረ ሁሉ የኢየሱስ ሞት መታሰቢያም የሚከበረው በዓመት አንድ ጊዜ ይኸውም በመጽሐፍ ቅዱስ የጨረቃ አቆጣጠር መሠረት ኒሳን 14 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ነው።​—ዮሐንስ 1:29ን አንብብ።

3. ቂጣውና ወይኑን መብላትና መጠጣት ያለባቸው እነማን ናቸው?

ኢየሱስ ወይኑን ለተከታዮቹ ከሰጠ በኋላ “ይህ ጽዋ . . . አዲሱ ቃል ኪዳን ማለት ነው” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 11:25) የሙሴ ሕግ ቃል ኪዳን በአዲሱ ቃል ኪዳን ተተክቷል፤ አምላክ፣ እስራኤላውያን እሱን በጥብቅ ከታዘዙ ሕዝቡ እንደሚሆኑ በሙሴ ሕግ ቃል ኪዳን አማካኝነት ቃል ገብቶላቸው ነበር። (ዘፀአት 19:5, 6) ይሁንና እስራኤላውያን አምላክን ሳይታዘዙ ቀሩ። በመሆኑም ይሖዋ አዲስ ቃል ኪዳን አዘጋጀ።​—ኤርምያስ 31:31ን አንብብ።

ይሖዋ በአዲሱ ቃል ኪዳን አማካኝነት በጥቂት ሰዎች ተጠቅሞ ለበርካታ ሰዎች በረከት ያፈስሳል። በቃል ኪዳኑ የታቀፉት ሰዎች 144,000 ብቻ ናቸው። በእነዚህ ሰዎች አማካኝነት፣ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት በማግኘት ይባረካሉ። በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ከታቀፉት መካከል አንዳንዶቹ በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ይሖዋን እያገለገሉ ነው። ከቂጣውና ከወይኑ የመብላትና የመጠጣት መብት ያላቸው እነዚህ ሰዎች ብቻ ናቸው፤ ምክንያቱም ይሖዋ በኢየሱስ ደም የጸናውን አዲሱን ቃል ኪዳን የገባው ከእነሱ ጋር ነው።​—ሉቃስ 12:32ን እና ራእይ 14:1, 3ን አንብብ።

4. በመታሰቢያው በዓል ላይ መገኘታችን ጥቅም የሚያስገኝልን እንዴት ነው?

በዓመት አንድ ጊዜ የሚከበረው የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ይሖዋ ላሳየን እጅግ ታላቅ ፍቅር ያለንን አድናቆት ይጨምርልናል። ይሖዋ ልጁን ወደ ምድር የላከው ለእኛ ሲል እንዲሞት ነው። በመሆኑም በመታሰቢያው በዓል ላይ ስንገኝ የኢየሱስ ሞት ለእኛ ምን ትርጉም እንዳለው ማሰላሰል አለብን። በተጨማሪም ይሖዋና ኢየሱስ ላደረጉልን ነገር ያለንን አድናቆት መግለጽ ስለምንችልበት መንገድ ማሰብ ይኖርብናል።​—ዮሐንስ 3:16ን እና 2 ቆሮንቶስ 5:14, 15ን አንብብ።

ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት እዚህ ላይ የሚታየውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ከገጽ 206-208 ተመልከት።