በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

  ከአምላክ ቃል ተማር

አምላክ ኢየሱስን ወደ ምድር የላከው ለምንድን ነው?

አምላክ ኢየሱስን ወደ ምድር የላከው ለምንድን ነው?

ይህ ርዕስ በአእምሮህ ሊመላለሱ የሚችሉ ጥያቄዎችን በማንሳት መልሶቹን መጽሐፍ ቅዱስህ ውስጥ የት ቦታ ላይ ማግኘት እንደምትችል ይጠቁምሃል። የይሖዋ ምሥክሮች ለጥያቄዎቹ በተሰጡት መልሶች ላይ ከአንተ ጋር ለመወያየት ፈቃደኞች ናቸው።

1. ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የት ነበር?

ኢየሱስ በቤተልሔም ከተማ ከመወለዱ በፊት መንፈሳዊ አካል ይዞ በሰማይ ይኖር ነበር። አምላክ መጀመሪያ የፈጠረው ኢየሱስን ነው። አምላክ በቀጥታ የፈጠረው እሱን ብቻ በመሆኑ የአምላክ አንድያ ልጅ መባሉ የተገባ ነው። በሰማይ እያለ ብዙ ጊዜ የአምላክ ቃል አቀባይ ሆኖ ያገለግል ስለነበር ቃል ተብሎም ተጠርቷል። ከዚህም ሌላ ሁሉም ነገሮች ሲፈጠሩ የአምላክ ረዳት በመሆን በፍጥረት ሥራ ተካፍሏል። (ዮሐንስ 1:2, 3, 14) ኢየሱስ፣ የሰው ልጆች ወደ ሕልውና ከመምጣታቸው በፊት ሕልቆ መሣፍርት ለሌለው ጊዜ ከአምላክ ጋር ኖሯል።—ሚክያስ 5:2ን እና ዮሐንስ 17:5ን አንብብ።

2. አምላክ ልጁን ወደ ምድር የላከው እንዴት ነው?

ይሖዋ በመንፈስ ቅዱስ ተጠቅሞ የኢየሱስን ሕይወት ከሰማይ ወደ ማርያም ማህፀን አዛወረው። በመሆኑም ኢየሱስ እንዲጸነስ ሰብዓዊ አባት አላስፈለገውም። ኢየሱስ በተወለደበት ወቅት መላእክት ልደቱን በአካባቢው ለነበሩ እረኞች አበሰሩ፤ በወቅቱ እረኞቹ በሌሊት ሜዳ ላይ መንጎቻቸውን እየጠበቁ ነበር። (ሉቃስ 2:8-12) በመሆኑም ኢየሱስ የተወለደው ከፍተኛ ቅዝቃዜ በነበረበት በታኅሣሥ ወይም በጥር ወር ሳይሆን አየሩ ሞቅ ያለ በሚሆንበት ጊዜ ይኸውም በጥቅምት መጀመሪያ አካባቢ ይመስላል። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ማርያምና ባሏ ዮሴፍ፣ ኢየሱስን ናዝሬት ወደሚገኘው ቤታቸው ይዘውት ሄዱ፤ ስለሆነም ኢየሱስ ያደገው በናዝሬት ነው። ዮሴፍ ኢየሱስን እንደ ልጁ ተንከባክቦ አሳድጎታል።—ማቴዎስ 1:18-23ን አንብብ።

ኢየሱስ 30 ዓመት ገደማ ሲሆነው ተጠመቀ፤ በዚህ ወቅት አምላክ፣ ኢየሱስ ልጁ እንደሆነ በሰዎች ፊት ተናገረ። ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ፣ አምላክ እንዲሠራው ያዘዘውን ሥራ ማከናወን ጀመረ።—ማቴዎስ 3:16, 17ን አንብብ።

 3. አምላክ ኢየሱስን ወደ ምድር የላከው ለምንድን ነው?

አምላክ ኢየሱስን የላከው ለሰዎች እውነትን እንዲያስተምር ነው። ኢየሱስ፣ በመላው ምድር ሰላም ስለሚያሰፍን በሰማይ ስለሚገኝ መንግሥት ይኸውም ስለ አምላክ መንግሥት አስተምሯል። ለሰዎች የዘላለም ሕይወት ተስፋ ሰጥቷል። (ዮሐንስ 4:14፤ 18:36, 37) ከዚህም በተጨማሪ ሰዎች እውነተኛ ደስታ ማግኘት ስለሚችሉበት መንገድ ብዙ ነገር አስተምሯል። (ማቴዎስ 5:3፤ 6:19-21) ኢየሱስ ጥሩ ምሳሌ በመሆን ትምህርት ሰጥቷል። ለምሳሌ ያህል፣ በአስቸጋሪ ሁኔታዎችም እንኳ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ አሳይቷል። ሌሎች በደል ሲያደርሱበት አጸፋውን አልመለሰም።—1 ጴጥሮስ 2:21-24ን አንብብ።

ኢየሱስ ከራስ ወዳድነት ነፃ ስለሆነ ፍቅር ለተከታዮቹ አስተምሯቸዋል። በሰማይ ከአባቱ ጋር እያለ የላቀ ቦታ ነበረው፤ ያም ሆኖ ወደ ምድር መጥቶ ከሰው ልጆች ጋር እንዲኖር አባቱ ሲልከው በትሕትና ታዝዟል። ፍቅር በማሳየት ረገድ ከኢየሱስ የተሻለ ግሩም ምሳሌ ሊሆን የሚችል ማንም የለም።—ዮሐንስ 15:12, 13ን እና ፊልጵስዩስ 2:5-8ን አንብብ።

4. የኢየሱስ ሞት ምን ነገሮችን አከናውኗል?

አምላክ ኢየሱስን የላከው ለኃጢአታችን እንዲሞትም ጭምር ነው። (ዮሐንስ 3:16) ሁላችንም ኃጢአተኞች በመሆናችን ፍጽምና ይጎድለናል። የምንታመመውና የምንሞተው በዚህ ምክንያት ነው። ከዚህ በተለየ መልኩ የመጀመሪያው ሰው አዳም ፍጹም ነበር። ኃጢአት ስላልነበረበት አይታመምም እንዲሁም አይሞትም ነበር። ይሁንና አዳም በአምላክ ላይ ሲያምፅ ፍጽምና የጎደለው ሆነ። እኛም ከአዳም ኃጢአትን እና የኃጢአት ደሞዝ የሆነውን ሞትን ወረስን።—ሮም 5:12ን እና ሮም 6:23ን አንብብ።

ኢየሱስ ፍጹም ሰው ስለነበር የሞተው በራሱ ኃጢአት ምክንያት ሊሆን አይችልም። ኢየሱስ የሞተው ለእኛ ኃጢአት ነው። የኢየሱስ ሞት የዘላለም ሕይወትና የአምላክን በረከት እንድናገኝ መንገድ ከፍቶልናል።—1 ጴጥሮስ 3:18ን አንብብ።