በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወደ አምላክ ቅረብ

“የማይታዩት ባሕርያቱ . . . በግልጽ ይታያሉ”

“የማይታዩት ባሕርያቱ . . . በግልጽ ይታያሉ”

በአምላክ ታምናለህ? የምታምን ከሆነ ስለ እሱ መኖር ማስረጃ ማቅረብ ትችላለህ? እንደ እውነቱ ከሆነ ጥበበኛ፣ ኃያልና አፍቃሪ የሆነ ፈጣሪ ለመኖሩ አጠገባችን ያለውን ማስረጃ መጥቀስ ይቻላል። ይህ ማስረጃ ምንድን ነው? ደግሞስ ምን ያህል አሳማኝ ነው? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለነበሩት ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን ቃላት እንመልከት።

ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “[የአምላክ] የማይታዩት ባሕርያቱ ይኸውም ዘላለማዊ ኃይሉና አምላክነቱ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በግልጽ ይታያሉ፤ ምክንያቱም ባሕርያቱን ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል፤ ስለሆነም የሚያመካኙበት ነገር የላቸውም።” (ሮም 1:20) ጳውሎስ እንደገለጸው ፈጣሪ በሠራው ነገር ሁሉ ላይ የእሱን ማንነት የሚጠቁም አሻራ ትቷል። እስቲ የጳውሎስን ቃላት በጥልቀት እንመርምር።

የአምላክ ባሕርያት “ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ” እንደሚታዩ ጳውሎስ ገልጿል። “ዓለም” የሚለው ቃል በዚህ አገባቡ የሚያመለክተው ፕላኔቷን ምድር አይደለም። ከዚህ ይልቅ የሰውን ዘር ያመለክታል። a በመሆኑም ጳውሎስ ሰዎች ከተፈጠሩበት ጊዜ አንስቶ፣ አምላክ ከሠራቸው ነገሮች የእሱን ባሕርያት መመልከት እንደሚችሉ እየተናገረ ነበር።

ይህ ማስረጃ በዙሪያችን ሞልቷል። ማስረጃው በተፈጥሮ ውስጥ ተደብቆ የሚገኝ ሳይሆን ‘በግልጽ የሚታይ’ ነው። ከትልቁ አንስቶ እስከ ትንሹ ድረስ ያሉት የፍጥረት ሥራዎች፣ ፈጣሪ መኖሩን ብቻ ሳይሆን አስደናቂ ባሕርያት እንዳሉትም ጭምር በግልጽ ያሳያሉ። ታዲያ በፍጥረት ላይ በግልጽ የሚንጸባረቀው አስገራሚ ንድፍ የአምላክን ጥበብ የሚያሳይ አይደለም? በከዋክብት የተሞሉት ሰማያትና ከባድ የሆኑ የባሕር ሞገዶች የእሱን ኃይል የሚያሳዩ አይደሉም? ፀሐይ ስትወጣና ስትጠልቅ ያለው ማራኪ እይታ ብሎም አስደሳች ጣዕም ያላቸው የተለያዩ ምግቦችስ ቢሆኑ አምላክ ለሰው ዘር ያለውን ፍቅር የሚገልጹ አይደሉም?—መዝሙር 104:24፤ ኢሳይያስ 40:26

ታዲያ ይህ ማስረጃ ምን ያህል በግልጽ የሚታይ ነው? ማስረጃው በጣም ግልጽ ስለሆነ ከእይታ የተሰወረ አይደለም፤ ይህን ማስረጃ ሳያዩ በመቅረት አምላክ መኖሩን ለማመን ፈቃደኛ የማይሆኑ ሰዎች “የሚያመካኙበት ነገር” የማይኖራቸው ለዚህ ነው። አንድ ምሁር ጉዳዩን ግልጽ ለማድረግ የሚከተለውን ምሳሌ ተጠቅመዋል፦ አንድ አሽከርካሪ “ተለዋጭ መንገድ—ወደ ግራ ታጠፍ” ለሚለው የመንገድ ምልክት ትኩረት ሳይሰጥ በመቅረቱ በተከለከለ መንገድ መንዳቱን ቀጠለ እንበል። በዚህ ጊዜ አንድ ትራፊክ ፖሊስ ያስቆመውና የቅጣት ወረቀት ይጽፍለታል። አሽከርካሪው ምልክቱን እንዳላየው በመናገር ይከራከራል። ይሁን እንጂ የተናገረው ነገር ተቀባይነት አይኖረውም፤ ምክንያቱም ምልክቱ በግልጽ የሚታይ ከመሆኑም በላይ አሽከርካሪው የማየት ችግር የለበትም። ደግሞም ሾፌር እንደመሆኑ መጠን እንዲህ ያሉትን የመንገድ ምልክቶች የማየትና የማክበር ግዴታ አለበት። አምላክ መኖሩን ከሚያረጋግጠው በተፈጥሮ ውስጥ ከሚገኘው ማስረጃ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። “ምልክቱ” በግልጽ የሚታይ ነው። የማሰብ ችሎታ ያለን ፍጡሮች እንደመሆናችን መጠን ማስረጃውን ማየት እንችላለን። በመሆኑም አላየሁም ብለን ማመካኘት አንችልም።

ፈጣሪ በሠራቸው ነገሮች ሁሉ ላይ አሻራውን ትቷል

በእርግጥም እንደ መጽሐፍ ሊቆጠሩ ከሚችሉት የፍጥረት ሥራዎች ስለ ፈጣሪያችን ብዙ ማወቅ እንችላለን። ይሁን እንጂ ስለ ፈጣሪያችን የበለጠ እንድናውቅ የሚያስችል ሌላ መጽሐፍ አለ፤ እሱም መጽሐፍ ቅዱስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ፣ ‘አምላክ ለምድርና በውስጧ ለሚኖሩ የሰው ዘሮች ያለው ዓላማ ምንድን ነው?’ ለሚለው መሠረታዊ ጥያቄ መልስ ማግኘት እንችላለን። የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቃችን ‘የማይታዩት ባሕርያቱን’ በዙሪያችን ባለው የፍጥረት ሥራው ላይ ‘በግልጽ ማየት ወደምንችለው’ አምላክ ይበልጥ እንድንቀርብ ሊረዳን ይችላል።

በነሐሴ ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል

ሮም 1 እስከ 16

a መጽሐፍ ቅዱስ “ዓለም” ኃጢአተኛ እንደሆነና አዳኝ እንደሚያስፈልገው የሚናገርበት ቦታ አለ፤ ቃሉ በዚህ አገባቡ የሚያመለክተው ምድርን ሳይሆን የሰው ዘርን እንደሆነ ግልጽ ነው።—ዮሐንስ 1:29፤ 4:42፤ 12:47