መዝሙር 104:1-35

  • ድንቅ ለሆኑት የፍጥረት ሥራዎች አምላክን ማወደስ

    • ምድር ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች (5)

    • የወይን ጠጅና ምግብ ሰውን ያስደስታል (15)

    • “ሥራህ ምንኛ ብዙ ነው!” (24)

    • ‘መንፈሳቸውን ስትወስድ ይሞታሉ’ (29)

104  ይሖዋን ላወድስ።*+ ይሖዋ አምላኬ ሆይ፣ አንተ እጅግ ታላቅ ነህ።+ ሞገስንና* ግርማን ለብሰሃል።+   ብርሃንን እንደ ልብስ ተጎናጽፈሃል፤+ሰማያትን እንደ ድንኳን መጋረጃ ዘርግተሃል።+   የላይኛዎቹን ክፍሎች ተሸካሚዎች ከላይ ባሉት ውኃዎች ላይ* ያኖራል፤+ደመናትን ሠረገላው ያደርጋል፤+በነፋስ ክንፎችም ይሄዳል።+   መላእክቱን መናፍስት፣አገልጋዮቹን የሚባላ እሳት ያደርጋል።+   ምድርን በመሠረቶቿ ላይ መሠረታት፤+እሷም ለዘላለም ከቦታዋ አትናወጥም።+   ጥልቅ ውኃን እንደ ልብስ አለበስካት።+ ውኃዎቹ ከተራሮቹ በላይ ቆሙ።   በገሠጽካቸው ጊዜ ሸሹ፤+የነጎድጓድህን ድምፅ ሲሰሙ በድንጋጤ ፈረጠጡ፤   ተራሮች ወደ ላይ ወጡ፤+ ሸለቆዎችም ወደ ታች ወረዱ፤ሁሉም ወዳዘጋጀህላቸው ቦታ ሄዱ።   ውኃዎቹ አልፈው እንዳይሄዱ፣እንደገናም ምድርን እንዳይሸፍኑ ወሰን አበጀህላቸው።+ 10  ምንጮችን ወደ ሸለቆዎች* ይልካል፤በተራሮች መካከል ይፈስሳሉ። 11  የዱር አራዊት ሁሉ ከዚያ ይጠጣሉ፤የዱር አህዮችም ጥማቸውን ይቆርጣሉ። 12  የሰማይ ወፎች ከእነሱ በላይ ይሰፍራሉ፤በለመለሙ የዛፍ ቅርንጫፎች መካከል ሆነው ይዘምራሉ። 13  ከላይ ካሉት ክፍሎቹ ሆኖ ተራሮችን ያጠጣል።+ በሥራህ ፍሬ ምድር ረካች።+ 14  ሣርን ለከብት፣አትክልትንም ለሰው ልጆች ጥቅም ያበቅላል፤+ይህን የሚያደርገው ምድር እህል እንድታስገኝ ነው፤ 15  እንዲሁም የሰውን ልብ ደስ የሚያሰኝ የወይን ጠጅ፣+ፊትን የሚያበራ ዘይትናየሰውን ልብ የሚያበረታ እህል እንዲገኝ ነው።+ 16  የይሖዋ ዛፎች፣ እሱ የተከላቸው አርዘ ሊባኖሶች፣ውኃ ጠጥተው ይረካሉ፤ 17  በዚያ ወፎች ጎጇቸውን ይሠራሉ። ራዛ*+ በጥድ ዛፎች ላይ ትኖራለች። 18  ረጃጅሞቹ ተራሮች፣ የተራራ ፍየሎች+ መኖሪያ ናቸው፤ቋጥኞቹ የሽኮኮዎች+ መሸሸጊያ ናቸው። 19  ጊዜያትን ለመለየት ጨረቃን ሠራ፤ፀሐይ የምትጠልቅበትን ጊዜ በሚገባ ታውቃለች።+ 20  ጨለማን ታመጣለህ፤ ሌሊትም ይሆናል፤+በዚህ ጊዜ በጫካ የሚኖሩ አራዊት ሁሉ ወጥተው ይንቀሳቀሳሉ። 21  ደቦል አንበሶች አደን ለማግኘት ያገሳሉ፤+ምግባቸውንም ከአምላክ ይሻሉ።+ 22  ፀሐይ ስትወጣ፣ተመልሰው በየጎሬአቸው ይተኛሉ። 23  ሰውም ወደ ሥራው ተሰማርቶእስኪመሽ ድረስ ሲሠራ ይውላል። 24  ይሖዋ ሆይ፣ ሥራህ ምንኛ ብዙ ነው!+ ሁሉንም በጥበብ ሠራህ።+ ምድር በፈጠርካቸው ነገሮች ተሞልታለች። 25  ባሕሩ እጅግ ትልቅና ሰፊ ነው፤በዚያ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ትናንሽም ሆኑ ትላልቅ ሕያዋን ነገሮች ይርመሰመሳሉ።+ 26  በዚያም መርከቦች ይጓዛሉ፤በዚያ እንዲጫወት የፈጠርከው ሌዋታንም*+ በውስጡ ይሄዳል። 27  በወቅቱ ምግባቸውን እንድትሰጣቸው፣ሁሉም አንተን ይጠባበቃሉ።+ 28  አንተ የምትሰጣቸውን ይሰበስባሉ።+ እጅህን ስትከፍት መልካም ነገሮችን ይጠግባሉ።+ 29  ፊትህን ስትሰውር ይታወካሉ። መንፈሳቸውን ከወሰድክ ይሞታሉ፤ ወደ አፈርም ይመለሳሉ።+ 30  መንፈስህን ከላክ ይፈጠራሉ፤+የምድርንም ገጽ ታድሳለህ። 31  የይሖዋ ክብር ለዘላለም ይኖራል። ይሖዋ በሥራው ሐሴት ያደርጋል።+ 32  ምድርን ሲመለከት ትንቀጠቀጣለች፤ተራሮችን ሲነካ ይጨሳሉ።+ 33  በሕይወቴ ዘመን ሁሉ ለይሖዋ እዘምራለሁ፤+በሕይወት እስካለሁ ድረስ ለአምላኬ የውዳሴ መዝሙር እዘምራለሁ።+ 34  ሐሳቤ እሱን የሚያስደስት ይሁን።* እኔም በይሖዋ ሐሴት አደርጋለሁ። 35  ኃጢአተኞች ከምድር ይጠፋሉ፤ክፉዎችም ከእንግዲህ አይገኙም።+ ይሖዋን ላወድስ።* ያህን አወድሱ!*

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ክብርንና።”
ወይም “ነፍሴ ይሖዋን ታወድስ።”
ቃል በቃል “በውኃዎቹ ውስጥ።”
ወይም “ደረቅ ወንዞች።”
ባለ ረጃጅም እግር ትልቅ አሞራ።
“ስለ እሱ የማሰላስለው ነገር ደስ የሚያሰኝ ይሁን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ነፍሴ ይሖዋን ታወድስ።”
ወይም “ሃሌሉያህ!” “ያህ” የይሖዋ ስም አጭር መጠሪያ ነው።