በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት

የአምላክ መንግሥት መግዛት የጀመረው መቼ ነው? (ክፍል 2)

የአምላክ መንግሥት መግዛት የጀመረው መቼ ነው? (ክፍል 2)

የይሖዋ ምሥክሮች ከሰዎች ጋር ምን ዓይነት ውይይት እንደሚያደርጉ የሚያሳይ ምሳሌ ከዚህ በታች ቀርቧል። ዳዊት የሚባል አንድ የይሖዋ ምሥክር ኢዮብ የሚባልን ሰው ቤቱ ሄዶ እያወያየው እንዳለ አድርገን እናስብ።

የናቡከደነፆርን ሕልም በአጭሩ መከለስ

ዳዊት፦ ታዲያስ ኢዮብ፣ እንደምን አለህ? በየሳምንቱ እንዲህ እየተገናኘን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የምናደርገው ውይይት በጣም ያስደስተኛል። * ለመሆኑ እንዴት ነህ?

ኢዮብ፦ እኔ ደህና ነኝ፤ አንተስ?

ዳዊት፦ እኔም በጣም ደህና ነኝ። ባለፈው ጊዜ ባደረግነው ውይይት ላይ የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክ መንግሥት መግዛት የጀመረው በ1914 ነው ብለው የሚያምኑት ለምን እንደሆነ ተነጋግረን ነበር። * ይህን እንድናምን ያደረገንን አንዱን ማስረጃም ተመልክተናል፤ ይህ ማስረጃ የሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በ⁠ዳንኤል ምዕራፍ 4 ላይ በተገለጸ አንድ ትንቢት ላይ ነው። በዳንኤል ምዕራፍ 4 ላይ ያለውን ሐሳብ ታስታውሰዋለህ?

ኢዮብ፦ አዎ፣ ሐሳቡ የሚናገረው ንጉሥ ናቡከደነፆር በሕልሙ ስላየው አንድ ትልቅ ዛፍ ነው።

ዳዊት፦ ልክ ነህ። ናቡከደነፆር በሕልሙ፣ ቁመቱ እስከ ሰማይ የሚደርስ አንድ ግዙፍ ዛፍ አየ። ከዚያም አንድ የአምላክ መልእክተኛ ዛፉ እንዲቆረጥ፣ ጉቶውና ሥሩ ግን በመሬት ውስጥ እንዲቆይ ትእዛዝ ሲያስተላልፍ ሰማ። “ሰባት ዓመት” ካለፈ በኋላ ዛፉ እንደገና ማደግ ይጀምራል። * በተጨማሪም ትንቢቱ ሁለት ፍጻሜዎች አሉት የምንለው ለምን እንደሆነ ተወያይተናል። የመጀመሪያው የትንቢቱ ፍጻሜ ምን እንደሆነ ታስታውሳለህ?

ኢዮብ፦ አዎ፣ ትንቢቱ በመጀመሪያ የተፈጸመው በራሱ በናቡከደነፆር ላይ ነው አይደል? ለሰባት ዓመታት አእምሮውን ስቶ ነበር።

ዳዊት፦ በትክክል። ናቡከደነፆር ለተወሰነ ጊዜ አእምሮውን ስለሳተ አገዛዙ ተቋርጦ ነበር። ይሁን እንጂ ትንቢቱ ዋነኛ ፍጻሜውን ሲያገኝ የአምላክ አገዛዝም ‘ለሰባት ዓመታት’ ይቋረጣል። ባለፈው እንዳየነው በትንቢቱ ላይ የተገለጹት “ሰባት ዓመታት” የጀመሩት ኢየሩሳሌም በ607 ዓ.ዓ. በጠፋች ጊዜ ነበር። ከዚያን ጊዜ ወዲህ በምድር ላይ ይሖዋን ወክለው የእሱን ሕዝብ የሚገዙ ነገሥታት አልተነሱም። ይሁን እንጂ ‘ሰባቱ ዓመታት’ ሲያበቁ አምላክ የእሱን ሕዝብ የሚገዛ አዲስ ንጉሥ ያነግሣል፤ ይህ የሚሆነው ግን በሰማይ ነው። በሌላ አነጋገር፣ የአምላክ መንግሥት በሰማይ መግዛት የሚጀምረው ‘ሰባቱ ዓመታት’ ሲያበቁ ነው። ‘ሰባቱ ዓመታት’ የጀመሩት መቼ እንደሆነ ቀደም ብለን ተወያይተናል። ስለዚህ ‘የሰባቱን ዓመታት’ ርዝማኔ ማወቅ ከቻልን የአምላክ መንግሥት መግዛት የሚጀምረው መቼ እንደሆነ ማወቅ እንችላለን ማለት ነው። እስካሁን ያልኩት ግልጽ ሆኖልሃል?

ኢዮብ፦ አዎን፣ ባለፈው የተወያየንበትን መከለስህ ነጥቦቹን እንዳስታውስ ረድቶኛል።

ዳዊት፦ በጣም ጥሩ። እንግዲያውስ ሰባቱ ዓመታት ምን ያህል ርዝማኔ እንዳላቸው እንመልከት። ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች ለማስታወስ እንዲረዳኝ እኔ ራሴ አንተ ጋር ከመምጣቴ በፊት ስለ ጉዳዩ አንብቤ ነበር። እስቲ የቻልኩትን ያህል በደንብ ለማብራራት ልሞክር።

ኢዮብ፦ እሺ።

ሰባቱ ዓመታት አበቁ፤ እንዲሁም የመጨረሻዎቹ ቀኖች ጀመሩ

ዳዊት፦ ትንቢቱ በናቡከደነፆር ላይ የመጀመሪያውን ፍጻሜ ሲያገኝ በትንቢቱ ላይ የተገለጹት “ሰባት ዓመታት” ርዝማኔ ቃል በቃል ሰባት ዓመት የነበረ ይመስላል። ይሁን እንጂ ትንቢቱ ከአምላክ መንግሥት ጋር በተያያዘ ፍጻሜውን ሲያገኝ ‘ሰባቱ ዓመታት’ ቃል በቃል ሰባት ዓመታትን ሳይሆን ከዚያ የበለጠ ጊዜን የሚያመለክቱ መሆን አለባቸው።

ኢዮብ፦ እንዲህ ያልከው ለምንድን ነው?

ዳዊት፦ በመጀመሪያ፣ ሰባቱ ዓመታት የጀመሩት ኢየሩሳሌም በ607 ዓ.ዓ. በጠፋች ጊዜ እንደሆነ አስታውስ። ከዚህ ዓመት ጀምረን ቃል በቃል ሰባት ዓመታት ብንቆጥር 600 ዓ.ዓ. ላይ እንደርሳለን። ይሁን እንጂ ከአምላክ አገዛዝ ጋር በተያያዘ በዚህ ዓመት ምንም የተፈጸመ ነገር የለም። ከዚህም ሌላ ባለፈው ጊዜ እንደተመለከትነው ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት እነዚህ “ሰባት ዓመታት” እንዳላበቁ ተናግሯል።

ኢዮብ፦ አሃ፣ ልክ ነው። አሁን አስታወስኩት።

ዳዊት፦ ከዚህ አንጻር እነዚህ “ሰባት ዓመታት” ቃል በቃል ሰባት ዓመታት ሳይሆኑ ከዚህ የበለጠ ርዝማኔ ያለውን ጊዜ የሚያመለክቱ መሆን አለባቸው።

ኢዮብ፦ ምን ያህል ጊዜ?

ዳዊት፦ ከዳንኤል መጽሐፍ ጋር ተያያዥነት ያለው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው የራእይ መጽሐፍ ሰባቱ ዓመታት ምን ያህል ርዝማኔ እንዳላቸው በትክክል እንድናውቅ ይረዳናል። መጽሐፉ ሦስት ተኩል ዘመናት ወይም ዓመታት የ1,260 ቀናት ርዝማኔ እንዳላቸው ይናገራል። * ሰባት ዓመታት ደግሞ የሦስት ተኩል ዘመናት ወይም ዓመታት እጥፍ ናቸው፤ ስለዚህ ሰባቱ ዓመታት የ2,520 ቀናት ርዝማኔ ይኖራቸዋል ማለት ነው። እስካሁን ያልኩት ግልጽ ነው?

ኢዮብ፦ አዎን፣ ገብቶኛል። ይሁን እንጂ ይህ፣ የአምላክ መንግሥት በ1914 መግዛት መጀመሩን የሚያሳየው እንዴት እንደሆነ አልገባኝም።

ዳዊት፦ እሺ፣ ይህ ጊዜ ከአምላክ መንግሥት ጋር ምን ግንኙነት እንዳለው እንመልከት። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንድ ቀን የአንድ ዓመት ርዝማኔ እንዳለው ተደርጎ የተገለጸበት ጊዜ አለ። * ስለዚህ አንድ ቀን እንደ አንድ ዓመት የሚለውን ደንብ ከተጠቀምን ሰባቱ ዓመታት 2,520 ዓመታት ይሆናሉ ማለት ነው። ከ607 ዓ.ዓ. ጀምረን 2,520 ዓመታት ብንቆጥር 1914 ላይ እንደርሳለን። * ስለዚህ 1914 ሰባቱ ዓመታት የሚያበቁበትና ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መግዛት የሚጀምርበት ዓመት ይሆናል ማለት ነው። ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስ በመጨረሻዎቹ ቀናት እንደሚፈጸሙ የተናገራቸው ክስተቶች ከ1914 ወዲህ ግልጽ በሆነ ሁኔታ መፈጸም ጀምረዋል።

ኢዮብ፦ ምን ዓይነት ክስተቶች?

ዳዊት፦ ኢየሱስ እሱ መግዛት በሚጀምርበት ጊዜ በምድር ላይ የሚከናወኑትን ነገሮች አስመልክቶ በ⁠ማቴዎስ 24:7 ላይ ምን እንዳለ እስቲ እንመልከት። “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳል፤ በተለያየ ስፍራ የምግብ እጥረትና የምድር ነውጥ ይከሰታል” ብሏል። ኢየሱስ በዚህ ወቅት የምግብ እጥረትና የምድር ነውጥ እንደሚኖር መናገሩን ልብ በል። ደግሞም ባለፈው መቶ ዓመት ውስጥ እነዚህ ችግሮች በዓለማችን ላይ በብዛት ታይተዋል አይደል?

ኢዮብ፦ አዎ፣ ልክ ነህ።

ዳዊት፦ በተጨማሪም ኢየሱስ፣ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በሚገኝበት ወቅት ጦርነት እንደሚኖር እዚህ ጥቅስ ላይ ተናግሯል። የራእይ መጽሐፍም በፍጻሜው ዘመን በአንድ አካባቢ ብቻ ሳይሆን መላውን ዓለም የሚነኩ ጦርነቶች እንደሚኖሩ የሚገልጽ ትንቢት ይዟል። * የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት የፈነዳው መቼ እንደሆነ ታስታውሳለህ?

ኢዮብ፦ በ1914 ነው፤ አሃ፣ ኢየሱስ መግዛት ጀምሯል ያልከውም በዚህ ዓመት ነው ለካ! እንደዚህ አስቤው አላውቅም ነበር።

ዳዊት፦ እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረስነው እነዚህን ሁሉ ማስረጃዎች ይኸውም ስለ ሰባቱ ዓመታት የሚገልጸውን ትንቢትና ስለ ፍጻሜው ዘመን የሚናገሩ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን በማስተያየት ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መግዛት የጀመረውም ሆነ የመጨረሻዎቹ ቀኖች የጀመሩት በ1914 እንደሆነ ያምናሉ። *

ኢዮብ፦ ይህንን ሐሳብ ሙሉ በሙሉ ለመረዳት ትንሽ ጊዜ የሚያስፈልገኝ ይመስለኛል።

ዳዊት፦ ይገባኛል። ከዚህ በፊት እንደነገርኩህ እኔም ይህንን ሐሳብ ሙሉ በሙሉ ለመረዳት ጊዜ ወስዶብኛል። ይሁን እንጂ እስካሁን ያደረግነው ውይይት 1914 የሚለው ዓመት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በቀጥታ ባይጠቀስም እንኳ የይሖዋ ምሥክሮች ስለ 1914 የሚያምኑት ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መሆኑን እንድትረዳ አስችሎሃል የሚል ተስፋ አለኝ።

ኢዮብ፦ አዎን፣ ይሄ ነገራችሁ ሁልጊዜም ያስደንቀኛል፤ ለምትናገሩት ነገር ሁሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ማስረጃ ታቀርባላችሁ። የምትናገሩት የራሳችሁን አመለካከት አይደለም። ይሁንና ጉዳዩ እንዲህ የተወሳሰበው ለምንድን ነው ብዬ እያሰብኩ ነበር። ኢየሱስ በሰማይ መግዛት የሚጀምረው በ1914 እንደሆነ አምላክ በቀጥታ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲሰፍር ማድረግ አይችልም ነበር?

ዳዊት፦ ይህ በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው። እንዲያውም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ያልተቀመጡ ብዙ ነገሮች አሉ። ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ጥረት ይጠይቅባቸዋል፤ በመሆኑም ‘አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን በዚህ መንገድ ያስጻፈው ለምንድን ነው?’ የሚል ጥያቄ ይነሳል። ስለዚህ ጉዳይ ሌላ ጊዜ ስመጣ ብንነጋገርበት ምን ይመስልሃል?

ኢዮብ፦ ደስ ይለኛል።

ለመረዳት ያስቸገረህ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ አለ? የይሖዋ ምሥክሮች ስለሚያምኑባቸው ነገሮች ወይም ስለ ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸው ለማወቅ ትፈልጋለህ? ከሆነ በሚቀጥለው ጊዜ ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር ስትገናኝ ጥያቄህን ከማቅረብ ወደኋላ አትበል። የይሖዋ ምሥክሮች ስለ እነዚህ ጉዳዮች ከአንተ ጋር ለመወያየት ፈቃደኛ ናቸው።

^ አን.5 የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ ለማስተማር ባደረጉት ዝግጅት አማካኝነት ከሰዎች ጋር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ርዕስ በርዕስ ይወያያሉ።

^ አን.7 በዚህ መጽሔት የጥቅምት 1, 2014 እትም ላይ የወጣውን “መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት—የአምላክ መንግሥት መግዛት የጀመረው መቼ ነው?—ክፍል 1” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.9 ዳንኤል 4:23-25⁠ን ተመልከት።

^ አን.22 ራእይ 12:6, 14⁠ን (የ1980 ትርጉም) ተመልከት።

^ አን.24 ዘኍልቍ 14:34⁠ን እና ሕዝቅኤል 4:6⁠ን ተመልከት።

^ አን.24 “ናቡከደነፆር ስለ አንድ ዛፍ ያየው ሕልም” የተሰኘውን ሠንጠረዥ ተመልከት።