በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ውድ የሆነ ጥንታዊ ሀብት ከቆሻሻ መሃል ማግኘት

ውድ የሆነ ጥንታዊ ሀብት ከቆሻሻ መሃል ማግኘት

የቆሻሻ ክምር ሲባል ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? ጥራጊና መጥፎ ጠረን ያለው ነገር ታስብ ይሆናል። በመሆኑም እንዲህ ካለው ቦታ፣ ዋጋ ያለው ነገር አገኛለሁ ብለህ እንደማትጠብቅ የታወቀ ነው፤ ውድ ሀብት ማግኘትማ የማይታሰብ ነገር ነው።

የሚገርመው ግን ከመቶ ዓመት በፊት አንድ ውድ ሀብት በቆሻሻ መሃል ተገኝቷል። የተገኘው ነገር በቁሳዊ ረገድ የከበረ ሀብት ከሚባሉት የሚመደብ ባይሆንም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው። ለመሆኑ ይህ ውድ ሀብት ምንድን ነው? በዛሬው ጊዜ ላለነው ጠቃሚ የሆነውስ ለምንድን ነው?

ያልተጠበቀ ግኝት

በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩት በርናርድ ፓይን ግሬንፌል እና አርተር ሰሪጅ ሀንት የተባሉ ምሁራን በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ግብፅን ጎብኝተው ነበር። በዚያም በናይል ሸለቆ አቅራቢያ በሚገኝ የቆሻሻ ክምር መሃል በርካታ የፓፒረስ ቁርጥራጮች አገኙ። በ1920 ሁለቱ የሥራ ባልደረቦች ያገኟቸውን ነገሮች ለይተው በመመዝገብ ላይ እያሉ ግሬንፌል ከግብፅ በቁፋሮ የተገኙ ጥቂት ተጨማሪ ቁርጥራጮችን ገዛ። እነዚህን ቁርጥራጮች የገዛው ማንቸስተር፣ እንግሊዝ ውስጥ የሚገኘውን ዘ ጆን ራይላንድስ ቤተ መጻሕፍት ወክሎ ነበር። ይሁን እንጂ ሁለቱም ሰዎች ዝርዝሩን አዘጋጅተው ከመጨረሳቸው በፊት ሞቱ።

ኮለን ሮበርትስ የሚባል ሌላ የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ምሁር እነሱ የጀመሩትን ሥራ አጠናቀቀው። ሮበርትስ ቁርጥራጮቹን እየለየ ሳለ 9 ሴንቲ ሜትር በ6 ሴንቲ ሜትር የሆነ አንድ የፓፒረስ ቁራጭ አገኘ። በግሪክኛ ቋንቋ የተጻፈው ይህ ጥንታዊ ቅጂ እሱ የሚያውቃቸውን ቃላት የያዘ መሆኑ በጣም አስገረመው። የቁራጩ አንደኛው ገጽ በዮሐንስ 18:31-33 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ የያዘ ነው። ሌላኛው ገጽ ደግሞ የቁጥር 37 እና 38ን ከፊል ሐሳብ ይዟል። ሮበርትስ በአጋጣሚ ያገኘው ነገር ውድ ሀብት እንደሆነ ተገነዘበ።

ዕድሜውን ማወቅ

ሮበርትስ፣ ይህ የፓፒረስ ቁራጭ በጣም ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረ እንደሆነ ቢጠረጥርም ዕድሜው ምን ያህል እንደሆነ እርግጠኛ አልሆነም። ይህን ለማወቅ በቁራጩ ላይ ያለውን የእጅ ጽሑፍ፣ ዕድሜያቸው ከሚታወቅ ሌሎች ጥንታዊ ጽሑፎች ጋር አነጻጸረው፤ ይህ የጥናት መስክ ፔሊዮግራፊ ተብሎ ይጠራል። * ይህን ዘዴ በመጠቀም የጥንታዊውን ጽሑፍ ዕድሜ መገመት ችሎ ነበር። ይሁን እንጂ እርግጠኛ መሆን ፈለገ። ስለዚህ ይህን ቁራጭ ፎቶግራፍ ካነሳ በኋላ ፎቶግራፎቹን ጥንታዊ የፓፒረስ ጽሑፎችን ወደሚያጠኑ ሦስት ምሁራን በመላክ የተጻፈበትን ዘመን እንዲነግሩት ጠየቃቸው። ታዲያ እነዚህ ባለሙያዎች ምን ድምዳሜ ላይ ደረሱ?

የጥንታዊውን ጽሑፍ የፊደል አጣጣል እንዲሁም በጽሑፉ ላይ የሚገኙትን ጭረቶች በማጥናት ይህ ጥንታዊ ጽሑፍ የተጻፈው በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ ማለትም ሐዋርያው ዮሐንስ ከሞተ ከጥቂት አሥርተ ዓመታት በኋላ እንደሆነ ሦስቱም ምሁራን ተስማሙ! ይሁን እንጂ ፔሊዮግራፊ፣ የጥንታዊ ጽሑፎችን ዕድሜ በእርግጠኝነት ለማወቅ የሚያስችል ዘዴ አይደለም፤ አንድ ሌላ ምሁር ይህ ጥንታዊ ጽሑፍ በሁለተኛው መቶ ዘመን ውስጥ በማንኛውም ጊዜ የተጻፈ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል። ያም ሆኖ፣ ይህ ትንሽ የፓፒረስ ቁራጭ እስካሁን ከተገኙት ሁሉ እጅግ ጥንታዊው የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂ ነው።

ፓፒረስ ራይላንድስ ምን ይጠቁማል?

በዛሬው ጊዜ የሚገኙ መጽሐፍ ቅዱስን የሚወዱ ሰዎች ከዮሐንስ ወንጌል ለተወሰደው ለዚህ ቁራጭ ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ለምንድን ነው? ቢያንስ ሁለት ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ይህ ጥንታዊ ጽሑፍ የተዘጋጀበት መንገድ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ቅዱሳን መጻሕፍትን ምን ያህል ከፍ አድርገው ይመለከቱ እንደነበረ ለማስተዋል ይረዳናል።

መጽሐፍ ቅዱስን የሚወዱ ሰዎች ከዮሐንስ ወንጌል ለተወሰደው ለዚህ ቁራጭ ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ለምንድን ነው?

በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ጽሑፍ ይዘጋጅ የነበረው በሁለት መንገዶች ይኸውም በጥቅልልና በኮዴክስ መልክ ነበር። ጥቅልሎችን ለማዘጋጀት የፓፒረስ ወይም የብራና ቁርጥራጮችን በማጣበቅ ወይም አገናኝቶ በመስፋት አንድ ረጅም ገጽ ይሠራል። ይህ ገጽ ሊጠቀለልና በሚያስፈልግ ጊዜ ደግሞ ጥቅልሉ ሊተረተር ይችላል። በአብዛኛው የሚጻፈው በጥቅልሉ አንደኛው ገጽ ላይ ብቻ ነበር።

ይሁን እንጂ ሮበርትስ ያገኘው የጥንታዊ ጽሑፍ ቁራጭ በሁለቱም ገጾች የተጻፈበት ነው። ይህም ይህ ጥንታዊ ጽሑፍ፣ ጥቅልል ሳይሆን ኮዴክስ እንደነበር ይጠቁማል። ኮዴክስ የሚዘጋጀው ከብራና ወይም ከፓፒረስ የተሠሩ ገጾች አንድ ላይ ከተሰፉ በኋላ አጥፎ በመጠረዝ ነው።

ኮዴክስ ከጥቅልል የተሻለ የነበረው ለምንድን ነው? የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ወንጌላውያን ነበሩ። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ሰዎች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ማለትም ከቤት ወደ ቤት፣ በገበያ ስፍራዎችና በጎዳናዎች ላይ ያሰራጩ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 5:42፤ 17:17፤ 20:20) በመሆኑም ቅዱሳን መጻሕፍት አንድ ላይ ተጠርዘው መዘጋጀታቸው ለሥራቸው በጣም አመቺ ነበር።

በተጨማሪም ኮዴክስ፣ ጉባኤዎችና ግለሰቦች የራሳቸውን የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ማዘጋጀት ቀላል እንዲሆንላቸው አድርጓል። በመሆኑም ወንጌሎች በተደጋጋሚ ይገለበጡ የነበረ ሲሆን ይህ ደግሞ ክርስትና በፍጥነት እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ጥርጥር የለውም።

ፓፒረስ ራይላንድስ የፊተኛውና የኋለኛው ገጽ

ፓፒረስ ራይላንድስ በዛሬው ጊዜ ላለነው ጠቃሚ የሆነበት ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፍ ምን ያህል አስተማማኝ በሆነ መልኩ ወደ ዘመናችን እንደተላለፈ ስለሚያሳይ ነው። ይህ ቁራጭ ከዮሐንስ ወንጌል ላይ ጥቂት ቁጥሮችን ብቻ የያዘ ቢሆንም እንኳ በቁራጩ ላይ ያለው ሐሳብ በዛሬው ጊዜ እኛ ካለን መጽሐፍ ቅዱስ ጋር በጣም ተመሳሳይ ነው ማለት ይቻላል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናቱ ሁሉ በተደጋጋሚ ሲገለበጥ የኖረ ቢሆንም እንዳልተለወጠ ፓፒረስ ራይላንድስ ያሳያል።

እርግጥ ነው፣ የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፍ በትክክል እንደተላለፈ ከሚያረጋግጡት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ቁርጥራጮችና ጥንታዊ ጽሑፎች መካከል ፓፒረስ ራይላንድስ ተብሎ የሚጠራው የዮሐንስ ወንጌል ቁራጭ አንዱ ብቻ ነው። ዌርነር ኬለር ዘ ባይብል አዝ ሂስትሪ በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “እነዚህ [በእጅ የተገለበጡ] ጥንታዊ ጽሑፎች፣ በዛሬው ጊዜ ባሉን መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ ያለው ሐሳብ ትክክለኛና እምነት የሚጣልበት ስለመሆኑ ለሚነሱ ጥያቄዎች በሙሉ ከሁሉ ይበልጥ አሳማኝ የሆነ መልስ ይሰጣሉ።”

እውነት ነው፣ ክርስቲያኖች እምነታቸው የተመሠረተው በአርኪኦሎጂ ግኝቶች ላይ አይደለም። ክርስቲያኖች “ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ” እንደሆኑ ያምናሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ያም ሆኖ በዋጋ ሊተመን የማይችለው ይህ ጥንታዊ ሀብት “የይሖዋ ቃል . . . ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ምንጊዜም ትክክል መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው!—1 ጴጥሮስ 1:25

^ አን.8 ማኑስክሪፕትስ ኦቭ ዘ ግሪክ ባይብል የተሰኘው መጽሐፍ እንደገለጸው ፔሊዮግራፊ “ጥንታዊ ጽሑፎችን የሚያጠና የሳይንስ መስክ ነው።” ጊዜ እያለፈ ሲሄድ የእጅ ጽሑፍ አጣጣል ይለወጣል። በመሆኑም የተጻፉበት ዘመን በአስተማማኝ ሁኔታ የታወቁ ሰነዶችን፣ አዲስ በተገኘው ጥንታዊ ቅጂ ላይ ካለው የእጅ ጽሑፍ አጣጣል ጋር በማነጻጸርና በመካከላቸው ያለውን የእጅ ጽሑፍ ልዩነት በማየት አዲስ የተገኘውን ጥንታዊ ቅጂ ዕድሜ ማወቅ ይቻላል።