በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ንድፍ አውጪ አለው?

የድመት ምላስ

የድመት ምላስ

 የቤት ድመቶች ራሳቸውን በማስዋብ ልማዳቸው ይታወቃሉ። ነቅተው ካሉበት ጊዜ ውስጥ 24 በመቶውን ራሳቸውን በማስዋብ ሊያሳልፉ ይችላሉ። ይህ የጽዳት ልማዳቸው ውጤታማ የሆነው ምላሳቸው ባለው አስደናቂ ንድፍ የተነሳ ነው።

 እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ የድመት ምላስ 290 ፓፒላዎች ወይም ወደ ኋላ የተቀሰሩ እብጥ እብጥ ያሉ ነገሮች አሉት፤ እነዚህ ፓፒላዎች የጥፍር ያህል ጥንካሬ አላቸው። እያንዳንዱ ፓፒላ የተቦረቦረ ጎን ያለው ሲሆን ድመቷ ምላሷን ወደ አፏ ስታስገባ ወዲያውኑ ምራቅ ይይዛል። ድመቷ ፀጉሯን ስትልስ ፓፒላዎቹ የፀጉሩ ሥር ድረስ ሄደው ቆዳው ላይ ሲደርሱ ምራቁን ይለቁታል።

ፓፒላዎች በአጉሊ መነጽር ሲታዩ

 የድመት ምላስ በየቀኑ 48 ሚሊ ሊትር የሚሆን ምራቅ ወደ ቆዳዋና ወደ ፀጉሯ ያደርሳል። የድመት ምራቅ በካይ ንጥረ ነገሮችን የሚያሟሙ ኢንዛይሞች አሉት። በተጨማሪም ምራቁ ሲተን ድመቷን ያቀዘቅዛታል፤ ድመት ከአካሏ ከምታስወጣው ሙቀት አንድ አራተኛው የሚወገደው በዚህ መንገድ ነው። ይህ ደግሞ ለድመቷ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ድመቶች ላብ የሚያመነጭ ብዙ ዕጢ የላቸውም።

 ፓፒላው የተቆጣጠረ ፀጉር ካጋጠመው ወደ ፀጉሩ ሥር ይበልጥ ጠልቆ ይገባል፤ በዚህ ጊዜ ከፍተኛ ጉልበት ስለሚኖረው የተቆጣጠረውን ፀጉር ጎትቶ መፍታት ይችላል። ድመቷ ራሷን ስትልስ ፓፒላዎቹ ቆዳዋንም ሊያነቃቁት ይችላሉ። ተመራማሪዎች የድመት ምላስ ያለውን ንድፍ በመኮረጅ ለሙከራ የሚሆን የፀጉር ማበጠሪያ ሠርተዋል። ይህ ማበጠሪያ እንደ ሌሎች ማበጠሪያዎች ብዙ ጉልበት መጠቀም ሳያስፈልግ ፀጉሩን ያበጥረዋል፤ ለማጽዳት ቀላል ነው፤ እንዲሁም የተቆጣጠረ ፀጉርን ይፈታል። ተመራማሪዎቹ የድመት ምላስ ያለውን ንድፍ ማጥናት ፀጉራማ የሆኑ ቁሳቁሶችን በተሻለ መንገድ ለማጽዳት የሚያስችሉ ዘዴዎችን ለመፍጠር እንደሚረዳ ያምናሉ። በተጨማሪም በፀጉር የተሸፈነ ቆዳ ላይ በተሻለ መንገድ ቅባት ወይም መድኃኒት ለመቀባት እንደሚያስችል ያስባሉ።

 ታዲያ ምን ይመስልሃል? የድመት ምላስ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?