በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

ማርቆስ 11:24—“የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ”

ማርቆስ 11:24—“የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ”

 “ስለዚህ እላችኋለሁ፣ በጸሎት የምትጠይቁትንና የምትለምኑትን ነገር ሁሉ እንዳገኛችሁት አድርጋችሁ እመኑ፤ ደግሞም ታገኙታላችሁ።”—ማርቆስ 11:24 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “ስለዚህ እላችኋለሁ፣ የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፣ ይሆንላችሁማል።”—ማርቆስ 11:24 የ1954 ትርጉም

የማርቆስ 11:24 ትርጉም

 ኢየሱስ እነዚህን ቃላት በመናገር ተከታዮቹ በጸሎት ኃይል ላይ ጠንካራ እምነት ሊኖራቸው እንደሚገባ አሳስቧቸዋል። አምላክ ጸሎታቸውን እንደሚሰማ ብቻ ሳይሆን መልስ እንደሚሰጣቸውም አረጋግጦላቸዋል። ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ከልቡ የሚጸልይ ሰው ጸሎቱ እንደሚመለስለት እርግጠኛ መሆን ይችላል። እንዲያውም በጸሎት የጠየቀውን ነገር ያኔውኑ ያገኘው ያህል ነው።

 ኢየሱስ በእምነት መጸለይ ያለውን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። አንድ ሰው ሲጸልይ “በልቡ ሳይጠራጠር የተናገረው ነገር እንደሚፈጸም” ሊያምን እንደሚገባ ተናግሯል። (ማርቆስ 11:23) ለምን? ምክንያቱም የሚጠራጠር ሰው “ከይሖዋ a አንዳች ነገር አገኛለሁ ብሎ መጠበቅ” አይችልም።—ያዕቆብ 1:5-8

 እምነት ያለው ሰው በተደጋጋሚ ይጸልያል። (ሉቃስ 11:9, 10፤ ሮም 12:12) በዚህ መንገድ፣ በጸሎት የጠየቀውን ነገር ከልቡ እንደሚፈልገው እንዲሁም አምላክ ጸሎቱን መመለስ እንደሚችል በእርግጥ እንደሚያምን ያሳያል። እርግጥ፣ አምላክ ጸሎቱን እሱ ከጠበቀው በተለየ መንገድ ወይም በተለየ ጊዜ ሊመልስለት እንደሚችል ይገነዘባል።—ኤፌሶን 3:20፤ ዕብራውያን 11:6

 ይሁንና ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ማንኛውም ሰው አምላክን በጸሎት የጠየቀውን ነገር ሁሉ እንደሚያገኝ መጠበቅ እንደሚችል የሚያመለክት አይደለም። ኢየሱስ ይህን ሐሳብ የተናገረው የእምነት ሰዎች ለሆኑት ለተከታዮቹ ነው፤ እነዚህ ሰዎች ይሖዋ አምላክን ተቀባይነት ባለው መንገድ ለማምለክ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ እያደረጉ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ የሚሰማው ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ መንገድ የቀረቡ ጸሎቶችን ብቻ እንደሆነ ይናገራል። (1 ዮሐንስ 5:14) ሆን ብለው የእሱን መሥፈርቶች የሚጥሱ እንዲሁም መጥፎ ነገሮችን ፈጽመው ንስሐ የማይገቡ ሰዎች የሚያቀርቡትን ጸሎት አይሰማም። (ኢሳይያስ 1:15፤ ሚክያስ 3:4፤ ዮሐንስ 9:31) አምላክ ምን ዓይነት ጸሎቶችን እንደሚሰማ ለማወቅ ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።

የማርቆስ 11:24 አውድ

 ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ሊያጠናቅቅ በተቃረበበት ወቅት በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት ማዳበር ያለውን አስፈላጊነት ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸዋል። ይህን ሐሳብ በምሳሌ አስደግፎ አስተምሯቸዋል። ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዘ ሳለ ያለጊዜዋ ቅጠል ያወጣች የበለስ ዛፍ ተመለከተ። ሆኖም ዛፏ ፍሬ ስላልነበራት ኢየሱስ ረገማት። (ማርቆስ 11:12-14) ዛፏ የነበራት አሳሳች መልክ የጥንቱ የእስራኤል ብሔር የነበረበትን ሁኔታ ያሳያል፤ እስራኤላውያን ይሖዋን የሚያመልኩ ቢመስሉም እምነት አልነበራቸውም። (ማቴዎስ 21:43) ብዙም ሳይቆይ ዛፏ ደረቀች፤ ይህም እምነት የለሽ የሆኑት እስራኤላውያን በቅርቡ የሚያጋጥማቸውን ጥፋት ያመለክታል።—ማርቆስ 11:19-21

 በአንጻሩ ግን፣ ኢየሱስ ተከታዮቹ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ለመወጣት አልፎ ተርፎም አስደናቂ ነገሮችን ለማከናወን የሚያስችል እምነት ማዳበር እንደሚችሉ እርግጠኛ ነበር። (ማርቆስ 11:22, 23) ኢየሱስ ጸሎትን አስመልክቶ የሰጣቸው ምክር ወቅታዊ ነበር፤ ምክንያቱም የተከታዮቹ እምነት ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ይፈተናል። የኢየሱስ መሞት እንዲሁም በአገልግሎታቸው የሚያጋጥማቸው ተቃውሞ እምነታቸውን ይፈትነዋል። (ሉቃስ 24:17-20፤ የሐዋርያት ሥራ 5:17, 18, 40) በዛሬው ጊዜ ያሉ የኢየሱስ ተከታዮችም በአምላክና በጸሎት ኃይል ላይ እምነት ካላቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መወጣት ይችላሉ።—ያዕቆብ 2:26

 የማርቆስ መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።

a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።