በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

ኢሳይያስ 40:31—‘ይሖዋን ተስፋ የሚያደርጉ ኃይላቸው ይታደሳል’

ኢሳይያስ 40:31—‘ይሖዋን ተስፋ የሚያደርጉ ኃይላቸው ይታደሳል’

 “ይሖዋን ተስፋ የሚያደርጉ ግን ኃይላቸው ይታደሳል። እንደ ንስር በክንፍ ወደ ላይ ይወጣሉ። ይሮጣሉ፣ አይዝሉም፤ ይሄዳሉ፣ አይደክሙም።”—ኢሳይያስ 40:31 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፣ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፣ አይደክሙም።”—ኢሳይያስ 40:31 የ1954 ትርጉም

የኢሳይያስ 40:31 ትርጉም

 ይሖዋ a አምላክ አገልጋዮቹ የሚያጋጥማቸውን ማንኛውንም ችግር ለመወጣት ወይም በጽናት ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቷል።

 ‘ይሖዋን ተስፋ የሚያደርጉ ኃይላቸው ይታደሳል።’ አምላክ ሕዝቦቹን ለመርዳት ችሎታውም ሆነ አቅሙ እንዳለው ተስፋ የሚያደርጉ ማለትም የሚተማመኑ ሰዎች እሱ እንደሚረዳቸው እርግጠኛ መሆን ይችላሉ። (ምሳሌ 3:5, 6) አምላክ አገልጋዮቹን የሚያበረታበት አንዱ መንገድ ቅዱስ መንፈሱን በመስጠት ነው።—ሉቃስ 11:13

 “እንደ ንስር በክንፍ ወደ ላይ ይወጣሉ።” ይህ አገላለጽ አምላክ የሚሰጠው ኃይል በአንድ ሰው ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ጥሩ አድርጎ ይገልጻል። አንድ ንስር ከፍ ብሎ ለመብረርና ለመንሳፈፍ ሞቃት አየር ወደ ላይ የሚወጣባቸውን ተርማል በመባል የሚጠሩ መስመሮች ይጠቀማል። ንስሩ ተርማል ያለበትን መስመር ካገኘ በኋላ ክንፉን ዘርግቶ እዚያ መስመር ላይ ሲያንዣብብ አየሩ እየገፋ ወደ ላይ ይዞት ይወጣል። በዚህ መንገድ ከአንዱ ተርማል ወደ ሌላው ተርማል በመሸጋገር ለሰዓታት በአየር ላይ መቆየት ይችላል። እንዲህ ያለ ዘዴ ተጠቅሞ መብረሩ ብዙ ኃይል ማውጣት ሳያስፈልገው ወደፈለገበት ቦታ ለመድረስ ያስችለዋል።

 “ይሮጣሉ፣ አይዝሉም።” በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙን ችግሮች በአካላዊም ሆነ በስሜታዊ ሁኔታ እንድንዝል ያደርጉናል። አምላክ የሚሰጠን ኃይል ግን በጽናት እንድንቀጥል ይረዳናል። ፈታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ የሚያስችል ብርታት ይሰጠናል። ከባድ ሁኔታዎችን በጽናት የተቋቋመው ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ።”—ፊልጵስዩስ 4:13

የኢሳይያስ 40:31 አውድ

 አምላክ ነቢዩ ኢሳይያስ በመንፈስ ተመርቶ እነዚህን ቃላት እንዲጽፍ ያነሳሳው በስምንተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ነው። ይህ ጥቅስ ለሁሉም የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች የሚሠራ ቢሆንም ይሖዋ እነዚህን ቃላት በዋነኝነት ያጻፈው ወደ ባቢሎን ተወስደው ለሰባ ዓመታት በግዞት የሚቆዩትን አይሁዳውያን ለማበረታታት ሳይሆን አይቀርም። አይሁዳውያኑ ከግዞት ወደ ትውልድ አገራቸው ሲመለሱ አምላክ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ ተመልክተዋል። (ኢሳይያስ 40:1-3) በ537 ዓ.ዓ. ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም ያደረጉትን ረጅምና አስቸጋሪ ጉዞ b በተሳካ ሁኔታ እንዲያጠናቅቁ አምላክ ኃይል ሰጥቷቸዋል።—ኢሳይያስ 40:29

a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው።—መዝሙር 83:18

b አይሁዳውያኑ የተጓዙበት መንገድ 1,600 ኪሎ ሜትር ገደማ ሳይሆን አይቀርም።