በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ኢየሱስ ያድናል—እንዴት?

ኢየሱስ ያድናል—እንዴት?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 ኢየሱስ ሕይወቱን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ በመስጠት ታማኝ የሰው ልጆች የሚድኑበትን መንገድ ከፍቷል። (ማቴዎስ 20:28) በዚህም ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን “የዓለም አዳኝ” በማለት ይጠራዋል። (1 ዮሐንስ 4:14) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “መዳን በሌላ በማንም አይገኝም፤ ምክንያቱም ልንድንበት የምንችል ከሰማይ በታች ለሰዎች የተሰጠ ሌላ ስም የለም።”—የሐዋርያት ሥራ 4:12

 ኢየሱስ በእሱ ለሚያምን “ሰው ሁሉ ሲል ሞትን ቀምሷል።” (ዕብራውያን 2:9፤ ዮሐንስ 3:16) ከዚያም ‘አምላክ ከሞት አስነስቶት’ መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ ወደ ሰማይ ተመልሷል። (የሐዋርያት ሥራ 3:15) በመሆኑም ኢየሱስ “[ለሰው ልጆች] ለመማለድ ሁልጊዜ ሕያው ሆኖ ስለሚኖር በእሱ አማካኝነት ወደ አምላክ የሚቀርቡትን ፈጽሞ ሊያድናቸውም ይችላል።”—ዕብራውያን 7:25

የኢየሱስ አማላጅነት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

 ሁላችንም ኃጢአተኞች ነን። (ሮም 3:23) ኃጢአት ከአምላክ ያራቀን ሲሆን ወደ ሞትም ይመራናል። (ሮም 6:23) ይሁን እንጂ ኢየሱስ በእሱ ቤዛዊ መሥዋዕት ለሚያምኑት “ጠበቃ” ሆኖ ያገለግላል። (1 ዮሐንስ 2:1፣ ግርጌ) አምላክ ጸሎታቸውን እንዲሰማቸውና ለሠሩት ኃጢአት በቤዛው አማካኝነት ይቅርታ እንዲያደርግላቸው ኢየሱስ ለሰው ልጆች ይማልድላቸዋል። (ማቴዎስ 1:21፤ ሮም 8:34) ኢየሱስ የሚያቀርበው ምልጃ ከአምላክ ፈቃድ ጋር ስለሚስማማ አምላክ ይቀበለዋል። ደግሞም አምላክ ኢየሱስን ወደ ምድር የላከው “ዓለም በእሱ አማካኝነት እንዲድን ነው።”—ዮሐንስ 3:17

ለመዳን የሚያስፈልገን በኢየሱስ ማመን ብቻ ነው?

 አይደለም። ለመዳን በኢየሱስ ማመናችን አስፈላጊ ቢሆንም ከዚያ የበለጠ ነገር ማድረግ ይኖርብናል። (የሐዋርያት ሥራ 16:30, 31) መጽሐፍ ቅዱስ “አካል ያለመንፈስ የሞተ እንደሆነ ሁሉ እምነትም ያለሥራ የሞተ ነው” ይላል። (ያዕቆብ 2:26) ለመዳን የሚከተሉትን ነገሮች ማድረግ ያስፈልገናል፦

  •   ስለ ኢየሱስ እና ስለ አባቱ ስለ ይሖዋ መማር።—ዮሐንስ 17:3

  •   በይሖዋና በኢየሱስ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር።—ዮሐንስ 12:44፤ 14:1

  •   ይሖዋና ኢየሱስ የሰጡንን ትእዛዛት በማክበር እምነት እንዳለን ማሳየት። (ሉቃስ 6:46፤ 1 ዮሐንስ 2:17) ኢየሱስ፣ የሚድኑት “ጌታ ሆይ” የሚሉት ሳይሆኑ ‘በሰማያት ያለውን የአባቱን ፈቃድ የሚያደርጉ ሰዎች ብቻ’ እንደሆኑ ተናግሯል።—ማቴዎስ 7:21

  •   አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም ምንጊዜም እምነት እንዳለን ማሳየት። ኢየሱስ ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር “እስከ መጨረሻው የጸና ግን ይድናል” ብሏል።—ማቴዎስ 24:13