በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ቃለ ምልልስ | ፍሬድሪክ ዱሙላ

‘ፈጣሪ ስለ መኖሩ እርግጠኛ ሆንኩ’

‘ፈጣሪ ስለ መኖሩ እርግጠኛ ሆንኩ’

ፍሬድሪክ ዱሙላ፣ ቤልጅየም በሚገኘው ጌንት ዩኒቨርስቲ በፋርማሲ የጥናት ዘርፍ ከአሥር ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ ሠርቷል። በአንድ ወቅት አምላክ የለሽ ነበር። በኋላ ግን ሕይወት የተገኘው በፍጥረት እንደሆነ አመነ። አሁን የይሖዋ ምሥክር የሆነውን ፍሬድሪክን ንቁ! ስለ ሥራውና ስለ እምነቱ አነጋግሮታል።

ሃይማኖት በልጅነት ሕይወትህ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ አለ?

አዎ። እናቴ የሮማ ካቶሊክ እምነት ተከታይ ነበረች። ስለ መስቀል ጦርነትና ስለ ኢንክዊዚሽን ካነበብኩ በኋላ ግን ሃይማኖት በጣም ስላስጠላኝ ከሃይማኖት ፈጽሞ ለመራቅ ፈለግኩ። ከክርስትና ውጭ ስላሉ ሃይማኖቶችም አንብቤ ነበር፤ ይሁን እንጂ እነሱም ምንም የተሻለ ነገር የላቸውም። አሥራ አራት ዓመት ሲሞላኝ በሃይማኖት ውስጥ ተንሰራፍቶ የሚታየው ምግባረ ብልሹነት አምላክ እንደሌለ የሚያሳይ በቂ ማስረጃ እንደሆነ አሰብኩ። በመሆኑም በትምህርት ቤት ስለ ዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ስማር ሕይወት የተፈጥሯዊ ክስተት ውጤት እንደሆነ ደመደምኩ።

ወደ ሳይንስ ማዘንበል የጀመርከው እንዴት ነው?

ሰባት ዓመት ሲሆነኝ አጉሊ መነጽር ተሰጠኝ፤ ካሉኝ መጫወቻዎች ሁሉ አስበልጬ እወደው ነበር። ብዙ ነገሮች እመለከትበት ነበር፤ ለምሳሌ እንደ ቢራቢሮ ያሉ አስደናቂ ነፍሳት ላይ ምርምር ለማድረግ እጠቀምበት ነበር።

ስለ ሕይወት አመጣጥ የማወቅ ፍላጎት ያደረብህ እንዴት ነው?

ሃያ ሁለት ዓመት ሲሆነኝ የይሖዋ ምሥክር ከሆነች አንዲት የሳይንስ ሊቅ ጋር ተገናኘሁ። ሕይወትን የፈጠረው አምላክ እንደሆነ ታምን ነበር። ይህ ያልጠበቅኩት ነገር ሆነብኝ። እምነቷ መሠረተ ቢስ እንደሆነ በቀላሉ ላስረዳት እንደምችል ተሰማኝ። ይሁን እንጂ ለጥያቄዎቼ አሳማኝ መልሶች ስትሰጠኝ በጣም ተደነቅኩ። ሰዎች በአምላክ ሊያምኑ የቻሉት ምን ማስረጃ ቢኖራቸው ነው የሚለውን ጉዳይ ለማወቅ ጉጉት አደረብኝ።

ከጥቂት ወራት በኋላ ስለ ሕክምና ጉዳዮች ጥሩ እውቀት ካለው ሌላ የይሖዋ ምሥክር ጋር ተገናኘሁ። ሰዎች በአምላክ የሚያምኑት ለምን እንደሆነ የማወቅ ፍላጎት ስለነበረኝ የሚያምንበትን ነገር አስመልክቶ ሊያስረዳኝ እንደሚችል ሲነግረኝ ጥያቄውን ተቀበልኩ። ምክንያቱም ከመታለል ላድነው ፈልጌ ነበር።

ታዲያ ተሳስቶ እንደነበረ አሳመንከው?

አላሳመንኩትም። ስለ ሕይወት አመጣጥ በሚናገሩ የተለያዩ ንድፈ ሐሳቦች ላይ ምርምር ማድረግ ጀመርኩ። የሚገርመው ውስብስብ እንዳልሆነ ተደርጎ የሚታሰብ አንድ ሴል እንኳ በጣም የተራቀቀ ከመሆኑ የተነሳ በራሱ ሊገኝ እንደማይችል አንዳንድ እውቅ የሳይንስ ሊቃውንት መናገራቸውን ተገነዘብኩ። አንዳንዶቹ  የሳይንስ ሊቃውንት እነዚህ ሴሎች የመጡት ከጠፈር እንደሆነ ያስባሉ። ሕይወት ስለተገኘበት መንገድ ያላቸው እምነት በጣም የተለያየ ነው።

ሁሉንም የሚያስማማ ነጥብ አለ?

የሚገርመው፣ ብዙ የሳይንስ ሊቃውንት ሕይወት ያላቸው ነገሮች በተፈጥሯዊ ክስተቶች አማካኝነት በሆነ መንገድ ሕይወት ከሌላቸው ነገሮች እንደተገኙ ይስማማሉ። እኔም ‘ሕይወት ያለፈጣሪ ሊገኝ የቻለው እንዴት እንደሆነ ማስረዳት ካልቻሉ በዚህ መንገድ ተገኘ ብለው እንዴት እርግጠኛ ሊሆኑ ይችላሉ?’ ብዬ አሰብኩ። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሕይወት አመጣጥ የሚናገረውን ማንበብ ጀመርኩ።

ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ድምዳሜ ላይ መድረስ ቻልክ?

ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ባወቅኩ መጠን ስለ እውነተኛነቱ ይበልጥ እርግጠኛ ሆንኩ። ለምሳሌ፣ የሳይንስ ሊቃውንት ጽንፈ ዓለም መጀመሪያ እንዳለው የሚያሳይ ማስረጃ ያገኙት በቅርቡ ነው። ይሁን እንጂ ከ3,500 ዓመታት በፊት የተጻፈው የመጽሐፍ ቅዱስ የመክፈቻ ቁጥር “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” * ይላል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሳይንሳዊ ጉዳዮች በሚናገርበት ቦታ ሁሉ ትክክለኛ መረጃ እንደሚያስተላልፍ ተገንዝቤያለሁ።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሳይንሳዊ ጉዳዮች በሚናገርበት ቦታ ሁሉ ትክክለኛ መረጃ እንደሚያስተላልፍ ተገንዝቤያለሁ

ስለ ሳይንስ ያለህ እውቀት በአምላክ ማመን አስቸጋሪ እንዲሆንብህ አድርጓል?

አላደረገብኝም። በአምላክ ማመን ስጀምር በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሦስተኛ ዓመት የሳይንስ ተማሪ ነበርኩ። ዛሬም ቢሆን ሕይወት ስላላቸው ነገሮች ባጠናሁ መጠን ፈጣሪ ስለ መኖሩ ይበልጥ እርግጠኛ እንድሆን ያደርገኛል።

አንድ ምሳሌ ልትሰጠን ትችላለህ?

አዎ። መድኃኒቶችና መርዛማ ንጥረ ነገሮች ሕይወት ባላቸው ነገሮች ላይ ስለሚያስከትሉት ውጤት አጥንቻለሁ። በጣም የሚያስደንቀኝ አንጎላችን ከጎጂ ንጥረ ነገሮችና ከባክቴሪያዎች ራሱን የሚጠብቅበት መንገድ ነው። ደማችን ወደ አንጎላችን ሴሎች እንዳይገባ የሚያግድ ነገር አለ።

ታዲያ ይህ የሚያስደንቀው ለምንድን ነው?

ተመራማሪዎች በደም ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮች ከአንጎልና ከህብለ ሰረሰር (አከርካሪ ላይ ያሉ የነርቭ ሴሎች) በስተቀር ወደ ሁሉም የሰውነታችን ክፍሎች እንደሚደርሱ ከአንድ መቶ ዓመት በፊት ደርሰውበታል። ይህ በጣም አስደንቆኛል፤ ምክንያቱም በአንጎል ውስጥ ለሚገኝ ለእያንዳንዱ ሴል ደም የሚያደርሱ በጣም ጥቃቅን የሆኑ የደም ሥሮች አሉ። ሁሉም የአንጎል ሴሎች ቆሻሻ የሚያስወግዱት እንዲሁም ምግብና ኦክስጅን የሚያገኙት በደም አማካኝነት ነው። ታዲያ ደማችን ወደ አንጎላችን ሴሎች እንዳይገባ የተደረገው እንዴት ነው? ይህ ነገር ለበርካታ ዓመታት ሚስጥር ሆኖ ቆይቷል።

ደማችን ወደ አንጎላችን ሴሎች የማይገባው ለምንድን ነው?

በአጉሊ መነጽር ብቻ ሊታዩ የሚችሉ ጥቃቅን የደም ሥሮች በውስጣቸው የያዙትን ነገር ወደ ውጪ ማስወጣትም ሆነ የውጪውን ማስገባት ከማይችሉ የፕላስቲክ ቱቦዎች የተለዩ ናቸው። የደም ሥሮቻችን ግድግዳዎች ከሴል የተሠሩ ናቸው። እነዚህ ሴሎች የተለያዩ ንጥረ ነገሮችንና ባክቴሪያዎችን በመካከላቸው እንዲሁም በውስጣቸው ያስተላልፋሉ። በአንጎላችን ውስጥ ያሉት የደም ሥሮች ግን ለየት ባሉ ሴሎች የተገነቡ ናቸው። እርስ በርሳቸው ተጠባብቀው የተቀመጡ ናቸው። እነዚህ ሴሎችም ሆኑ በመካከላቸው ያለው ርቀት ጠባብ መሆኑ በጣም የሚያስደንቅ ነው። እንደ ኦክስጅን፣ ካርቦን ዳይኦክሳይድና ግሉኮስ ያሉ የተወሰኑ ነገሮች ብቻ ከደም ሥር ወደ አንጎል ወይም ከአንጎል ወደ ደም ሥር ቁጥጥር እየተደረገባቸው ይተላለፋሉ፤ ይህ ሂደት በጣም ውስብስብ ነው። ሌሎች ንጥረ ነገሮች፣ ፕሮቲኖችና ሴሎች ግን ሊገቡ አይችሉም። ስለዚህ ደማችን ወደ አንጎላችን ሴሎች እንዳይገባ የሚታገድበት ሂደት የሚሠራው በሞለኪውል ደረጃ ነው፤ በመሆኑም ማለፍ የሚችሉት ንጥረ ነገሮች የሚለዩት በመጠናቸው እንዲሁም በኬሚካላዊና በኤሌክትሪክ ባሕርያቸው ነው። እንዲህ ያለው ንድፍ እንዲሁ በአጋጣሚ የተገኘ ነው ማለት የማይመስል ነገር ነው።