በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የክርስቲያኖች ጥምቀት የመጣው ከአይሁዳውያን የመንጻት ሥርዓት ነው?

የክርስቲያኖች ጥምቀት የመጣው ከአይሁዳውያን የመንጻት ሥርዓት ነው?

የክርስቲያኖች ጥምቀት የመጣው ከአይሁዳውያን የመንጻት ሥርዓት ነው?

መጥምቁ ዮሐንስ ስለ “ንስሓ ጥምቀት” ሰብኳል። ኢየሱስም ተከታዮቹ ሌሎችን ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉና እንዲያጠምቁ አዟል።—ማርቆስ 1:4፤ ማቴዎስ 28:19

መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያናዊ ጥምቀት ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ በመጥለቅ መከናወን እንዳለበት ይጠቁማል። ጂሰስ ኤንድ ሂዝ ዎርልድ የተሰኘው መጽሐፍ “ጥንት በነበሩትም ሆነ በዘመናችን ባሉት ሃይማኖቶች ዘንድ እንዲሁም በተለያዩ አገሮችና ባሕሎች ውስጥ ተመሳሳይ የሆነ ልማድ ይስተዋላል” ብሏል። ቀጠል አድርጎም “የክርስቲያኖች ጥምቀት የመጣው . . . ከአይሁድ እምነት ነው” ሲል ገልጿል። ይህ አባባል ምን ያህል ትክክል ነው?

አይሁዳውያን የመንጻት ሥርዓት የሚያከናውኑባቸው ገንዳዎች

አርኪኦሎጂስቶች የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ በሚገኝበት ጉብታ ላይ የመንጻት ሥርዓት ይከናወንባቸው የነበሩ ወደ 100 የሚጠጉ ገንዳዎች በቁፋሮ ማግኘት ችለዋል። እነዚህ ገንዳዎች በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊትና በአንደኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የተሠሩ እንደሆኑ ታውቋል። በሁለተኛው ወይም በሦስተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ እንደተጻፈ የሚገመት በአንድ ምኩራብ ውስጥ የተገኘ ጽሑፍ እነዚህ ገንዳዎች የተዘጋጁት ይህን የመንጻት ሥርዓት ማከናወን “ለሚፈልጉ እንግዶች” መሆኑን ይገልጻል። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሩሳሌም ውስጥ ባለጠጎችና የክህነት ዝርያ ያላቸው ቤተሰቦች ይኖሩበት በነበረው አካባቢ ሌሎች ገንዳዎች ተገኝተዋል፤ እያንዳንዱ ቤት ሃይማኖታዊ የመንጻት ሥርዓት የሚካሄድበት የግል መታጠቢያ ነበረው ማለት ይቻላል።

መታጠቢያ ገንዳዎቹ በአራት ማዕዘን ቅርጽ ከድንጋይ ተፈልፍለው የወጡ ወይም ደግሞ መሬቱ ተቆፍሮ ግድግዳውና ወለሉ በጡብ አሊያም በድንጋይ ከተገነባ በኋላ ውኃው እንዳይወጣ ውስጣቸው የተለሰኑ ናቸው። አብዛኞቹ ገንዳዎች 1.8 በ2.7 ሜትር ስፋት አላቸው። የዝናብ ውኃ ወደ ገንዳዎቹ እንዲገባ ለማድረግ ቦይ ተሠርቶላቸዋል። የውኃው ጥልቀት 1.2 ሜትር ያህል በመሆኑ አንድ ሰው ትንሽ ሸብረክ ካለ ሙሉ በሙሉ መጥለቅ ይችላል። ወደ ገንዳው የሚያስገቡት ደረጃዎች አንዳንዴ ዝቅ ብሎ በተሠራ ግንብ ለሁለት እንዲከፈሉ ይደረጋል። ንጹሕ ያልሆነ አንድ ግለሰብ በአንድ በኩል ባለው ደረጃ ወደ ውኃው ገብቶ ከታጠበ በኋላ በሌላኛው በኩል ከገንዳው ይወጣል፤ ይህም ማንኛውንም ብክለት ለማስወገድ ይረዳል ተብሎ ይታሰባል።

አይሁዳውያን እነዚህን መታጠቢያዎች ሃይማኖታዊ የመንጻት ሥርዓት ለማከናወን ይጠቀሙባቸው ነበር። ይህ ምንን ይጨምራል?

መንጻትን በተመለከተ የወጣው ሕግና የአይሁድ ልማድ

የሙሴ ሕግ፣ የአምላክ ሕዝቦች መንፈሳዊም ሆነ አካላዊ ንጽሕናቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው ጎላ አድርጎ ይገልጻል። እስራኤላውያንን ሊያረክሷቸው የሚችሉ የተለያዩ ሁኔታዎች የነበሩ ሲሆን ሰውነታቸውን በመታጠብና ልብሳቸውን በማጠብ ራሳቸውን ማንጻት ነበረባቸው።—ዘሌዋውያን 11:28፤ 14:1-9፤ 15:1-31፤ ዘዳግም 23:10, 11

ይሖዋ አምላክ ፍጹም ንጹሕና ቅዱስ ነው። በመሆኑም ካህናትና ሌዋውያን ለማገልገል ወደ መሠዊያው በሚቀርቡበት ጊዜ እንዳይሞቱ እጃቸውንና እግራቸውን መታጠብ ነበረባቸው።—ዘፀአት 30:17-21

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ፣ የአይሁድ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ሌዋውያን ያልሆኑ ሰዎችም እንደ ካህናቱ ዓይነት የመንጻት ልማድ እንዲያከናውኑ ይጠብቅባቸው እንደነበር ምሑራን ያምናሉ። ኤሴናውያንም ሆኑ ፈሪሳውያን ሃይማኖታዊውን የመንጻት ሥርዓት አዘውትሮ የመፈጸም ልማድ ነበራቸው። አንድ ጽሑፍ በኢየሱስ ዘመን የነበረውን ሁኔታ አስመልክቶ እንዲህ ብሏል:- “አንድ አይሁዳዊ ወደ ቤተ መቅደሱ ከመግባቱ፣ መሥዋዕት ከማቅረቡ፣ ካህኑ ከሚያቀርበው መሥዋዕት ተጠቃሚ ከመሆኑና በሌሎች ተመሳሳይ እንቅስቃሴዎች ከመካፈሉ በፊት ሃይማኖታዊ የመንጻት ሥርዓት ማከናወን ይጠበቅበት ነበር።” የታልሙዳውያን ጽሑፎች፣ የሚታጠቡት ሰዎች ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ መጥለቅ እንደነበረባቸው ይገልጻሉ።

ኢየሱስ ፈሪሳውያንን ድርቅ ባለው ሃይማኖታዊ የመንጻት ወጋቸው ምክንያት አውግዟቸዋል። ፈሪሳውያን ‘ዋንጫን፣ ማሰሮንና ሳሕንን’ እንደ ማጠብ ያሉትን ጨምሮ “የተለያዩ የመንጻት ሥርዓቶች” ነበሯቸው። ኢየሱስ፣ ፈሪሳውያን የራሳቸውን ወግ ለመጠበቅ ሲሉ የአምላክን ትእዛዝ እንደሚተላለፉ ተናግሯል። (ዕብራውያን 9:10፤ ማርቆስ 7:1-9፤ ዘሌዋውያን 11:32, 33፤ ሉቃስ 11:38-42) የትኛውም የሙሴ ሕግ አንድ ሰው ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ መጥለቅ እንዳለበት አይገልጽም።

ታዲያ የክርስቲያኖች ጥምቀት የመጣው ከአይሁዳውያን ሃይማኖታዊ የመንጻት ሥርዓት ነበር? በፍጹም!

የመንጻት ሥርዓትና የክርስቲያኖች ጥምቀት

እያንዳንዱ አይሁዳዊ፣ ሃይማኖታዊ የመንጻት ሥርዓቱን የሚያካሂደው ራሱ ነበር። ይሁንና ዮሐንስ ሲያከናውነው የነበረው ጥምቀት አይሁዳውያን ከሚያውቁት ሃይማኖታዊ የመንጻት ሥርዓት ጋር የሚመሳሰል አልነበረም። ዮሐንስ አጥማቂው በመባል መታወቁ ሲያከናውን የነበረው ጥምቀት የተለየ እንደነበር ይጠቁማል። እንዲያውም በአንድ ወቅት የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች “ለምን ታጠምቃለህ?” ብለው እንዲጠይቁት መልእክተኞችን ልከው ነበር።—ዮሐንስ 1:25

የሙሴ ሕግ አንድ አምላኪ የሚያረክስ ድርጊት በፈጸመ ቁጥር የመንጻት ሥርዓቱን መፈጸም እንዳለበት ይደነግጋል። ሆኖም ዮሐንስም ሆነ ከዚያ በኋላ የመጡት ክርስቲያኖች ሲያካሂዱት የነበረው ጥምቀት ከዚህ የተለየ ነበር። የዮሐንስ ጥምቀት ንስሐ መግባትንና ቀድሞ ሲከተሉት የነበረውን የስህተት ጎዳና እርግፍ አድርጎ መተውን ያመለክታል። ክርስቲያናዊ ጥምቀት ደግሞ አንድ ሰው ራሱን ለአምላክ መወሰኑን ለማሳየት ያገለግላል። ይህንንም የሚያደርገው በተደጋጋሚ ሳይሆን አንዴ ብቻ ነው።

በአይሁድ ካህናት መኖሪያ ቤቶችና በቤተ መቅደሱ አቅራቢያ ባሉት የሕዝብ መታጠቢያዎች ውስጥ ይከናወኑ የነበሩት ሃይማኖታዊ የመንጻት ሥርዓቶች ከውጭ ሲታዩ ካልሆነ በቀር ከክርስቲያናዊ ጥምቀት ጋር የሚያመሳስላቸው አንዳችም ነገር የለም። ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ በመጥለቅ የሚከናወኑት የእነዚህ ድርጊቶች ትርጉም ፈጽሞ የተለያየ ነው። ዚ አንከር ባይብል ዲክሽነሪ የተሰኘው የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት “በርካታ ምሑራን [አጥማቂው] ዮሐንስ በአካባቢው የሚደረገውን ማንኛውንም ዓይነት የጥምቀት ሥርዓት እንዳልተከተለ ወይም እንዳልኮረጀ ያምናሉ” በማለት ይገልጻል። እዚህ ላይ “በአካባቢው” የሚለው ቃል የሚያመለክተው የአይሁድን እምነት ነው። ይህ መዝገበ ቃላት ያሰፈረው ሐሳብ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ለሚከናወነው ጥምቀትም ይሠራል።

ክርስቲያናዊው ጥምቀት ‘ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የበጎ ሕሊና ልመናን’ ያመለክታል። (1 ጴጥሮስ 3:21 የ1954 ትርጉም) ይህ ጥምቀት አንድ ሰው የኢየሱስ ደቀ መዝሙር በመሆን ይሖዋን ለማገልገል ሙሉ በሙሉ ራሱን መወሰኑን ያመለክታል። ውኃ ውስጥ ሙሉ በሙሉ መጥለቁ እንዲህ ላለው ውሰና ተስማሚ ምሳሌ ነው። አንድ ሰው፣ ወደ ውኃው መግባቱ ለቀድሞ ሕይወቱ ሙት መሆኑን የሚያመለክት ሲሆን ከውኃው መውጣቱ ደግሞ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ሕያው መሆኑን ይጠቁማል።

ይሖዋ በዚህ ዓይነት መንገድ ራሳቸውን ወስነው ለሚጠመቁ ሰዎች በጎ ሕሊና ይሰጣቸዋል። ሐዋርያው ጴጥሮስ በመንፈስ አነሳሽነት ተገፋፍቶ ለእምነት አጋሮቹ “ጥምቀት . . . ያድናችኋል” ብሏቸዋል። ይህ ደግሞ የአይሁዳውያን የመንጻት ሥርዓት በምንም ዓይነት ሊያስገኝ የማይችለው ነገር ነው።