በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማየት ማመን ነው

ማየት ማመን ነው

ማየት ማመን ነው

“የአግኖስቲክ ፍልስፍና አራማጆች የክርስትና እምነትም ሆነ ሌሎች ሃይማኖቶች አምላክንና የወደፊቱን ሕይወት አስመልክተው የሚናገሯቸውን ነገሮች ትክክለኛነት ማረጋገጥ አይቻልም ብለው ያምናሉ። ወይም ፈጽሞ ማወቅ አይቻልም ባይባልም እንኳ ቢያንስ በአሁኑ ወቅት የሚታወቅ ነገር የለም።”—በርትራንድ ራስል የተባለ ፈላስፋ፣ 1953

“አግኖስቲክ” የሚለውን ቃል የፈጠረው ቶማስ ሃክስሊ የተባለ የሥነ እንስሳት ተመራማሪ ነው። በ1825 የተወለደው ይህ ሰው በቻርልስ ዳርዊን ዘመን የኖረ ሲሆን እሱም የዝግመተ ለውጥ ትምህርት ደጋፊ ነበር። በ1863 ሃክስሊ፣ “ክርስቲያኖች እንደሚሉት የሚወደንና ለእኛ የሚያስብ” አምላክ አለ ብሎ ለማመን የሚያስችል አንድም ማስረጃ እንዳላገኘ ጽፏል።

በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ በርካታ ሰዎች፣ በሚያዩት ነገር ብቻ እንደሚያምኑ በመግለጽ ተደማጭነት ያላቸውን የእነዚህን ሰዎች ስሜት ይጋራሉ። ምናልባትም ተጨባጭ ማስረጃ በሌለው አንድ አካል ወይም ነገር ላይ ማመን ሞኝነት ነው ሊሉ ይችላሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ አለ ብለን በጭፍን እንድናምን ይጠብቅብናል? በፍጹም! እንዲያውም ከዚህ ተቃራኒ የሆነ ነገር እንድናደርግ ያበረታታናል። መጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ በሌላቸው ነገሮች ማመን ሞኝነት እንደሆነ ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ “ተላላ ሰው ሁሉን ያምናል፤ አስተዋይ ግን ርምጃውን ያስተውላል” ይላል።—ምሳሌ 14:15

በአምላክ ስለማመንስ ምን ማለት ይቻላል? አምላክ ይወደናል እንዲሁም ያስብልናል ብሎ ማመን ይቅርና ፈጣሪ መኖሩን እንኳ የሚያሳይ ማስረጃ ይኖር ይሆን?

የአምላክ ባሕርያት በግልጽ ይታያሉ

ከመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች መካከል አንዱ የሆነው ጳውሎስ፣ ለአቴና ምሑራን ሲናገር አምላክ “ዓለምንና በውስጡ ያለውን ሁሉ [ፈጥሯል]” ብሏል። ጳውሎስ ተጠራጣሪ ለነበሩት አድማጮቹ፣ ፈጣሪ ለሰው ልጆች እንደሚያስብ የነገራቸው ከመሆኑም በላይ ‘አምላክ ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም’ ብሏቸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 17:24-27

ጳውሎስ፣ አምላክ ስለ መኖሩና ለሰብዓዊ ፍጡሮቹም የሚያስብ ስለ መሆኑ በእርግጠኝነት የተናገረው ለምንድን ነው? ጳውሎስ በሮም ከተማ ለነበሩት ክርስቲያን ባልንጀሮቹ በጻፈበት ወቅት አንዱን ምክንያት እንደሚከተለው በማለት ገልጿል:- “ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ . . . ከፍጥረቱ በግልጽ ይታያል።”—ሮሜ 1:20

የሚቀጥሉት ርዕሶች፣ አምላክ ከፈጠራቸው ነገሮች በግልጽ ማየት የምንችላቸውን ሦስት ባሕርያት ያብራራሉ። ቀጥሎ ያሉትን ምሳሌዎች ስትመረምር ‘እነዚህን የአምላክ ባሕርያት ማወቄ ምን ተጽዕኖ ያሳድርብኛል?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ አለ ብለን በጭፍን እንድናምን አይጠብቅብንም