በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሰሎሞን ደሴቶች የደረሰ የተፈጥሮ አደጋ

በሰሎሞን ደሴቶች የደረሰ የተፈጥሮ አደጋ

በሰሎሞን ደሴቶች የደረሰ የተፈጥሮ አደጋ

ሰኞ ዕለት ሚያዝያ 2, 2007 የሰሎሞን ደሴቶች የተወሰነ ክፍል በሬክተር መለኪያ 8.1 በደረሰ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ተመታ። ሞቃታማ የአየር ንብረት ያላቸው እነዚህ ደሴቶች ከአውስትራሊያ በስተ ሰሜን ምሥራቅ የሚገኙ ናቸው። በዚህ ወቅት በምዕራባዊ ክፍል የሚገኙትን ደሴቶች ያጥለቀለቀው ውኃ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ 52 ሰዎችን ለሕልፈተ ሕይወት የዳረገ ከመሆኑም ሌላ 6,000 ሰዎችን ያለ መጠለያ አስቀርቷል። አንዳንዶች እንደዘገቡት የውኃው ከፍታ 10 ሜትር ይደርሳል።

በዚህ የመሬት መንቀጥቀጥ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች መካከል አንዷ በጊዞ ደሴት ጠረፍ ላይ የምትገኘውና 7,000 ነዋሪዎች ያሏት የጊዞ ከተማ ናት። ይህች ከተማ የምትገኘው የመሬት መንቀጥቀጡ ከተቀሰቀሰበት ዋነኛ ቦታ (ኤፒሴንቴር) 45 ኪሎ ሜትር ርቃ ነው። በጊዞ ከተማ የሚገኘው አነስተኛ አባላት ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ በዚያ ምሽት የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ በዓል ለማክበር በጉጉት እየተጠባበቀ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 11:23-26) በዚያን ዕለት የማለዳዋ ፀሐይ ፍንትው ብላ የወጣች ሲሆን ባሕሩም ጸጥ ያለ ነበር። ይሁን እንጂ ከጠዋቱ 1:39 ላይ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከሰተ።

የመሬት መንቀጥቀጥ!

የጉባኤ ሽማግሌ የሆነው ሮን ፓርኪንሰን እና ባለቤቱ ዶራቲ የመሬት መንቀጥቀጡ ሲከሰት ቁርስ በማዘጋጀት ላይ ነበሩ። ሮን እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “አሮጌው ቤታችን እንደ ዛፍ ወዲያ ወዲያ ይወዛወዝ ነበር፤ ያም ሆኖ ቤቱ አልፈረሰም። እጅግ በጣም አስፈሪ ድምፅ ይሰማ ነበር። ቁም ሣጥኖች፣ የመመገቢያ ዕቃዎች፣ ፒያኖና ሌሎች የቤት ዕቃዎች ወለሉ ላይ ተከሰከሱ። እኛ ግን እንደ ምንም ብለን ወደ ውጪ ለመውጣት ቻልን። ዶራቲ ባዶ እግሯን ስለነበረች የተሰበረ ጠርሙስ ቆረጣት።”

በዚያው አቅራቢያ የሚኖሩት ቶኒና ክርስቲን ሾ የተባሉ ሚስዮናውያን በፍጥነት ቤታቸውን ለቀው ወጡ። ክርስቲን እንዲህ ብላለች:- “የመሬት መንቀጥቀጡ በጣም ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሳ ከወደቅኩበት መነሳት አቃተኝ። ኃይለኛው ማዕበል ቤቶቹን ከመሠረታቸው ነቅሎ ስለወሰዳቸው በባሕሩ ላይ ሲንሳፈፉ ይታዩ ነበር። አንዳንዶች፣ በፍርስራሾቹ መሃል ጀልባቸውን እየቀዘፉ ከአደጋው የተረፉ ሰዎችን ይፈልጉ ነበር። ከዚያም ሌሎች ከባድ የምድር መናወጦች ተከሰቱ። በቀጣዮቹ አምስት ቀናት ደግሞ ቀላል የሆኑ የምድር መናወጦች ተከሰቱ። በእርግጥም ሁኔታው በጣም አስፈሪ ነበር!”

ከዚያም ሱናሚ ተነሳ

የመሬት መንቀጥቀጡ በተከሰተበት ወቅት ፓትሰን ባኤኣ፣ ከጊዞ ከተማ 6 ኪሎ ሜትር ያህል በሚርቀው በሲፖ ሃይት በሚገኘው ቤቱ ነበር። ፓትሰንና ቤተሰቡ በዚህ ወቅት ምን አጋጠማቸው?

ፓትሰን የነበረውን አስከፊ ሁኔታ በማስታወስ እንዲህ ብሏል:- “የባሕሩን ዳርቻ ተከትዬ ባለቤቴ ናኦሚና አራቱ ልጆቼ ወዳሉበት ሮጥኩ። መሬት ላይ ወድቀው የነበረ ቢሆንም እንኳ ጉዳት አልደረሰባቸውም። ልጆቹ በፍርሃት ይንቀጠቀጡ እንዲያውም አንዳንዶቹ ያለቅሱ ነበር። ይሁንና እኔና ናኦሚ ወዲያውኑ አረጋጋናቸው።”

ፓትሰን በመቀጠል እንደሚከተለው ብሏል:- “ባሕሩ ከተለመደው የተለየ እንቅስቃሴ እንደነበረው አስተዋልኩ። ይህም ሱናሚ ሊከሰት መሆኑን የሚጠቁም ነበር። ትንሿ ደሴታችን በውኃ መጥለቅለቋ እንደማይቀር አሰብኩ። ከምንኖርበት አካባቢ ብዙም በማትርቅ ትንሽ ደሴት ላይ የምትኖረው እናቴ ኤቨላንም በአደገኛ ሁኔታ ሥር እንደሆነች ተሰማኝ። ቤተሰቦቼ በሞተር ጀልባችን ላይ ቶሎ እንዲወጡ ካደረግኩ በኋላ እናቴን ለማዳን ጉዞ ጀመርን።

“ትንሽ እንደተጓዝን ኃይለኛ ሞገድ በጀልባችን ሥር አለፈ። ባሕሩ ላይና ታች ይዋዥቅ ነበር። ወደ ደሴቲቱ ስንደርስ እናቴ እጅግ ተደናግጣና ግራ ተጋብታ ስለነበር እየዋኘች ወደ ጀልባው መምጣት ፈራች። በዚህ ወቅት ናኦሚና የ15 ዓመቱ ልጃችን ጄረሚ፣ በኃይል ወደሚናወጠው ውኃ ዘለው በመግባት እናቴን ወደ ጀልባው እንድትመጣ ረዷት። ከዚያም የሞተር ጀልባችንን በከፍተኛ ፍጥነት በመንዳት ወደ ባሕሩ ገባን።

“ውኃው በጣም ወደኋላ ከመሸሹ የተነሳ በባሕሩ ዳርቻ ላይ የነበሩት ኮራል ሪፎች መታየት ጀመሩ። ከዚያም ኃይለኛ ማዕበል ሁለቱንም ደሴቶች በድንገት አጥለቀለቃቸው። በባሕሩ ዳርቻ ላይ የሚገኘው የእንግዳ መቀበያ ቤታችን ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ ሆነ። በተጨማሪም ውኃው ወደ ዋናው ቤታችን በመግባት አብዛኛውን ንብረታችንን አበላሸብን። ባሕሩ ወደ ቦታው ሲመለስ ጉዳት ወደደረሰበት ቤታችን በመሄድ መጽሐፍ ቅዱሶችንና የመዝሙር መጽሐፎችን ይዘን ወደ ጊዞ ከተማ ተጓዝን።”

በባሕሩ ዳርቻ ላይ የነበሩ በርካታ ቤቶች ከመውደማቸውም ሌላ ብዙ ሰዎች ሞተዋል። ከፍተኛ ጉዳት የደረሰው በጊዞ ደሴት ምዕራባዊ ክፍል ነበር። አምስት ሜትር ከፍታ እንዳለው ሪፖርት የተደረገው ይህ ውኃ ቢያንስ 13 መንደሮችን ሙሉ በሙሉ አውድሟል!

በዚያ ምሽት 22 ሰዎች የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ ለማክበር በጊዞ ከተማ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ተሰብስበው ነበር። የሚያስደስተው ግን ከባድ ጉዳት የደረሰበት ሰው አልነበረም። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ሮን እንዲህ ብሏል:- “በወቅቱ መብራት የጠፋ ከመሆኑም በላይ ፋኖሶቻችንም ተሰባብረው ነበር። ስለዚህ ወንድም ሾ የእጅ ባትሪ ተጠቅሞ ንግግሩን አቀረበ። እኛም በጨለማ ውስጥ ሆነን ድምፃችንን ከፍ አድርገን ለይሖዋ የምሥጋና መዝሙር ዘመርን።”

እርዳታ ለመስጠት የተደረገ ጥረት

አደጋ መድረሱን የሚገልጸው ዜና በዋና ከተማዋ ሆኒያራ እንደተሰማ በዚያ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ በአደጋው ለተጎዱት ወንድሞች እርዳታ ለመላክ ዝግጅት ማድረግ ጀመረ። በተጨማሪም ስልክ በመደወል አደጋው በደረሰበት ቦታ የሚገኙ አብዛኞቹ ወንድሞች ጉዳት እንዳልደረሰባቸው ማረጋገጥ ችሏል። በሽዋዚውል ደሴት ላይ የምትኖር አንዲት እህት ስላለችበት ሁኔታ እንዲያጣሩ ኃላፊነት የሚሰማቸው ወንድሞች ወደዚያ ተላኩ። እነዚህ ወንድሞች እህትን በደህና አግኝተዋታል። ከዚህም በተጨማሪ የእርዳታ ቁሳቁሶችን ለመግዛት የሚያስችል ገንዘብ ወደ ጊዞ ከተማ ተልኳል።

ሐሙስ ዕለት፣ የቅርንጫፍ ቢሮ ተወካዮች ያገኙትን የመጀመሪያ አውሮፕላን ይዘው ወደ ጊዞ ከተማ በረሩ። የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ክራግ ታከር እንዲህ ብሏል:- “በርካታ የእርዳታ ቁሳቁሶችን ይዘን ነበር። የሚጫኑት ዕቃዎች ከአውሮፕላኑ አቅም በላይ ስለነበሩ የሌሎች ተሳፋሪዎች ሻንጣዎች እንዲመለሱ ሲደረግ የእኛ ግን በሰላም መድረስ ችለዋል። በአደጋው አካባቢ ቀድመው ከደረሱት እርዳታዎች መካከል አንዱ የእኛ ነበር። በጀልባ የተጫኑ ሌሎች የእርዳታ ቁሳቁሶች ከሁለት ቀን በኋላ ወደ ቦታው ደረሱ።”

ቶኒ ሾ እና ፓትሰን ባኤኣ፣ በጊዞ ካሉ ሌሎች ወንድሞች ጋር በመሆን በራኖጋ ደሴት ለሚኖሩ ወንድሞች እርዳታ ለመስጠት ለሁለት ሰዓታት ያህል በጀልባ ተጉዘዋል። የመሬት መንቀጥቀጡ፣ 32 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 8 ኪሎ ሜትር ስፋት ያላትን ይህችን ደሴት ከ2 ሜትር በላይ ከፍ አድርጓት ነበር! ይህ ሁኔታ ውኃው እንዲናወጥና በአካባቢው ያሉትን ደሴቶች የመታው ሱናሚ እንዲነሳ ምክንያት እንደሆነ ይታመናል።

ቶኒ እንዲህ በማለት ይናገራል:- “የጉባኤው አባላት እኛን በማየታቸው በጣም ተደሰቱ። ሁሉንም በደህና ያገኘናቸው ቢሆንም ወንድሞች ሌሎች አነስተኛ የምድር መናወጦችን በመፍራት ከቤታቸው ውጪ ሰፍረው ነበር። የእርዳታ ቁሳቁሶችን ጭና የደረሰችው የመጀመሪያዋ ጀልባ የእኛ ነበረች። ከመሰነባበታችን በፊት ከልብ የመነጨ ጸሎት በማቅረብ ይሖዋን በኅብረት አመሰገንን።”

ፓትሰን እንዲህ ይላል:- “ከበርካታ ቀናት በኋላ፣ ተጨማሪ የእርዳታ ቁሳቁሶችን ለማድረስ እንዲሁም ራቅ ባለው የደሴቲቱ ክፍል የሚገኝን አንድ ቤተሰብ ለመፈለግ ወደ ራኖጋ ተመልሰን ሄድን። በመጨረሻም ማቲው ኢቱንና ቤተሰቡን ጫካ ውስጥ ሰፍረው አገኘናቸው። እነሱን ፍለጋ እዚያ ድረስ በመሄዳችን የደስታ እንባ አነቡ! የምድር መናወጡ የእነሱን ጨምሮ በመንደራቸው ያሉትን አብዛኞቹን ቤቶች ቢያወድምም ከምንም በላይ ያሳሰባቸው መጽሐፍ ቅዱስ የማግኘታቸው ጉዳይ ነበር።”

ሌሎች ሰዎች የሰጡት አስተያየት

እንዲህ ያለውን ክርስቲያናዊ ፍቅር ሌሎችም ማስተዋል ችለው ነበር። ክራግ ታከር እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “በአደጋው የተጠቁትን ሰዎች ለመርዳት የተደረገውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ይተች የነበረ አንድ ጋዜጠኛ፣ የይሖዋ ምሥክሮች የመሬት መናወጡ በደረሰ በጥቂት ቀናት ውስጥ ለእምነት ባልንጀሮቻቸው ምግብ፣ ድንኳንና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ማቅረባቸው እንዳስደነቀው ገልጿል።” ፓትሰን ደግሞ እንዲህ ብሏል:- “የራኖጋ መንደር ነዋሪዎች የእምነት አጋሮቻችንን ለመርዳት የወሰድነውን አፋጣኝ እርምጃ ያደነቁ ሲሆን የእነሱ ቤተ ክርስቲያን ግን እንዲህ ባለማድረጓ ማዘናቸውን ተናግረዋል።” አንዲት ሴት “ድርጅታችሁ እርዳታ ለመለገስ ፈጣን ነው!” ስትል ተናግራለች።

የይሖዋ ምሥክሮች ሌሎች ሰዎችንም ለመርዳት ጥረት አድርገዋል። ክርስቲን ሾ እንዲህ በማለት ተናግራለች:- “በጊዞ ከተማ ወደ ተቋቋመ ጊዜያዊ ሆስፒታል ሄደን ሳለ ከጥቂት ቀናት በፊት በአገልግሎት ላይ ያነጋገርናቸውን ባልና ሚስት አገኘናቸው። ሁለቱም ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ስሜታቸውም በጣም ተረብሿል። ኃይለኛው ጎርፍ የሴትየዋን የልጅ ልጅ ከእጇ ነጥቆ ወስዶት ነበር። እኛም በፍጥነት ወደ ቤት ተመልሰን የሚያስፈልጋቸውን ልብስና ምግብ አመጣንላቸው። እነሱም በጣም አመሰገኑን።”

እርግጥ ነው፣ የተፈጥሮ አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች ከቁሳዊ እርዳታ የበለጠ ነገር ያስፈልጋቸዋል። የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የሚሰጠውን ማጽናኛ ማግኘታቸው ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው። ሮን እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “አንዳንድ የሃይማኖት አስተማሪዎች አምላክ ሕዝቡን በኃጢአታቸው ምክንያት እየቀጣቸው እንዳለ ነግረዋቸዋል። ይሁን እንጂ አምላክ ፈጽሞ የክፋት ምንጭ እንዳልሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አሳየናቸው። እንዲህ ያለውን መንፈሳዊ ማጽናኛ ስለነገርናቸው በርካታ ሰዎች አመስግነውናል።”—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4፤ ያዕቆብ 1:13 *

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.24 “‘ለምን?’—ለሚለው ከባድ ጥያቄ መልስ መስጠት” የሚል ርዕስ ያለውን የኅዳር 2006 ንቁ! ገጽ 3–9 ያለውን ተመልከት። አደጋው ከደረሰ በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ የዚህ መጽሔት ቅጂዎች በጊዞ ከተማ ተሰራጭተዋል።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ/ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ሽዋዚውል

የጊዞ ደሴት

የጊዞ ከተማ

ራኖጋ

ሆኒያራ

አውስትራሊያ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የባኤኣ ቤተሰብ በሞተር ጀልባቸው ላይ ሆነው

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሱናሚ በጊዞ ከተማ ላይ ያደረሰው ጉዳት

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በራኖጋ ደሴት ካሉት ቤቶች ሳይፈርስ የቀረው ይህ የመንግሥት አዳራሽ ብቻ ነበር