በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መምረጥ የምትችለው እንዴት ነው?

ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መምረጥ የምትችለው እንዴት ነው?

ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መምረጥ የምትችለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ የተጻፈው በጥንቶቹ የዕብራይስጥ፣ የአረማይክና የግሪክኛ ቋንቋዎች ነበር። በመሆኑም ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እንዲችሉ በቋንቋቸው መተርጎሙ የግድ ሆነ።

በዛሬው ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በብዙ ቋንቋዎች የተተረጎመ መጽሐፍ የለም፤ ይህ መጽሐፍ በሙሉም ሆነ በከፊል ከ2,400 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይገኛል። በአንዳንድ ቋንቋዎች ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ሊገኙ ይችላሉ። በቋንቋህ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የሚገኙ ከሆነ የተሻለውን መጠቀም እንደምትፈልግ ጥርጥር የለውም።

የምታነበውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በመምረጥ ረገድ ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ ማድረግ እንድትችል ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ያስፈልግሃል:- ስንት ዓይነት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አሉ? የእያንዳንዳቸው ጠንካራና ደካማ ጎንስ ምንድን ነው? አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን ስታነብ ጠንቃቃ መሆን የሚኖርብህ ለምንድን ነው?

ከአንዱ ጽንፍ ወደ ሌላው

የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በተለያዩ የአጻጻፍ ስልቶች የሚዘጋጁ ቢሆንም በጥቅሉ በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ይመደባሉ። በአንደኛው ጽንፍ ያለው የትርጉም ዓይነት የቃል በቃል ትርጉም (ኢንተርሊንየር) በመባል ይታወቃል። ይህ የትርጉም ዓይነት መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበትን የመጀመሪያ ቋንቋና የቃል በቃል ትርጉሙን አጣምሮ ይይዛል።

በሌላው ጽንፍ የሚገኘው የትርጉም ዓይነት ደግሞ ነፃ ትርጉም (ፍሪ ትራንስሌሽን ወይም ፓራፍሬዝ) ይባላል። ይህን ዓይነቱን ትርጉም የሚያዘጋጁ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት እነሱ በተረዱበትና አንባቢዎቻቸውን ይማርካል ብለው ባሰቡት መንገድ እንዳሻቸው ይተረጉሙታል።

ሦስተኛው የትርጉም ዓይነት ደግሞ በሁለቱ ጽንፎች መካከል የሚገኝ ሲሆን ሚዛናዊ ለመሆን የሚጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን በሙሉ ያቀፈ ነው። የዚህ ትርጉም አዘጋጆች፣ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበትን የመጀመሪያ ቋንቋ መንፈሱንና ለዛውን እንደያዘ ለአንባቢዎች ቀላል በሆነ መንገድ ለመተርጎም ይጥራሉ።

ቃል በቃል የተተረጎሙ መጽሐፍ ቅዱሶች የተሻሉ ናቸው?

ቃል በቃል የተተረጎሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች፣ አብዛኛውን ጊዜ የእያንዳንዱን ጥቅስ ሐሳብ በተሻለ መንገድ አያስተላልፉም። ለምን? በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም ሁለቱን ተመልከት:-

1. ሁለት ቋንቋዎች ፍጹም ተመሳሳይ የሆነ ሰዋስው፣ የቃላት ብዛትና የዓረፍተ ነገር አወቃቀር ሊኖራቸው አይችልም። በዕብራይስጥ ቋንቋ ላይ ጥናት ያካሄዱት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ድራይቨር እንዲህ ብለዋል:- “[ቋንቋዎች] በሰዋስው ሕግና በአመጣጣቸው ብቻ ሳይሆን . . . ሐሳቦችን በዓረፍተ ነገር ውስጥ በሚያስቀምጡበት መንገድም ይለያያሉ።” ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች የሚያስቡበት መንገድ ይለያያል። ፕሮፌሰር ድራይቨር በመቀጠል “በዚህም ምክንያት የተለያዩ ቋንቋዎች ተመሳሳይ የዓረፍተ ነገር አወቃቀር አይኖራቸውም” ብለዋል።

የትኛውም ቋንቋ ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈበት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቋንቋ ጋር ፍጹም ተመሳሳይ የሆነ የቃላት ብዛትና የሰዋስው ሕግ ሊኖረው አይችልም። በመሆኑም የቃል በቃል ትርጉም ግልጽ ላይሆን ብሎም የተሳሳተ ሐሳብ ሊያስተላልፍ ይችላል። ከዚህ በታች ያሉትን ምሳሌዎች ተመልከት:-

ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ቃል በቃል ሲተረጎም “በሰዎች የዳይ ጨዋታ” የሚል አባባል ተጠቅሟል። (ኤፌሶን 4:14 የኪንግደም ኢንተርሊንየር የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም) * ይህ አባባል በዳይ ጨዋታ የማጭበርበር ድርጊትን ያመለክታል። ይሁንና ይህን ጥቅስ ቃል በቃል መተርጎም በብዙ ቋንቋዎች ስሜት የሚሰጥ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይህ አባባል ‘በሰዎች ረቂቅ ተንኰል’ ተብሎ መተርጎሙ ሐሳቡን ይበልጥ ግልጽ ያደርገዋል።

ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ቃል በቃል ሲተረጎም “መንፈሳችሁ ይፍላ” የሚል ግሪክኛ አባባል ተጠቅሟል። (ሮሜ 12:11 ኪንግደም ኢንተርሊንየር) ይህ አባባል በቋንቋህ ስሜት ይሰጣል? ሊተላለፍ የተፈለገው ሐሳብ ግን “በመንፈስ የጋላችሁ ሁኑ” የሚለው ነው።

ኢየሱስ ታዋቂ በሆነው ንግግሩ ላይ የተናገረው አንድ አባባል በብዙዎች ዘንድ “በመንፈስ ድኾች የሆኑ ብፁዓን ናቸው” ተብሎ ተተርጉሟል። (ማቴዎስ 5:3) ይሁንና ብዙውን ጊዜ ይህን አባባል ቃል በቃል መተርጎሙ ትክክለኛውን ሐሳብ አያስተላልፍም። በአንዳንድ ቋንቋዎች አባባሉን ቃል በቃል መተርጎም የአእምሮ ችግር ያለባቸውን ሰዎች ወይም መንፈሰ ጠንካራና ቆራጥ ያልሆኑ ሰዎችን ሊያመለክት ይችላል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሰዎቹን ማስተማር የፈለገው፣ ደስታቸው የተመካው ቁሳዊ ፍላጎታቸውን በማርካታቸው ላይ ሳይሆን የአምላክ መመሪያ እንደሚያስፈልጋቸው በመረዳታቸው ላይ መሆኑን ነው። (ሉቃስ 6:20) በመሆኑም “በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ ደስተኞች ናቸው” የሚለው ትርጉም የኢየሱስን አነጋገር በተሻለ መንገድ ይገልጸዋል።—ማቴዎስ 5:3 NW

2. የአንድ ቃል ወይም አባባል ትርጉም እንደየአገባቡ ይለያያል። ለምሳሌ ያህል፣ አብዛኛውን ጊዜ የሰውን እጅ ለማመልከት የሚሠራበት የዕብራይስጥ ቃል የተለያዩ ትርጎሞች ሊኖሩት ይችላሉ። በመሆኑም ቃሉ እንደየአገባቡ “መቆጣጠርን፣” “ልግስናን” ወይም “ኃይልን” ሊያመለክት ይችላል። (2 ሳሙኤል 8:3፤ 1 ነገሥት 10:13፤ ምሳሌ 18:21) ይህ ቃል በአዲስ ዓለም የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም (እንግሊዝኛ) ውስጥ ከ40 በሚበልጡ የተለያዩ ቃላት ተተርጉሟል።

የአንድ ቃል አገባብ በትርጉም ላይ ለውጥ ስለሚያመጣ የአዲስ ዓለም የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም (እንግሊዝኛ) 5,500 የግሪክኛ ቃላትን ለመተርጎም 16,000 የእንግሊዝኛ አባባሎችን የተጠቀመ ከመሆኑም ሌላ 8,500 የዕብራይስጥ ቃላትን ለመተርጎም ደግሞ ከ27,000 የሚበልጡ የእንግሊዝኛ ቃላትን ተጠቅሟል። * እንዲህ ያለ ልዩነት ሊኖር የቻለው ለምንድን ነው? የትርጉም ኮሚቴው እነዚህን ቃላት በቀጥታ ከመተርጎም ይልቅ እንደየአገባባቸው ትክክለኛ ሐሳባቸውን ማስተላለፉ የተሻለ እንደሆነ ስላመነበት ነው። ያም ሆኖ የአዲስ ዓለም ትርጉም አዘጋጆች የዕብራይስጥም ሆነ የግሪክኛ ቃላትን ወጥነት ባለው መልኩ ለመተርጎም የተቻላቸውን ያህል ጥረዋል።

ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስን መተርጎም በመጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ ያለን አንድን ቃል ሁልጊዜ በተመሳሳይ ቃል ከመተካት የበለጠ ነገር ይጠይቃል። ተርጓሚዎቹ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈባቸውን የመጀመሪያ ቋንቋዎች ሐሳብ ሳያዛቡ ሰዎች በቀላሉ ሊረዱት በሚችሉት መንገድ ለማስተላለፍ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ሊጠቀሙ ይገባል። በተጨማሪም ተርጓሚዎቹ ቃላትንና ዓረፍተ ነገሮችን ከቋንቋቸው የሰዋስው ሕግ ጋር በሚስማማ መንገድ ማዋቀር ይኖርባቸዋል።

ነፃ ትርጉም ስለሚባሉት ምን ማለት ይቻላል?

የነፃ ትርጉም አዘጋጆች፣ መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ የተጻፈባቸው ቋንቋዎች የያዙትን ሐሳብ እንዳሻቸው ይተረጉሙታል። ይህን የሚያደርጉት እንዴት ነው? የራሳቸውን አመለካከት ሊጨምሩ አሊያም የተወሰነ ሐሳብ ሊቀንሱ ይችላሉ። እንዲህ ያሉት ትርጉሞች ለማንበብ ቀላል ስለሆኑ ሰዎችን ይማርኩ ይሆናል። ይሁን እንጂ ቀለል ባለ ቋንቋ ለማዘጋጀት የሚደረገው ጥረት አንዳንድ ጊዜ ትክክለኛው ሐሳብ እንዲድበሰበስና እንዲዛባ ሊያደርግ ይችላል።

አንድ ነፃ ትርጉም በሰፊው የሚታወቀውን የኢየሱስን የናሙና ጸሎት እንዴት እንደተረጎመው ተመልከት:- “በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ማንነትህን ግለጽልን።” (ማቴዎስ 6:9 ዘ መሴጅ:- ዘ ባይብል ኢን ኮንቴምፖራሪ ላንጉጅ) ሐሳቡን በትክክል ለማስቀመጥ የሚጥር አንድ ትርጉም ግን ይህን አባባል “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ” ሲል ተርጉሞታል። በተጨማሪም አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች በዮሐንስ 17:26 ላይ የሚገኘውን ኢየሱስ በተያዘበት ምሽት ወደ አባቱ ያቀረበውን ጸሎት እንዴት እንደተረጎሙት ልብ በል። አንድ ነፃ ትርጉም “አንተን እንዲያውቁህ አድርጌያለሁ” በማለት ተርጉሞታል። (ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርዥን) ይሁንና የጸሎቱን ሐሳብ ሳያዛባ ለማቅረብ የሞከረ አንድ ትርጉም “ስምህን አስታወቅኋቸው” በማለት አስቀምጦታል። አንዳንድ ተርጓሚዎች፣ አምላክ ልንጠቀምበትና ልንቀድሰው የሚገባ ስም እንዳለው የሚናገረውን እውነት እንዴት እንደደበቁት አስተዋልክ?

ጥንቃቄ ማድረግ ለምን አስፈለገ?

አንዳንድ ነፃ ትርጉሞች፣ መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈባቸው ቋንቋዎች ውስጥ የሚገኙትን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ያድበሰብሳሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ዘ መሴጅ:- ዘ ባይብል ኢን ኮንቴምፖራሪ ላንጉጅ በተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ላይ 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10 እንዲህ ይላል:- “በዚህ መንገድ መኖር እንደሌለባችሁ አታውቁምን? ለአምላክ ደንታ የሌላቸው ዓመጸኞች የእሱን መንግሥት አይወርሱም። ሌሎችን የሚጎዱ፣ ፆታን ያላግባብ የሚጠቀሙ እንዲሁም ምድርን የሚያበላሹም ሆነ በላይዋ ያሉትን ሁሉ የሚጎዱ የአምላክ መንግሥት ዜጋ መሆን አይችሉም።”

አዲስ ዓለም ትርጉም ይህን ጥቅስ እንዴት በትክክል እንዳስቀመጠው ተመልከት:- “ዓመፀኞች የአምላክን መንግሥት እንደማይወርሱ አታውቁም? አትታለሉ። ሴሰኞችም ሆኑ ጣዖት አምላኪዎች ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ ወይም ሌቦች ወይም ስግብግቦች ወይም ሰካራሞች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ቀማኞች የአምላክን መንግሥት አይወርሱም።” (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) ሐዋርያው ጳውሎስ በዝርዝር ያሰፈራቸው ልንርቃቸው የሚገቡን መጥፎ ድርጊቶች በነፃ ትርጉሙ ላይ እንዳልተጠቀሱ ልብ በል።

በተጨማሪም አንድ ተርጓሚ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ትምህርቶችን የሚረዳበት መንገድ በሥራው ላይ ተጽዕኖ ያሳድርበታል። ለምሳሌ ያህል፣ በአብዛኛው ጉድ ኒውስ ባይብል በመባል የሚታወቀው ቱዴይስ እንግሊሽ ቨርዥን የተባለ ትርጉም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “በጠባቡ በር ግቡ፤ ወደ ሲኦል የሚወስደው መንገድ ቀላል፣ በሩም ሰፊ ነውና፤ ብዙዎችም በዚያ ይጓዛሉ” እንዳላቸው ይናገራል። (ማቴዎስ 7:13) የማቴዎስ ዘገባ “ወደ ጥፋት የሚወስደው” በማለት በግልጽ የተናገረ ቢሆንም ተርጓሚዎቹ ግን “ወደ ሲኦል” በሚል ተክተውታል። ይህን ያደረጉት ለምንድን ነው? ‘ክፉዎች ለዘላለም ይሠቃያሉ እንጂ አይጠፉም’ የሚለውን አመለካከት ለመደገፍ አስበው ሊሆን ይችላል። *

አንድ ትርጉም ጥሩ መሆኑን ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ገበሬዎችን፣ እረኞችንና ዓሣ አጥማጆችን ጨምሮ ተራው ሕዝብ ይጠቀምበት በነበረው ቋንቋ ነው። (ነህምያ 8:8, 12፤ የሐዋርያት ሥራ 4:13) ስለዚህ አንድ ትርጉም ጥሩ ነው የሚባለው ባሕላቸው ወይም አስተዳደጋቸው ምንም ይሁን ምን ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች መልእክቱን በቀላሉ ሊረዱት ከቻሉ ነው። በተጨማሪም ጥሩ የሚባል ትርጉም ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን መሥፈርቶች ያሟላል:-

አምላክ በመንፈሱ አማካኝነት የገለጸውን ሐሳብ በትክክል ያስተላልፋል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16

የቋንቋው ሥርዓት እስከፈቀደለት ድረስ መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ ውስጥ ለሰፈረው ቃል ቀጥተኛ ፍቺ ይሰጣል።

መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ ላይ ያለው ቃል ወይም ሐረግ በቀጥታ በሚተረጉምበት ወቅት ሊተላለፍ የተፈለገውን መልእክት የሚያዛባ ወይም የሚያድበሰብስ ከሆነ የቃሉን ወይም የሐረጉን ትክክለኛ መንፈስ ለማስተላለፍ ይጥራል።

ለማንበብ የሚማርክ ለዛውን የጠበቀ ቀለል ያለ ቋንቋ ይጠቀማል።

እንዲህ ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ማግኘት ይቻላል? ይህንን መጽሔት የሚያነቡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አዲስ ዓለም ትርጉምን ማንበብ ይመርጣሉ። ለምን? እነዚህ ሰዎች፣ የአዲስ ዓለም ትርጉም (እንግሊዝኛ) የትርጉም ኮሚቴ መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎም የተጠቀመበት ዘዴ ትክክል መሆኑን ስለሚያምኑ ነው። የመጽሐፉ መቅድም ይህን አስመልክቶ እንዲህ ይላል:- “ቅዱሳን መጻሕፍትን የተረጎምነው በራሳችን አባባል አይደለም። ዘመናዊው የእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚፈቅድልን እስከሆነና ቃል በቃል መተርጎማችን ሐሳቡን የሚያድበሰብሰው ወይም የሚያዛባው እስካልሆነ ድረስ በተቻለን መጠን ቃል በቃል ለመተርጎም ጥረት አድርገናል።”

አዲስ ዓለም የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም በሙሉ አሊያም በከፊል ከ60 በሚበልጡ ቋንቋዎች ከ145,000,000 በላይ ቅጂዎች ታትሟል! ይህ መጽሐፍ ቅዱስ በቋንቋህ የሚገኝ ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች አንድ ቅጂ እንዲያመጡልህ መጠየቅ ትችላለህ። ይህን ትክክለኛ ትርጉም ማንበብህ ጥቅም ያስገኝልሃል።

ቅን ልብ ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የአምላክ ቃል የሚለውን በትክክል መረዳትና ከተማሩት ነገር ጋር ተስማምተው መኖር ይፈልጋሉ። አንተም እንዲህ ያለ ሰው ከሆንክ በቀላሉ ልታነበውና ልትረዳው የምትችለው ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ያስፈልግሃል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.13 የቃል በቃል ትርጉም፣ አንባቢው መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበትን የመጀመሪያ ቋንቋ ከቀጥተኛ ፍቺው ጋር ለማስተያየት ያስችለዋል።

^ አን.17 አንዳንድ እንግሊዝኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አንድን የዕብራይስጥ ወይም የግሪክኛ ቃል ለመተርጎም ከአዲስ ዓለም ትርጉም በበለጠ በርካታ ቃላቶችን በመጠቀማቸው ወጥነት ይጎድላቸዋል።

^ አን.25 መጽሐፍ ቅዱስ ስንሞት ወደ አፈር እንደምንመለስ፣ ልናስብ እንደማንችል እንዲሁም ምንም ዓይነት ስሜት እንደማይኖረንና ነፍስ እንደምትሞት ያስተምራል። (ዘፍጥረት 3:19፤ መክብብ 9:5, 6፤ ሕዝቅኤል 18:4) ቅዱሳን መጻሕፍት ‘የክፉ ሰዎች ነፍስ በእሳታማ ሲኦል ውስጥ ለዘላለም ትሠቃያለች’ ብለው በየትም ቦታ አይናገሩም።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ነፃ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች፣ ለማንበብ ቀላል ስለሆኑ ሰዎችን ይማርኩ ይሆናል። ይሁን እንጂ ቀለል ባለ ቋንቋ ለማዘጋጀት የሚደረገው ጥረት አንዳንድ ጊዜ ትክክለኛው ሐሳብ እንዲድበሰበስና እንዲዛባ ሊያደርግ ይችላል።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አዲስ ዓለም የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም በሙሉ አሊያም በከፊል ከ60 በሚበልጡ ቋንቋዎች ከ145,000,000 በላይ ቅጂዎች ታትሟል!

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በጥንት ዘመን የተዘጋጀ ነፃ ትርጉም

ነፃ የሚባለው የትርጉም ዓይነት ከጥንት ጀምሮ የሚታወቅ ነው። በጥንት ዘመን አይሁዳውያን በአሁኑ ጊዜ አረማይክ ታርገም ወይም ነፃ ትርጉም ተብለው የሚጠሩትን የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉሞች አንድ ላይ ያሰባስቧቸው ነበር። እነዚህ መጻሕፍት ትክክለኛ ትርጉም ናቸው ማለት ባይቻልም እንኳ አይሁዳውያን አንዳንድ ጥቅሶችን እንዴት ይረዷቸው እንደነበር የሚጠቁሙ ሲሆን ተርጓሚዎች አንዳንድ ግልጽ ያልሆኑ ጥቅሶችን ለመረዳት አስችለዋቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በኢዮብ 38:7 (የ1954 ትርጉም) ላይ የተጠቀሱትን ‘የአምላክ ልጆች’ “መላእክት” ብለዋቸዋል። ታርገም፣ በዘፍጥረት 10:9 ላይ የናምሩድን ማንነት ለመግለጽ በገባው የዕብራይስጥ ቃል ላይ የተጨመረው “ፊት” ተብሎ የተተረጎመው መስተዋድድ “ተቃዋሚ” የሚል አሉታዊ አንድምታ እንዳለው ይጠቁማል። ይህ ነፃ ትርጉም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እያስተያየን ልንጠቀምበት የምንችል ቢሆንም ፈጽሞ መጽሐፍ ቅዱስን አይተካም።

[ሥዕል]

በዋልተን የተዘጋጀው “ቢብሊያ ፖሊግሎታ” የተወሰነ ክፍል በ1657 የተጠናቀቀ፣ ኢዮብ 38:1-15

በዕብራይስጥ የተጻፈው ኢዮብ 38:1-15 (ከላቲንኛ የቃል በቃል ትርጉሙ ጋር)

ይኸው ጥቅስ በአረማይክ ታርገም (ነፃ ትርጉም)

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“የኪንግደም ኢንተርሊንየር የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም” የተወሰነ ክፍል፣ ኤፌሶን 4:14

በግራ በኩል ያለው፣ ቃል በቃል የተተረጎመውን የሚያሳይ ሲሆን በቀኝ በኩል ያለው ደግሞ ትርጉሙን ያሳያል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከጀርባ የሚታየው ጽሑፍ:- Shrine of the Book, Israel Museum, Jerusalem