በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

ምድር ትጠፋ ይሆን?

ምድር ትጠፋ ይሆን?

▪ አንዳንዶች ምድር ጥቅምት 21 ቀን 2011 ትጠፋለች ብለው ይጠብቁ ነበር። ሆኖም አልጠፋችም። በመሆኑም በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሬዲዮ ፕሮግራም አቅራቢ የሆኑት ሃሮልድ ካምፒንግ የተናገሩት ትንቢት አልተፈጸመም። እኚህ ሰው ግንቦት 21 ቀን 2011 የፍርድ ቀን እንደሚመጣ ተንብየው ነበር፤ በዚያን ዕለት መላውን ዓለም የሚያናውጥ ታላቅ የምድር መንቀጥቀጥ እንደሚከሰትና ከአምስት ወር በኋላ ይኸውም ጥቅምት 21 ምድር እንደምትጠፋ ተናግረው ነበር።

ይሁንና ምድር ፈጽሞ አትጠፋም። የምድር ፈጣሪ ይህ እንዲሆን አይፈቅድም። የአምላክ ቃል “ምድርን መሠረትሃት፤ እርሷም ጸንታ ትኖራለች” በማለት ይናገራል።​—መዝሙር 119:90

መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡ አንዳንድ ሰዎች ግን ይህች ፕላኔት በእሳት እንደምትጠፋ ይናገራሉ። ይህን ሐሳባቸውን ለመደገፍ 2 ጴጥሮስ 3:7, 10⁠ን ይጠቅሳሉ፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “በዚያው ቃል አሁን ያሉት ሰማያትም ሆኑ ምድር ለእሳትና ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ለሚጠፉበት የፍርድ ቀን ተጠብቀው ይቆያሉ። . . . የሆነ ሆኖ የይሖዋ ቀን እንደ ሌባ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በነጎድጓድ ድምፅ በቅጽበት ያልፋሉ፤ ሰማያትና ምድር የተሠሩባቸው ንጥረ ነገሮችም በኃይለኛ ሙቀት ይቀልጣሉ፤ ምድርና በላይዋ የተሠሩ ነገሮችም ይጋለጣሉ።” ታዲያ ሐዋርያው ጴጥሮስ የተናገረውን ሐሳብ ልንረዳው የሚገባው ቃል በቃል ነው?

አይደለም። ለምን? ምክንያቱም የዚህ ጥቅስ ትርጉም በዙሪያው ካለው ሐሳብና ከተቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ጋር መስማማት ይኖርበታል። እዚህ ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ ቃል በቃል የምንወስድ ከሆነ ከግዑዙ ጠፈር ስፋት አንፃር ስትታይ እንደ ነጥብ በምትቆጠር ፕላኔት ውስጥ በሚኖሩ ክፉ ሰዎች ምክንያት ‘ሰማያት’ ወይም በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠሩ ከዋክብትንና ሌሎች የጠፈር አካላትን የያዘው አጽናፈ ዓለም በሙሉ በእሳት ይጠፋል ማለታችን ነው። አንድ የአሸዋ ቅንጣት ደስ ስላለህ ብቻ አንድን ሰፊ የባሕር ዳርቻ ታጠፋለህ? እንዲህ እንደማታደርግ የታወቀ ነው። ይህ ምክንያታዊ አይደለም! በተመሳሳይም ይሖዋ ከፍጥረት ሥራዎቹ በአንዱ ላይ ዓመፅ ስለተነሳ ብቻ መላውን ጽንፈ ዓለም አያጠፋም።

ደግሞም እንዲህ ያለው አመለካከት ኢየሱስ ክርስቶስ “ገሮች ደስተኞች ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉ” ብሎ ከተናገረው ሐሳብ ጋር በቀጥታ ይቃረናል። (ማቴዎስ 5:5፤ መዝሙር 37:29) አንድ አፍቃሪ አባት ለቤተሰቡ ምቹ ቤት ከሠራላቸው በኋላ ቤቱን ያቃጥለዋል? (መዝሙር 115:16) ይህ የማይመስል ነገር ነው! ይሖዋ ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን አፍቃሪ አባትም ነው።​—መዝሙር 103:13፤ 1 ዮሐንስ 4:8

ጴጥሮስ “ምድር” የሚለውን ቃል የተጠቀመበት ሰብዓዊውን ኅብረተሰብ ለማመልከት ሲሆን እዚህ ጥቅስ ላይ ቃሉ ክፉ የሆነውን ማኅበረሰብ ይወክላል። ጴጥሮስ መጪውን ጥፋት በኖኅ ዘመን ከነበረው የጥፋት ውኃ ጋር እንዳመሳሰለው ልብ በል። (2 ጴጥሮስ 3:5, 6) ያን ጊዜ የጠፉት ክፉ ሰዎች ብቻ ነበሩ፤ ጻድቁ ኖኅ ከነቤተሰቡ የተረፈ ሲሆን ምድርም ብትሆን አልጠፋችም። በተመሳሳይም ጴጥሮስ፣ ስለ “ሰማያት” የተናገረው በምሳሌያዊ ሁኔታ ነው። እዚህ ላይ “ሰማያት” የሚለው ቃል ሰብዓዊ ገዥዎችን ያመለክታል። ስለዚህ ለመለወጥ ፈቃደኛ ያልሆኑ ክፉ ሰዎችና ክፉ የሆኑ መንግሥታት ይወገዳሉ፤ በምትኩ የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት መላውን ምድር ይገዛል።​—ዳንኤል 2:44

ታዲያ ምድር ትጠፋ ይሆን? በፍጹም አትጠፋም። የሚጠፋው ምሳሌያዊው ምድር ወይም ክፉ የሆነው ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ነው። ምድርም ሆነች አምላካዊ ፍርሃት ያላቸው ሰዎች ለዘላለም ይኖራሉ።​—ምሳሌ 2:21, 22