በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአርማጌዶን ጦርነት የሚጀምረው መቼ ነው?

የአርማጌዶን ጦርነት የሚጀምረው መቼ ነው?

የአርማጌዶን ጦርነት የሚጀምረው መቼ ነው?

“እነሆም፣ ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች የተውጣጡ አንድም ሰው ሊቆጥራቸው የማይችል እጅግ ብዙ ሕዝብ . . . ታላቁን መከራ አልፈው [መጡ]።”​—ራእይ 7:9, 14

መድረኩ ለአርማጌዶን ጦርነት ተመቻችቷል። ይህ የሆነው እንዴት ነው?

በአሁኑ ጊዜ፣ ይሖዋን የሚያገለግልና ላቅ ባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች የሚመራ ዓለም አቀፋዊ አንድነት ያለው ሕዝብ አለ። አምላክ ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶችና ቋንቋዎች የተውጣጡ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አንድነት ያለውና በፍቅር የተሳሰረ የወንድማማችነት ኅብረት እንዲመሠርቱ እያደረገ ነው። እንዲህ ዓይነቱ የወንድማማችነት ኅብረት የሚገኘው በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ነው።​—ዮሐንስ 13:35

በቅርቡ ሰይጣን ጭፍሮቹን አሰባስቦ በእነዚህ ሰላማዊና ምንም መከላከያ የሌላቸው መስለው በሚታዩ ሕዝቦች ላይ ከባድ ጥቃት ይሰነዝራል። (ሕዝቅኤል 38:8-12፤ ራእይ 16:13, 14, 16) ይህ እንደሚፈጸም እንዴት እርግጠኛ መሆን ትችላለህ? መጽሐፍ ቅዱስ፣ የአርማጌዶን ጦርነት መቼ እንደሚጀምር ለማወቅ የሚረዱ አንዳንድ ክንውኖችን ለይቶ ይጠቅሳል። ከእነዚህ ክንውኖች መካከል ብዙዎቹ በአሁኑ ጊዜም እየተፈጸሙ ነው።

በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸሙ ያሉ ክንውኖች

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” መቅረቡን እንዴት ማወቅ እንደሚችሉ ኢየሱስን ጠይቀውት ነበር። (ማቴዎስ 24:3) ኢየሱስ መልስ ሲሰጥ ‘ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ የሚነሳበት እንዲሁም በተለያየ ስፍራ የምግብ እጥረትና የምድር ነውጥ የሚከሰትበት’ ጊዜ እንደሚመጣ ተናግሯል። ከዚያ በመቀጠልም “እነዚህ ነገሮች ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው” ብሏል። (ማቴዎስ 24:7, 8) ሐዋርያው ጳውሎስም ይህንን ጊዜ ‘የመጨረሻው ቀን’ በማለት የጠራው ሲሆን “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” እንደሚሆንም ገልጿል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) እነዚህ ትንቢቶች በዛሬው ጊዜ እየተፈጸሙ ያሉ ክንውኖችን የሚገልጹ እንደሆኑ ይሰማሃል?

ይህ ዘመን ያን ያህል አስቸጋሪ የሚሆነው ለምንድን ነው? ሐዋርያው ዮሐንስ ምክንያቱን ገልጾልናል። ሰይጣንና አጋንንቱ ‘ለጥቂት ጊዜ’ ያህል በምድር አካባቢ ብቻ ተወስነው እንዲቆዩ እንደሚደረጉ ዮሐንስ ትንቢት ተናግሮ ነበር። በዚያ ጊዜ ሰይጣን “በታላቅ ቁጣ” እንደሚሞላ ተገልጿል። (ራእይ 12:7-12) በዛሬው ጊዜ በአንድ ስፍራ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም የሚኖሩ ሰዎች የቁጣና የዓመፅ መንፈስ እንደሚያንጸባርቁ ይሰማሃል?

ኢየሱስ በዚህ እጅግ አስቸጋሪ ዘመን አንድ ልዩ የሆነ ሥራ እንደሚከናወንም ተናግሮ ነበር። “ይህ [የአምላክ መንግሥት] ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” ብሏል። (ማቴዎስ 24:14) በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን መንግሥት ምሥራች ከ235 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ ከ500 በላይ በሆኑ ቋንቋዎች እየሰበኩ ነው። እነሱ የሚያዘጋጇቸው መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! የሚባሉት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መጽሔቶች በዓለም ዙሪያ በመሰራጨት ረገድ ተወዳዳሪ የላቸውም። በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን ወደ 100 በሚጠጉ ቋንቋዎች ተርጉመዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ የሚከናወነው በፈቃደኛ ሠራተኞች ሲሆን ለሥራቸው የሚሆነውን የገንዘብ ድጋፍ በሙሉ የሚያገኙትም በፈቃደኝነት ከሚደረግ የገንዘብ መዋጮ ነው። ይህ አስደናቂ የስብከት ዘመቻ ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜ እንደሆነ ይሰማሃል?

መጽሐፍ ቅዱስ በይሖዋ አምላክና እሱን በሚቃወሙ መካከል ወደሚደረገው ጦርነት የሚያመሩ ክንውኖችንም በዝርዝር አስቀምጧል። ከእነዚህ መካከል ወደፊት ሲፈጸሙ የምታያቸውን ሦስት ትንቢቶች እስቲ እንመልከት።

በቅርቡ ሲፈጸሙ የምታያቸው ክንውኖች

ትንቢት 1 ብሔራት፣ “ሰላምና ደህንነት ሆነ!” የሚል ትልቅ ትርጉም ያዘለ አዋጅ እንደሚያወጡ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። እነዚህ ብሔራት የዓለማችንን ታላላቅ ችግሮች ለመፍታት በጣም እንደተቃረቡ ያስቡ ይሆናል። ይህን አዋጅ ተከትለው የሚመጡት ክንውኖች ግን ሰላም እንዲሰፍን የሚያደርጉ አይሆኑም።​—1 ተሰሎንቄ 5:1-3

ትንቢት 2 ቀጥሎም የተለያዩ መንግሥታት በዓለም የሃይማኖት ድርጅቶች ላይ ይነሳሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እነዚህ መንግሥታት በአውሬ ተመስለዋል፤ የዓለም የሐሰት ሃይማኖቶች ደግሞ በአውሬው ጀርባ ላይ እንደተቀመጠች ሴት ተደርገው ተገልጸዋል። (ራእይ 17:3, 15-18) ምሳሌያዊው አውሬ አምላክን እንደሚወክሉ የሚናገሩትን የሐሰት ሃይማኖቶች በማጥፋት ሳይታወቀው የአምላክን ሐሳብ ይፈጽማል።

ሐዋርያው ዮሐንስ ይህን ክንውን እንደሚከተለው በማለት በምሳሌያዊ መንገድ ይገልጸዋል፦ “ያየሃቸው አሥሩ ቀንዶችና አውሬውም ጋለሞታይቱን ይጠሏታል፤ ከዚያም ያወድሟታል፣ እርቃኗንም ያስቀሯታል፤ እንዲሁም ሥጋዋን ይበላሉ፤ ሙሉ በሙሉም በእሳት ያቃጥሏታል። ምክንያቱም አምላክ . . . ሐሳቡን ዳር እንዲያደርሱ . . . ይህን በልባቸው አኑሯል።”​—ራእይ 17:16, 17

ትንቢት 3 በሐሰት ሃይማኖት ላይ የተሰነዘረው ይህ ጥቃት ከተሳካ በኋላ ብሔራት፣ ይሖዋ አምላክን በሚያመልኩት ሕዝቦች ላይ ጥቃት እንዲሰነዝሩ ሰይጣን ያነሳሳቸዋል።​—ራእይ 7:14፤ ማቴዎስ 24:21

አርማጌዶን አንተን እንዴት ይነካሃል?

መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ ለማጥናት አጋጣሚው ካልነበረህ ከላይ የተገለጹት ክንውኖች ይፈጸማሉ ብለህ ማመን አዳጋች ሊሆንብህ ይችላል። ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ሁኔታ በትክክል እንደሚፈጸምና ይህም የሚሆነው በጣም በቅርቡ እንደሆነ ለማመን የሚያበቃ ምክንያት አለ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉት ፍጻሜያቸውን ያገኙ በርካታ ትንቢቶች ስለ ወደፊቱ ጊዜ የተነገሩት ትንቢቶችም እንደሚፈጸሙ ዋስትና ይሆናሉ። *

የይሖዋ ምሥክሮች ‘ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን’ በቅርቡ እንደሚመጣ እርግጠኞች የሆኑበትን ምክንያት እንዲሁም ይህን ቀን መፍራት የሌለብህ ለምን እንደሆነ ለማወቅ ጊዜ እንድትመድብ እናበረታታሃለን። ይሖዋ አምላክ ጥበቃ ከሚያደርግላቸው ሰዎች መካከል አንዱ መሆን እንድትችል ምን ማድረግ እንዳለብህ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ሐሳብ እንዲያሳዩህ የይሖዋ ምሥክሮችን ለምን አትጠይቃቸውም? (ራእይ 16:14) የምትማረው ነገር ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያለህን አመለካከት ሊለውጠው ይችላል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.17 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ትንቢቶች በትክክል እንደተፈጸሙ ማስረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 2 እና ምዕራፍ 9 ተመልከት።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የይሖዋ ምሥክሮች እያከናወኑ ያሉት ሥራ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ ይሆን?