በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

በኢየሱስ ዘመን የኖሩ ሰዎች በእርግጥ በቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ እምቢልታ ይነፉ ነበር?

መጽሐፍ ቅዱስ በደስታ ወቅት እምቢልታ ወይም ዋሽንት እንደሚነፋ ይናገራል። (1 ነገሥት 1:40፤ ኢሳይያስ 5:12፤ 30:29) በሌላ በኩል ደግሞ በቀብር ሥነ ሥርዓት ላይም ሰዎች ይህን የሙዚቃ መሣሪያ ይጫወቱ እንደነበር ይገልጻል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሰዎች በሐዘን ወቅት እንደሚጠቀሙበት የተጠቀሰው የሙዚቃ መሣሪያ እምቢልታ ወይም ዋሽንት ብቻ ነው። ለምሳሌ፣ የማቴዎስ ወንጌል አንድ አይሁዳዊ አለቃ ልትሞት ተቃርባ የነበረችውን ልጁን እንዲያድንለት ኢየሱስን እንደጠየቀው የሚገልጽ ዘገባ ይዟል። ኢየሱስ አለቃው ቤት ሲደርስ ልጅቷ አርፋ ስለነበር ‘የሐዘን እምቢልታ ነፊዎችን እንዲሁም የሚንጫጫና የሚተራመስ ሕዝብ’ ተመለከተ።​—ማቴዎስ 9:18, 23

በእርግጥ በዚያ ወቅት ማቴዎስ የጠቀሰው ዓይነት ልማድ ነበር? የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ የሆኑት ዊልያም ባርክሌይ እንዲህ ብለዋል፦ “በጥንት ጊዜ በአብዛኞቹ አካባቢዎች ይኸውም በሮም፣ በግሪክ፣ በፊንቄ፣ በአሦርና በፓለስቲና ሰው ሲሞት ወይም አሳዛኝ ሁኔታ ሲያጋጥም በእምቢልታ ተጠቅሞ የሐዘን እንጉርጉሮ ማሰማት በጣም የተለመደ ነበር።” ታልሙድ እንደሚለው ከሆነ በአንደኛው መቶ ዘመን፣ የመጨረሻው ድሃ አይሁዳዊ እንኳ ሚስቱ ብትሞትበት በለቅሶ ወቅት ሁለት እምቢልታ ነፊዎችና አንድ አልቃሽ ሴት ይቀጥር ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው ፍላቭየስ ጆሴፈስ የተባለው የታሪክ ምሁር፣ በ67 ዓ.ም. የሮም ወታደሮች በገሊላ የምትገኘውን ጆታፕታን ድል እንዳደረጉ እንዲሁም ነዋሪዎቿን እንደጨፈጨፉ የሚገልጽ ወሬ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ “ከሐዘንተኞቹ መካከል ብዙዎቹ የቀብር ሥነ ሥርዓቱን የሚያጅቡ እምቢልታ ነፊዎች ቀጥረው” እንደነበር ዘግቧል።

ከኢየሱስ አጠገብ የተሰቀሉት ወንጀለኞች የሠሩት ጥፋት ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ወንጀለኞች “ወንበዴዎች” ወይም ዘራፊዎች ብሎ ይጠራቸዋል። (ማቴዎስ 27:38፤ ማርቆስ 15:27) አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላቶች እንደሚያሳዩት ቅዱሳን መጻሕፍት አንዱን ወንጀለኛ ከሌላው ለመለየት የተለያዩ ቃላትን ይጠቀማሉ። ክሌፕቲስ የሚለው የግሪክኛ ቃል እንዳይያዝ ተጠንቅቆ የሚሰርቅን ሌባ ያመለክታል። ይህ ቃል ከደቀ መዛሙርቱ የገንዘብ ሣጥን በድብቅ ይሰርቅ የነበረውን የአስቆሮቱ ይሁዳን ለማመልከት ተሠርቶበታል። (ዮሐንስ 12:6) በሌላ በኩል ግን ሊስቲስ የሚለው ቃል ብዙውን ጊዜ የሚያመለክተው በኃይል ተጠቅሞ የሚዘርፍን ሰው አልፎ ተርፎም አብዮተኛን፣ ዓማፂን ወይም የደፈጣ ተዋጊን ነው። ከኢየሱስ ጋር የተሰቀሉት ግለሰቦች እንዲህ ዓይነት ወንጀለኞች ነበሩ። እንዲያውም አንደኛው ‘እኛ ላደረግነው ነገር የሚገባንን ቅጣት በሙሉ እየተቀበልን ነው’ ብሎ መናገሩ ተዘግቧል። (ሉቃስ 23:41) ይህ ደግሞ የፈጸሙት ወንጀል ተራ ስርቆት ብቻ እንዳልሆነ ያሳያል።

እንደ እነዚህ ሁለት ዘራፊዎች ሁሉ በርባንም ሊስቲስ ተብሎ ተጠርቷል። (ዮሐንስ 18:40) በርባን፣ ተራ ሌባ ብቻ አለመሆኑን ከ⁠ሉቃስ 23:19 በግልጽ መረዳት ይቻላል፤ ዘገባው ስለ በርባን ሲናገር “በከተማው ውስጥ በተከሰተ የሕዝብ ዓመፅና በነፍስ ግድያ የታሰረ ነበር” ይላል።

ከኢየሱስ ጋር ተሰቅለው የነበሩት ወንጀለኞች፣ ዘራፊዎች መሆናቸው ባይካድም ሕዝብን በማሳመፅ አልፎ ተርፎም በነፍስ ግድያ ተካፍለው ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሰዎች የፈጸሙት ወንጀል ምንም ይሁን ምን፣ የሮም ገዥ የነበረው ጳንጥዮስ ጲላጦስ በስቅላት ሊቀጡ እንደሚገባ ተሰምቶታል።