በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

ለነበሩኝ ጥያቄዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አጥጋቢ መልስ አገኘሁ

ለነበሩኝ ጥያቄዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አጥጋቢ መልስ አገኘሁ
  • የትውልድ ዘመን: 1987

  • የትውልድ አገር: አዘርባጃን

  • የኋላ ታሪክ: አባቷ ሙስሊም፣ እናቷ አይሁዳዊት

የቀድሞ ሕይወቴ፦

የተወለድኩት በባኩ፣ አዘርባጃን ሲሆን ወላጆቼ ካፈሯቸው ሁለት ልጆች መካከል ትንሿ እኔ ነኝ። አባቴ ሙስሊም ሲሆን እናቴ ደግሞ አይሁዳዊት ናት። ወላጆቼ ይዋደዱ የነበረ ከመሆኑም ሌላ አንዳቸው የሌላውን ሃይማኖት ያከብሩ ነበር። አባቴ የረመዳን ፆም በሚጾምበት ወቅት እናቴ የሚያስፈልገውን ታደርግለት ነበር፤ እናቴ ፋሲካን ስታከብር ደግሞ አባቴ ይደግፋት ነበር። ቤታችን ውስጥ ቁርዓን፣ ቶራ እና መጽሐፍ ቅዱስ ነበረን።

እኔ ራሴን ሙስሊም አድርጌ እቆጥር ነበር። አምላክ መኖሩን ተጠራጥሬ ባላውቅም አንዳንድ ጉዳዮች ግራ ያጋቡኝ ነበር። ለምሳሌ ‘አምላክ ሰዎችን የፈጠረው ለምንድን ነው? ደግሞስ አንድ ሰው በሲኦል ለዘላለም መሠቃየቱ ላይቀርለት አሁን ሕይወቱን ሙሉ በችግር መማቀቁ ጥቅሙ ምንድን ነው?’ እያልኩ አስብ ነበር። ብዙ ሰዎች፣ ሁሉም ነገር የአምላክ ፈቃድ እንደሆነ ይናገሩ ነበር፤ በመሆኑም ‘አምላክ፣ አሻንጉሊቶችን በእጃቸው እያንቀሳቀሱ ድራማ እንደሚሠሩ ሰዎች ሁሉ ሰዎችን በማሠቃየት ይደሰታል ማለት ነው?’ የሚል ጥያቄ ይፈጠርብኝ ነበር።

አሥራ ሁለት ዓመት ሲሆነኝ በቀን አምስት ጊዜ ሶላት መስገድ ጀመርኩ። በዚያው ጊዜ አካባቢ አባቴ፣ እኔንና እህቴን ወደ አንድ የአይሁዳውያን ትምህርት ቤት አስገባን። እዚያም ከሌሎች ትምህርቶች በተጨማሪ የቶራን ወጎችና የዕብራይስጥ ቋንቋን እንማር ነበር። በየቀኑ ትምህርት ከመጀመሩ በፊት በአይሁዳውያን ባሕል መሠረት እንጸልያለን። በመሆኑም ጠዋት ከቤት ከመውጣቴ ሶላት እሰግዳለሁ፤ ረፋዱ ላይ ደግሞ በትምህርት ቤት በሚደረገው የአይሁዳውያን የጸሎት ሥርዓት ላይ እካፈላለሁ።

ለጥያቄዎቼ አጥጋቢ መልስ ለማግኘት በጣም እጓጓ ነበር። ስለሆነም በትምህርት ቤት የነበሩትን ረቢዎች እንዲህ እያልኩ በተደጋጋሚ እጠይቃቸው ነበር፦ “አምላክ ሰዎችን የፈጠረው ለምንድን ነው? አምላክ ሙስሊም ለሆነው አባቴ ምን አመለካከት አለው? አባቴ ጥሩ ሰው ነው፤ ታዲያ እንደ ርኩስ ተደርጎ የሚታየው ለምንድን ነው? አምላክ አባቴን ለምን ፈጠረው?” ይሁንና የተሰጡኝ መልሶች ጥቂት ሲሆኑ እነሱም ምክንያታዊነት የጎደላቸውና አሳማኝ ያልሆኑ ነበሩ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

በ2002 ባጋጠመኝ ነገር የተነሳ በአምላክ ላይ የነበረኝ እምነት ተናጋ። ወደ ጀርመን ተዛውረን  መኖር ከጀመርን ገና በሳምንታችን አባቴ ጭንቅላቱ ውስጥ ደም ስለፈሰሰ ራሱን ሳተ። የቤተሰቤን ጤንነትና ደኅንነት እንዲጠብቅልኝ አምላክን ለዓመታት ስለምነው ቆይቻለሁ። በሕይወትና በሞት ላይ ሥልጣን ያለው ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ብቻ እንደሆነ አምን ስለነበር የአባቴን ሕይወት እንዲታደግልኝ በየዕለቱ አምላክን እማጸነው ጀመር። ‘አምላክ፣ የአንዲትን ትንሽ ልጅ ምኞት መፈጸም አይሳነውም’ ብዬ አስብ ነበር። የለመንኩትን እንደሚያደርግልኝ እርግጠኛ ነበርኩ። ይሁን እንጂ አባቴ ሞተ።

አምላክ ለሰዎች ስሜት ደንታ ቢስ እንደሆነ ስለተሰማኝ እጅግ አዘንኩ። በመሆኑም ‘አንድም፣ እኔ የምጸልየው በተሳሳተ መንገድ ነው፤ አለዚያም አምላክ የለም’ የሚለው መደምደሚያ ላይ ደረስኩ። በሁኔታው ከመደንገጤ የተነሳ ሶላት መስገድ አቆምኩ። ሌሎች ሃይማኖቶችም አጥጋቢ መልስ ስላልሰጡኝ አምላክ የለም ብዬ ደመደምኩ።

ከስድስት ወራት በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች በራችንን አንኳኩ። እኔና እህቴ ስለ ክርስትና ጥሩ አመለካከት ስላልነበረን ስህተት መሆናቸውን በትሕትና ልናስረዳቸው አሰብን። ስለሆነም “ክርስቲያኖች ኢየሱስን፣ መስቀልን፣ ማርያምንና ሌሎች ጣዖቶችን የሚያመልኩት ለምንድን ነው? ይህ ከአሥርቱ ትእዛዛት ጋር የሚጋጭ አይደለም እንዴ?” ብለን ጠየቅናቸው። እነሱም የጣዖት አምልኮ በእውነተኛ ክርስቲያኖች ዘንድ የተወገዘ እንደሆነና ጸሎት መቅረብ ያለበት ለአምላክ ብቻ እንደሆነ ከቅዱሳን መጻሕፍት በመጥቀስ አሳማኝ ማስረጃ አቀረቡልን። ይህም አስደነቀኝ።

ከዚያም “ስለ ሥላሴስ ምን ትላላችሁ? ኢየሱስ፣ አምላክ ከሆነ እንዴት በምድር ላይ ሊኖርና በሰዎች ሊገደል ይችላል?” ብለን ጠየቅናቸው። አሁንም መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ተጠቅመው ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ እንዳልሆነና ከእውነተኛው አምላክ ጋር እኩል አለመሆኑን አስረዱን። በዚህም ምክንያት ምሥክሮቹ በሥላሴ እንደማያምኑ ገለጹልን። እኔም በመገረም ‘እነዚህ ደግሞ ለየት ያሉ ክርስቲያኖች ናቸው’ ብዬ አሰብኩ።

ያም ሆኖ ሰዎች የሚሞቱት እንዲሁም አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነ ማወቅ ፈለግሁ። የይሖዋ ምሥክሮቹም ለጥያቄዎቼ ዝርዝር ማብራሪያ የሚሰጡ ምዕራፎችን የያዘ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት * የተሰኘ መጽሐፍ አሳዩኝ። ወዲያውኑም አብሬያቸው መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ።

ከይሖዋ ምሥክሮቹ ጋር ባጠናን ቁጥር ለማነሳቸው ጥያቄዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ አሳማኝ መልሶችን ይሰጡኝ ነበር። የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነ አወቅሁ። (መዝሙር 83:18 NW) የይሖዋ ዋነኛ ባሕርይም ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር መሆኑን ተረዳሁ። (1 ዮሐንስ 4:8) ሰዎችን የፈጠረው እነሱም የሕይወትን ስጦታ እንዲያገኙ ስለፈለገ እንደሆነ ተገነዘብኩ። አምላክ በሰዎች ላይ ግፍ እንዲደርስ የፈቀደ ቢሆንም ግፍን እንደሚጠላና በቅርቡም ለዘላለም እንደሚያስወግደው ተረዳሁ። አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ ማመፃቸው በሰው ልጆች ላይ ብዙ መዘዝ እንዳስከተለ ተማርኩ። (ሮም 5:12) ይህ ዓመፅ ካስከተላቸው አሳዛኝ መዘዞች አንዱ በእኔ ላይ እንደደረሰው ሁሉ ሰዎች የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣታቸው ነው። ይሁን እንጂ አምላክ ወደፊት በሚመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ እንዲህ ያሉ አሳዛኝ ሁኔታዎችን ያስወግዳቸዋል፤ እንዲሁም የሞቱ ሰዎች ዳግም ሕያው ይሆናሉ።—የሐዋርያት ሥራ 24:15

ለነበሩኝ ጥያቄዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አጥጋቢ መልስ አገኘሁ። ስለሆነም እንደገና በአምላክ ማመን ጀመርኩ። የይሖዋ ምሥክሮችን ይበልጥ እያወቅኋቸው ስሄድ በዓለም ዙሪያ አንድነት እንዳላቸው ተገነዘብኩ። በመካከላቸው ያለው አንድነትና ፍቅር እጅግ አስደነቀኝ። (ዮሐንስ 13:34, 35) ስለ ይሖዋ የተማርኩት ነገር እሱን እንዳገለግል ስላነሳሳኝ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ወሰንኩ። ጥር 8, 2005 ተጠመቅሁ።

ያገኘሁት ጥቅም፦

ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አሳማኝ የሆኑ መልሶችን ማግኘቴ ስለ ሕይወት የነበረኝ አመለካከት ሙሉ በሙሉ እንዲለወጥ አደረገ። ከአምላክ ቃል ላይ ያገኘሁት አሳማኝ ማብራሪያ ውስጣዊ ሰላም አስገኝቶልኛል። የአምላክ ቃል በሚናገረው መሠረት አባቴን ከሞት ተነስቶ እንደማገኘው ብሩህ ተስፋ አለኝ፤ ይህም ደስታ ያስገኘልኝ ከመሆኑም ሌላ እንድጽናና ረድቶኛል።—ዮሐንስ 5:28, 29

በኋላም ጆናታን የሚባል አምላክን የሚፈራ ሰው አገባሁ፤ ላለፉት ስድስት ዓመታት አስደሳች የትዳር ሕይወት አሳልፈናል። ሁለታችንም ስለ አምላክ የሚገልጸው እውነት ምክንያታዊና ለመረዳት የማይከብድ፣ ሆኖም በዋጋ ሊተመን የማይችል ውድ ሀብት እንደሆነ ተረድተናል። በዚህም የተነሳ ስለምናምንበት ነገር እንዲሁም ስላለን አስደናቂ ተስፋ ለሰዎች መናገር ያስደስተናል። አሁን የይሖዋ ምሥክሮች “ለየት ያሉ ክርስቲያኖች” ሳይሆኑ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደሆኑ አውቃለሁ።

^ አን.15 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ፤ አሁን መታተም አቁሟል።