በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰዎች ፍትሕ ለማግኘት የሚያሰሙት ጩኸት ተሰሚነት ያገኝ ይሆን?

ሰዎች ፍትሕ ለማግኘት የሚያሰሙት ጩኸት ተሰሚነት ያገኝ ይሆን?

 የፍትሕ መጓደል ያላዳረሰው የማኅበረሰቡ ክፍል የለም። ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለእስር ከተዳረጉ ሰዎች ጋር በተያያዘ ብቻ እንኳ ሁለት ምሳሌዎችን መጥቀስ እንችላለን፦

  •   ጥር 2018 በዩናይትድ ስቴትስ ያለች አንዲት ዳኛ ለ38 ዓመት ገደማ የታሰረ አንድ እስረኛ ነፃ እንዲለቀቅ ወሰነች። ግለሰቡ ወንጀሉን እንዳልፈጸመ በዲ ኤን ኤ ማስረጃ ማረጋገጥ ተችሏል።

  •   መስከረም 1994 በአንድ የአፍሪካ አገር የሚኖሩ ሦስት ወጣት ወንዶች በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ታሰሩ። መስከረም 2020 ላይ ከታሰሩ 26 ዓመት የሞላቸው ሲሆን እነዚህን ሁሉ ዓመታት የታሰሩት ሕጋዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መንገድ ክስ ሳይመሠረትባቸው ወይም ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ነው።

 አንተም ፍትሕ የጎደለው ድርጊት ተፈጽሞብህ ከሆነ በጥንት ዘመን የኖረ ኢዮብ የተባለ ሰው የተሰማው ዓይነት ስሜት ሊሰማህ ይችላል፤ ኢዮብ “እርዳታ ለማግኘት ብጣራም ፍትሕ የለም” በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 19:7) እውነተኛ ፍትሕ የሕልም እንጀራ ቢመስልም መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ፍትሕ ለማግኘት የሚያሰሙት ጩኸት ተሰሚነት የሚያገኝበት ጊዜ እንደሚመጣ ቃል ገብቷል። በተጨማሪም በውስጡ የሚገኘው ጥበብ ያዘለ ምክር በዛሬው ጊዜ የሚደርስብህን ኢፍትሐዊ ድርጊት እንድትቋቋም ሊረዳህ ይችላል።

ፍትሕ የጎደላቸው ድርጊቶች መንስኤ ምንድን ነው?

 ፍትሕ የጎደለው ድርጊት የሚፈጽሙት የአምላክን መመሪያ ችላ የሚሉ ሰዎች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ የእውነተኛ ፍትሕ ምንጭ አምላክ እንደሆነ ይናገራል። (ኢሳይያስ 51:4) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ፍትሕ” እና “ጽድቅ” ተብለው የሚተረጎሙት ቃላት በጥብቅ የተቆራኙ ናቸው። (መዝሙር 33:5) በአምላክ መሥፈርቶች መሠረት ጽድቅ ማለትም ትክክልና ተገቢ የሆኑ ነገሮችን ማድረግ ፍትሐዊ ለመሆን ያስችላል። በተቃራኒው የአምላክን የጽድቅ መሥፈርቶች መጣስ ማለትም ኃጢአት መሥራት ኢፍትሐዊ ድርጊት ወደመፈጸም ይመራል። እስቲ የሚከተሉትን ምሳሌዎች ተመልከት፦

  •   ራስ ወዳድነት። የራስ ወዳድነት ምኞትና ኃጢአት በጥብቅ የተሳሰሩ ናቸው። (ያዕቆብ 1:14, 15) ብዙዎች የሚፈልጉትን ነገር ለማግኘት ሲሉ በሌሎች ላይ ኢፍትሐዊ ድርጊት በመፈጸም መጠቀሚያ ያደርጓቸዋል። በተቃራኒው ግን አምላክ የሌሎችን ጥቅም እንድናስቀድም ይፈልጋል።—1 ቆሮንቶስ 10:24

  •   አለማወቅ። አንዳንዶች በሰዎች ላይ ግፍ የሚፈጽሙት ሳይታወቃቸው ሊሆን ይችላል፤ በአምላክ ፊት ግን ይህም ቢሆን ኃጢአት ነው። (ሮም 10:3) እንዲያውም በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ከተፈጸሙት ፍትሕ የጎደላቸው ድርጊቶች ሁሉ የከፋው ድርጊት እንዲፈጸም ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲገደል ምክንያት የሆነው አለማወቅ ነው።—የሐዋርያት ሥራ 3:15, 17

  •   ውጤታማ ያልሆነው የሰዎች ሥርዓት። በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ የዓለም የፖለቲካ፣ የንግድና የሃይማኖት ሥርዓቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ ፍትሕ እንዲያሰፍኑ ይጠበቅባቸዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በዛሬው ጊዜ በስፋት ለሚታየውና ኢፍትሐዊ ወደሆነ ድርጊት ለሚመራው ሙስና፣ መድልዎ፣ ስግብግብነት፣ ከፍተኛ የኑሮ ልዩነትና አለመቻቻል በዋነኝነት ተጠያቂ የሆኑት እነዚህ ሥርዓቶች ናቸው። አንዳንድ ሰዎች እነዚህን ሥርዓቶች የሚደግፉት በቅን ልቦና ተነሳስተው ነው። ዞሮ ዞሮ ግን ሰዎች የአምላክን አመራር ችላ ብለው የሚያደርጉት ማንኛውም ጥረት ስኬታማ ሊሆን አይችልም።—መክብብ 8:9፤ ኤርምያስ 10:23

በሰዎች ላይ እየደረሰ ያለው የፍትሕ መጓደል አምላክን ያሳስበዋል?

 አዎ፣ አምላክ የፍትሕ መጓደልንም ሆነ ለዚያ ምክንያት የሚሆኑ ዝንባሌዎችንና ድርጊቶችን ይጠላል። (ምሳሌ 6:16-18) ነቢዩ ኢሳይያስን “እኔ ይሖዋ a ፍትሕን እወዳለሁና፤ ዝርፊያንና ክፋትን እጠላለሁ” ብሎ እንዲጽፍ አነሳስቶታል።—ኢሳይያስ 61:8

 አምላክ ለጥንቶቹ እስራኤላውያን የሰጠው ሕግ ሕዝቡ ፍትሐዊ እንዲሆን እንደሚፈልግ ያሳያል። ዳኞች ጉቦ እንዳይቀበሉና ፍትሕ የሚያዛቡ ሌሎች ነገሮችን እንዳያደርጉ አዟል። (ዘዳግም 16:18-20) በድሆችና በምስኪኖች ላይ ግፍ በመፈጸም እሱን ያልታዘዙትን እስራኤላውያን አውግዟቸዋል፤ በመጨረሻም የእሱን መሥፈርቶች ባለመጠበቃቸው ከናካቴው ትቷቸዋል።—ኢሳይያስ 10:1-3

አምላክ የፍትሕ መጓደልን ያስወግዳል?

 አዎ። አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት፣ ለኢፍትሐዊ ድርጊቶች መንስኤ የሆነውን ኃጢአትን የሚያስወግድ ከመሆኑም ሌላ የሰው ዘር ወደ ፍጽምና ደረጃ እንዲደርስ ያደርጋል። (ዮሐንስ 1:29፤ ሮም 6:23) በተጨማሪም ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም እንዲመጣና ሁሉም ሰው ፍትሕ እንዲያገኝ የሚያደርግ መንግሥት አቋቁሟል። (ኢሳይያስ 32:1፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) በሰማይ ስለተቋቋመው ስለዚህ መንግሥት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? የተባለውን ቪዲዮ ተመልከት።

ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ ሰዎች ምን ዓይነት ሕይወት ይኖራቸዋል?

 በመላዋ ምድር ላይ ፍትሕ ሲሰፍን ሁሉም ሰው ሰላም አግኝቶና ተረጋግቶ ይኖራል። (ኢሳይያስ 32:16-18) አምላክ እያንዳንዱን ሰው ከፍ አድርጎ ስለሚመለከት ፍትሕ የጎደለው ድርጊት የሚፈጸምበት ሰው አይኖርም። ኢፍትሐዊ ከሆነ ድርጊት ጋር ተያይዞ የሚመጣ ሐዘን፣ ጩኸትና ሥቃይ ለዘላለም ይወገዳል፤ ሌላው ቀርቶ ቀደም ሲል የተፈጸመብን ግፍ ያስከተለብን መጥፎ ትዝታም ቀስ በቀስ ከአእምሯችን ይጠፋል። (ኢሳይያስ 65:17፤ ራእይ 21:3, 4) ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “የአምላክ መንግሥት ምን ነገሮችን ያከናውናል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

አምላክ ፍትሕ የሰፈነበት ዓለም እንደሚያመጣ በገባው ቃል ላይ እምነት መጣል ይቻላል?

 አዎ። መጽሐፍ ቅዱስ አስተማማኝ ትንቢት የያዘ፣ ከታሪክና ከሳይንስ አንጻር ትክክል የሆነና እርስ በርሱ የሚስማማ መጽሐፍ ነው፤ ይህም በውስጡ የሚገኙት ተስፋዎች እምነት የሚጣልባቸው እንደሆኑ ያሳያል። የሚከተሉት ርዕሶች በዚህ ረገድ ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጣሉ፦

በዛሬው ጊዜ ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን ስለ መዋጋት ምን ማለት ይቻላል?

 መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ዘመን የኖሩ ጥሩ ሰዎች፣ ኢፍትሐዊ የሆነ ድርጊት እንዳይፈጸምባቸው የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በሞት ሊያስቀጣ የሚችል መሠረተ ቢስ ክስ ተሰንዝሮበት ነበር። ጳውሎስ ይህን ሁኔታ በጸጋ ከመቀበል ይልቅ ሕጋዊ መብቱን በመጠቀም ለቄሳር ይግባኝ ብሏል።—የሐዋርያት ሥራ 25:8-12

 ይሁንና የሰው ልጆች በዓለም ላይ ያለውን የፍትሕ መጓደል ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ የሚያደርጉት ጥረት ሊሳካ አይችልም። (መክብብ 1:15) ያም ሆኖ ብዙዎች አምላክ ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም እንደሚያመጣ በገባው ቃል ላይ እምነት መጣላቸው ኢፍትሐዊ ድርጊት ሲፈጸምባቸው እንዲረጋጉና የአእምሮ ሰላም እንዲያገኙ ረድቷቸዋል።

a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው።—መዝሙር 83:18