በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሙስና መፍትሔ ይኖረው ይሆን?

ሙስና መፍትሔ ይኖረው ይሆን?

 የመንግሥት ባለሥልጣናት የሚፈጽሙት ሙስና ዓለም አቀፍ ችግር ሆኗል፤ ከፍተኛ ጉዳትም እያስከተለ ነው። a በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የተፈጸመውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት፤ የተለያዩ አገራት ባለሥልጣናት ወረርሽኙን ለመዋጋት የተመደበውን በጀት ራሳቸውን ለማበልጸግ ተጠቅመውበታል የሚሉ ሪፖርቶች ሰምተናል። ይህ ድርጊት ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን የሕክምና እርዳታ እንዳያገኙ እንቅፋት ፈጥሯል፤ ይህም ብዙዎች ለሥቃይ ብሎም ለሞት እንዲዳረጉ ምክንያት ሆኗል።

 የመንግሥት ሙስና ያልነካው ቦታ የለም። የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ዴቪድ ካሜሩን ጉዳዩን እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል፦ “ሙስና እንደ አንድ ትልቅ ድር ነው፤ ሁሉም አገራት በዚህ ድር ተተብትበዋል።”

 ይሁንና በቅርቡ ሙስና ጨርሶ እንደሚወገድ እርግጠኛ መሆን እንችላለን። ምን ማረጋገጫ አለን? መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ወደፊት ስለሚያደርጋቸው ነገሮች ምን እንደሚል ተመልከት።

አምላክ ሙስናን እንደሚያስወግድ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

 መጽሐፍ ቅዱስ ላይ አምላክ እንዲህ ብሏል፦ “እኔ ይሖዋ ፍትሕን እወዳለሁና፤ ዝርፊያንና ክፋትን እጠላለሁ።” b (ኢሳይያስ 61:8) ራሳቸውን ለመጥቀም ሲሉ ሌሎችን የሚበድሉ ሰዎች ድርጊታቸው ከአምላክ እይታ አያመልጥም። (ምሳሌ 14:31) አምላክ “የተጎሳቆሉት ሰዎች በመጨቆናቸው፣ . . . እርምጃ ለመውሰድ እነሳለሁ” ሲል ቃል ገብቷል።—መዝሙር 12:5

 ታዲያ አምላክ ምን እርምጃ ይወስዳል? አሁን ባሉት መንግሥታት ላይ የተሃድሶ ዘመቻ አይጀምርም። ከዚህ ይልቅ እነዚህን መንግሥታት፣ ራሱ ባቋቋመው ሰማያዊ መንግሥት ይተካቸዋል፤ ይህ መንግሥት “የአምላክ መንግሥት” ተብሎ ይጠራል። (ማርቆስ 1:14, 15፤ ማቴዎስ 6:10) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የሰማይ አምላክ . . . መንግሥት ያቋቁማል። . . . እነዚህን መንግሥታት ሁሉ ያደቅቃል፤ ፈጽሞም ያጠፋቸዋል፤ እሱም ብቻውን ለዘላለም ይቆማል።” (ዳንኤል 2:44) በዚህ መንገድ አምላክ ዛሬ የተንሰራፋውን ሙስና ያስወግዳል።

ከሙስና የጸዳ መንግሥት

 አምላክ ያቋቋመው መንግሥት ሙስና ውስጥ እንደማይዘፈቅ በምን እናውቃለን? እስቲ የሚከተሉትን ነጥቦች እንመልከት።

  1.  1. ሥልጣን። የአምላክን መንግሥት ሥልጣን ላይ የሚያቆየው ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ነው።—ራእይ 11:15

     ይህ ምን ለውጥ ያመጣል? ሰዎች የሚያቋቁሟቸው መንግሥታት ሥልጣን ላይ ለመቆየት የዜጎቻቸው ገንዘብ ያስፈልጋቸዋል። ይህ ደግሞ በአብዛኛው ሲታይ ለጉቦ፣ ለሌብነትና ለማጭበርበር መንገድ ይከፍታል። የአምላክ መንግሥት ግን ድጋፍ የሚያገኘው ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ነው። ስለዚህ ዜጎቹ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ ምንጊዜም ማሟላት ይችላል።—መዝሙር 145:16

  2.  2. መሪ። አምላክ ለመንግሥቱ መሪ አድርጎ የሾመው ኢየሱስ ክርስቶስን ነው።—ዳንኤል 7:13, 14

     ይህ ምን ለውጥ ያመጣል? ጥሩ የሚባሉት መሪዎችም እንኳ በተጽዕኖ ወይም በመደለያ ሊሸነፉ ይችላሉ። (መክብብ 7:20) በተቃራኒው ኢየሱስ በጉቦ እንደማይደለል አስመሥክሯል። (ማቴዎስ 4:8-11) ደግሞም ኢየሱስ ማንኛውንም ነገር የሚያደርገው ለዜጎቹ ባለው ፍቅር ተነሳስቶ ነው፤ ለደህንነታቸውም ከልብ ያስባል።—መዝሙር 72:12-14

  3.  3. ሕጎች። የአምላክ መንግሥት ሕጎች ፍጹም ናቸው፤ ለሚታዘዟቸውም እረፍት ያስገኛሉ።—መዝሙር 19:7, 8

     ይህ ምን ለውጥ ያመጣል? ሰዎች የሚያወጧቸው ሕጎች ብዙውን ጊዜ ውስብስብና ጫና የሚፈጥሩ ናቸው፤ ሕጎቹን ከማስፈጸም ጋር በተያያዘም ብዙውን ጊዜ ክፍተት ይኖራል፤ ይህ ደግሞ ለሙስና ቀዳዳ ይከፍታል። በተቃራኒው የአምላክ ሕግጋት ተፈጻሚ ሊሆኑ የሚችሉና ጠቃሚ ናቸው። (ኢሳይያስ 48:17, 18) በተጨማሪም ሕጎቹ ትኩረት የሚያደርጉት ድርጊቱ ላይ ብቻ ሳይሆን ለድርጊቱ መነሻ በሆነው የልብ ዝንባሌ ላይም ነው። (ማቴዎስ 22:37, 39) ደግሞም አምላክ ልብን ማንበብ ስለሚችል ሕጎቹን የሚያስፈጽመው የእያንዳንዱን ግለሰብ ሁኔታና የልብ ዝንባሌ ከግምት አስገብቶ ነው።—ኤርምያስ 17:10

 ከሙስና የጸዳ ዓለም እንደሚመጣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ተስፋ ጊዜ ወስደህ እንድትመረምር እንጋብዝሃለን።

a አንድ መዝገበ ቃላት ሙስናን ሲፈታው “በሥልጣን ወይም በሥራ ድርሻ አላግባብ የመገልገል፣ የመጠቀም ወይም የመጥቀም ድርጊት” ይለዋል።

b ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።