በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

ዮሐንስ 15:13—“የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም”

ዮሐንስ 15:13—“የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም”

 “ሕይወቱን ለወዳጆቹ ሲል አሳልፎ ከሚሰጥ ሰው የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም።”—ዮሐንስ 15:13 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “ስለ ወዳጆቹ ሕይወቱን አሳልፎ ከመስጠት የሚበልጥ ፍቅር ማንም የለውም።”—ዮሐንስ 15:13 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

የዮሐንስ 15:13 ትርጉም

 ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ አንዳቸው ለሌላው ለመሞት ፈቃደኛ እንዲሆኑ የሚያነሳሳ ጠንካራ ፍቅር ሊኖራቸው እንደሚገባ ሊያስተምራቸው ፈልጎ ነበር።

 ኢየሱስ ይህን ሐሳብ ከመናገሩ በፊት ሐዋርያቱን “ትእዛዜ ይህ ነው፤ እኔ እንደወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 15:12) ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ያሳየው ምን ዓይነት ፍቅር ነው? ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ነው። በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት የተከታዮቹንና የሌሎችን ፍላጎት ከራሱ አስቀድሟል። ሰዎችን ከሕመማቸው ፈውሷል፤ እንዲሁም ስለ አምላክ መንግሥት አስተምሯቸዋል። a እንዲያውም ሌሎችን ለመርዳት ሲል ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ሥራዎችን አከናውኗል። (ማቴዎስ 9:35፤ ሉቃስ 22:27፤ ዮሐንስ 13:3-5) ሆኖም ኢየሱስ በዮሐንስ 15:13 ላይ የጠቀሰው የፍቅር መግለጫ ከዚህ በእጅጉ የላቀ ነው። እነዚህን ቃላት ከተናገረ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ “በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ” በፈቃደኝነት በመስጠት እንዲህ ያለውን የላቀ ፍቅር አሳይቷል። (ማቴዎስ 20:28፤ 22:39) በመሆኑም ከራሱ አስበልጦ ሌሎችን እንደሚወድ አስደናቂ በሆነ መንገድ አሳይቷል።

 ኢየሱስ ሁሉንም ሰዎች ይወዳል። ሆኖም ትምህርቱን ለሚከተሉ ሰዎች ለየት ያለ ፍቅር አለው። ደቀ መዛሙርቱ ትእዛዛቱን በመፈጸማቸው እንዲሁም በፈተናዎቹ ከጎኑ ባለመለየታቸው የቅርብ ወዳጆቹ አድርጎ ተመልክቷቸዋል። (ሉቃስ 22:28፤ ዮሐንስ 15:14, 15) ይህም ለእነሱ ሲል ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ለመስጠት የሚያነሳሳ ተጨማሪ ምክንያት ነው።

 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች የኢየሱስን ምክር ተግባራዊ አድርገዋል፤ አንዳቸው ለሌላው ለመሞት ፈቃደኞች ነበሩ። (1 ዮሐንስ 3:16) በእርግጥም ኢየሱስ ያሳየው ዓይነት ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር የእውነተኛ ክርስቲያኖች ዋነኛ መለያ ምልክት ሆኗል።—ዮሐንስ 13:34, 35

የዮሐንስ 15:13 አውድ

 የዮሐንስ ወንጌል ከምዕራፍ 13 እስከ 17 ኢየሱስ ለ11 ታማኝ ሐዋርያቱ የሰጠውን የስንብት ምክርና ከእነሱ ጋር ያቀረበውን የመጨረሻ ጸሎት ይዟል። ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ኢየሱስ ሞተ። በምዕራፍ 15 ላይ ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ተከታዮቹ መሆናቸውን ለማሳየት ከእሱ ጋር ያላቸውን አንድነት ጠብቀው መኖር እንዳለባቸው በምሳሌ ለማስረዳት ሲል ደቀ መዛሙርቱን ከወይን ተክል ቅርንጫፎች ጋር አመሳስሏቸዋል። ከዚያም ‘ብዙ ፍሬ እንዲያፈሩ’ አበረታታቸው። (ዮሐንስ 15:1-5, 8) ይህን ማድረግ የሚችሉበት አንዱ መንገድ ለሌሎች ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር በማሳየት ነው፤ ይህም ኢየሱስ የሰበከውን መልእክት ማለትም “የአምላክን መንግሥት ምሥራች” መስበክን ይጨምራል።—ሉቃስ 4:43፤ ዮሐንስ 15:10, 17

 የዮሐንስ መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።

a የአምላክ መንግሥት በሰማይ ላይ ያለ መስተዳድር ነው። አምላክ ይህን መንግሥት ያቋቋመው ምድርን እንዲገዛና ለምድር ያለውን ፈቃድ እንዲያስፈጽም ነው። (ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:9, 10) ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።