በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

አሥርቱ ትእዛዛት ምንድን ናቸው?

አሥርቱ ትእዛዛት ምንድን ናቸው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 አሥርቱ ትእዛዛት አምላክ ለጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ የሰጣቸው ሕጎች ናቸው። እነዚህ ሕጎች አሥርቱ ቃላት በመባልም ይታወቃሉ፤ ይህ ስያሜ አሴሬት ሃድቨሪም የሚለውን የዕብራይስጥ አገላለጽ ቃል በቃል በመተርጎም የተገኘ ስያሜ ነው። ይህ የዕብራይስጥ አገላለጽ በኦሪት (ቶራ) ማለትም በመጀመሪያዎቹ አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ውስጥ ሦስት ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል። (ዘፀአት 34:28፤ ዘዳግም 4:13፤ 10:4) በግሪክኛ ቋንቋ የሚገኘው ተመሳሳይ አገላለጽ ደግሞ ዴካ (አሥር) ሎጉስ (ቃላት) የሚል ሲሆን “ዴካሎግ” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የመጣው ከዚህ አገላለጽ ነው።

 አምላክ አሥርቱን ትእዛዛት በሁለት የድንጋይ ጽላቶች ላይ በመቅረጽ በሲና ተራራ ላይ ለነቢዩ ሙሴ ሰጠው። (ዘፀአት 24:12-18) አሥርቱ ትእዛዛት በዘፀአት 20:1-17 እና በዘዳግም 5:6-21 ላይ ተዘርዝረዋል።

 የአሥርቱ ትእዛዛት ዝርዝር

  1.   ይሖዋ አምላክን ብቻ አምልክ።—ዘፀአት 20:3

  2.   ጣዖት አታምልክ።—ዘፀአት 20:4-6

  3.   የአምላክን ስም በከንቱ አታንሳ።—ዘፀአት 20:7

  4.   ሰንበትን አክብር።—ዘፀአት 20:8-11

  5.   ወላጆችህን አክብር።—ዘፀአት 20:12

  6.   አትግደል።—ዘፀአት 20:13

  7.   አታመንዝር።—ዘፀአት 20:14

  8.   አትስረቅ።—ዘፀአት 20:15

  9.   በሐሰት አትመሥክር።—ዘፀአት 20:16

  10.   አትጎምጅ።—ዘፀአት 20:17

 የአሥርቱ ትእዛዛት ዝርዝር የሚለያየው ለምንድን ነው?

 መጽሐፍ ቅዱስ አሥርቱን ትእዛዛት በቁጥር አይዘረዝርም። በዚህም ምክንያት ሰዎች የአሥርቱን ትእዛዛት ቅደም ተከተል በተመለከተ የተለያየ አመለካከት አላቸው። ከላይ የሚገኘው ዝርዝር፣ በስፋት የሚሠራበትን የአሥርቱ ትእዛዛት ቅደም ተከተል የሚያሳይ ነው። ሆኖም አንዳንዶች አሥርቱን ትእዛዛት ከዚህ በተለየ መንገድ ያስቀምጧቸዋል። ልዩነቱ የሚታየው በመጀመሪያው፣ በሁለተኛውና በመጨረሻው ትእዛዛት ላይ ነው። a

 የአሥርቱ ትእዛዛት ዓላማ ምን ነበር?

 አሥርቱ ትእዛዛት የሙሴ ሕግ ክፍል ነበሩ። ከ600 የሚበልጡ ትእዛዛትን የያዘው ይህ ሕግ በአምላክና በጥንቱ የእስራኤል ብሔር መካከል ለተመሠረተው ቃል ኪዳን መሠረት ሆኖ አገልግሏል። (ዘፀአት 34:27) አምላክ፣ እስራኤላውያን የሙሴን ሕግ ከታዘዙ ስኬታማ ሕይወት መምራት እንደሚችሉ ቃል ገብቶላቸው ነበር። (ዘዳግም 28:1-14) ይሁንና የሙሴ ሕግ የተሰጠበት ዋነኛ ዓላማ እስራኤላውያን ቃል የተገባለትን መሲሕ ወይም ክርስቶስ ለመቀበል ዝግጁ እንዲሆኑ ማድረግ ነበር።—ገላትያ 3:24

 ክርስቲያኖች አሥርቱን ትእዛዛት ማክበር ይጠበቅባቸዋል?

 አይጠበቅባቸውም። አምላክ አሥርቱን ትእዛዛት ጨምሮ የሙሴን ሕግ የሰጠው ለጥንቱ የእስራኤል ብሔር ነበር። (ዘዳግም 5:2, 3፤ መዝሙር 147:19, 20) ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር አይደሉም፤ አይሁዳውያን የሆኑ ክርስቲያኖችም ጭምር ‘ከሕጉ ነፃ ወጥተዋል።’ (ሮም 7:6) b የሙሴ ሕግ ‘በክርስቶስ ሕግ’ ተተክቷል፤ ‘የክርስቶስ ሕግ’ የሚያመለክተው ኢየሱስ ለተከታዮቹ የሰጣቸውን ትእዛዛት በሙሉ ነው።—ገላትያ 6:2፤ ማቴዎስ 28:19, 20

 አሥርቱ ትእዛዛት በዘመናችንም ጠቃሚ ናቸው?

 አዎ። አሥርቱ ትእዛዛት የአምላክን አስተሳሰብ ለማወቅ ስለሚረዱን ስለ እነዚህ ትእዛዛት ማጥናታችን ጠቃሚ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) አሥርቱ ትእዛዛት የተመሠረቱባቸው መመሪያዎች እምነት የሚጣልባቸውና ፈጽሞ ጊዜ የማይሽራቸው ናቸው። (መዝሙር 111:7, 8) እንዲያውም በተለምዶ አዲስ ኪዳን ተብሎ በሚጠራው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ያሉት ብዙዎቹ ትምህርቶች የተመሠረቱት በእነዚህ መመሪያዎች ላይ ነው።—“ ለአሥርቱ ትእዛዛት መሠረት የሆኑት መመሪያዎች በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተገለጹት እንዴት ነው?” የሚለውን ተመልከት።

 ኢየሱስ አሥርቱን ትእዛዛት ጨምሮ መላው የሙሴ ሕግ በሁለት መሠረታዊ ትእዛዛት ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “‘አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ።’ ይህ ከሁሉ የሚበልጠውና የመጀመሪያው ትእዛዝ ነው። ሁለተኛውም ይህንኑ የሚመስል ሲሆን ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ ይላል። መላው ሕግም ሆነ የነቢያት ቃል በእነዚህ ሁለት ትእዛዛት ላይ የተመሠረቱ ናቸው።” (ማቴዎስ 22:34-40) ስለዚህ ክርስቲያኖች የሙሴን ሕግ ማክበር ባይጠበቅባቸውም አምላክንና ሰዎችን እንዲወዱ ታዘዋል።—ዮሐንስ 13:34፤ 1 ዮሐንስ 4:20, 21

  ለአሥርቱ ትእዛዛት መሠረት የሆኑት መመሪያዎች በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተገለጹት እንዴት ነው?

መመሪያ

በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተጠቀሰበት ቦታ

ይሖዋ አምላክን ብቻ አምልክ

ራእይ 22:8, 9

ጣዖት አታምልክ

1 ቆሮንቶስ 10:14

ለአምላክ ስም አክብሮት ይኑርህ

ማቴዎስ 6:9

አዘውትረህ ለአምላክ አምልኮ አቅርብ

ዕብራውያን 10:24, 25

ወላጆችህን አክብር

ኤፌሶን 6:1, 2

አትግደል

1 ዮሐንስ 3:15

አታመንዝር

ዕብራውያን 13:4

አትስረቅ

ኤፌሶን 4:28

በሐሰት አትመሥክር

ኤፌሶን 4:25

አትጎምጅ

ሉቃስ 12:15

a የጥንት አይሁዶች “ዘፀ[አት] 20 ቁጥር 2ን የመጀመሪያው ‘ቃል’፣ ከቁጥር 3-6 ያሉትን ደግሞ በአንድነት እንደ ሁለተኛ” አድርገው ይቆጥሯቸው ነበር። (ዘ ጂዊሽ ኢንሳይክሎፒድያ) በሌላ በኩል ግን ካቶሊኮች ዘፀአት ምዕራፍ 20 ከቁጥር 1-6 እንደ አንድ ትእዛዝ ሊቆጠር እንደሚገባ ይናገራሉ። በዚህ መሠረት፣ የአምላክን ስም በከንቱ ማንሳት ተገቢ እንዳልሆነ የሚገልጸው ትእዛዝ ሁለተኛ ትእዛዝ ይሆናል። ካቶሊኮች አጠቃላይ የትእዛዛቱ ቁጥር አሥር እንዲሆን ለማድረግ፣ የባልንጀራን ሚስትና ንብረት መመኘት ተገቢ እንዳልሆነ የሚገልጸውን ትእዛዝ እንደ ሁለት ትእዛዝ አድርገው ይቆጥሩታል።

b ሮም 7:7 ላይ አሥረኛው ትእዛዝ “ሕጉ” ከሚያካትታቸው ነገሮች መካከል እንደ ምሳሌ ተደርጎ ተጠቅሷል፤ ይህም የሙሴ ሕግ አሥርቱን ትእዛዛትም እንደሚያጠቃልል ያሳያል።