በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሕይወት እርካታ ለማግኘት የሚረዳ ቁልፍ

በሕይወት እርካታ ለማግኘት የሚረዳ ቁልፍ

ወጣት አረጋዊ፣ ያገባ ያላገባ ሳይል ሁላችንም በሕይወታችን ደስታና እርካታ ማግኘት እንፈልጋለን። ፈጣሪያችንም በሕይወታችን እርካታ እንድናገኝ ይፈልጋል፤ ስለዚህ በዚህ ረገድ የሚረዳን ጠቃሚ ምክር ሰጥቶናል።

ትጉ ሠራተኛ ሁን

“ለተቸገረ ሰው የሚያካፍለው ነገር እንዲኖረው በእጆቹ መልካም ተግባር እያከናወነ በትጋት ይሥራ።”—ኤፌሶን 4:28

ፈጣሪያችን ሥራን እንዳንጠላ ያበረታታናል። ለምን? ተግቶ የሚሠራ ሰው ደስተኛ ነው፤ ምክንያቱም ራሱን ማስተዳደርም ሆነ ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር ማቅረብ ይችላል። እንዲያውም ከራሱ አልፎ የተቸገሩትን መርዳት ይችል ይሆናል። በአሠሪው ዘንድ ተፈላጊ ይሆናል። ስለዚህ ትጉ ሠራተኛ ከሥራ የመባረር አጋጣሚው ጠባብ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ተግቶ መሥራት የሚያስገኘው መልካም ውጤት “የአምላክ ስጦታ” እንደሆነ መናገሩ አያስገርምም።—መክብብ 3:13

ሐቀኛ ሁን

“ሐቀኛ ሕሊና እንዳለን እናምናለን፤ ደግሞም በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር እንፈልጋለን።”—ዕብራውያን 13:18

ሐቀኛ ከሆንን ለራሳችን አክብሮት ይኖረናል፤ የአእምሮ ሰላም እናገኛለን እንዲሁም ጥሩ እንቅልፍ እንተኛለን። በተጨማሪም በሌሎች ዘንድ አክብሮትና አመኔታ እናተርፋለን። ሐቀኛ ያልሆኑ ሰዎች፣ እነዚህን መልካም ነገሮች ራሳቸውን ይነፍጋሉ። ሕሊናቸው ይረብሻቸዋል፤ እንዲሁም ‘ያደረግኩት ነገር ቢታወቅብኝስ’ በሚል ስጋት ይኖራሉ።

ለገንዘብ ትክክለኛ አመለካከት ይኑርህ

“አኗኗራችሁ ከገንዘብ ፍቅር ነፃ ይሁን፤ ባሏችሁ ነገሮች ረክታችሁ ኑሩ።”—ዕብራውያን 13:5

ምግብና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ለማግኘት ገንዘብ ያስፈልገናል። ይሁንና ‘የገንዘብ ፍቅር’ በጣም አደገኛ ነው። ገንዘብ የሚወድ ሰው፣ ብዙ ገንዘብ ለማግኘት የሚያደርገው ሩጫ ጊዜውንና ጉልበቱን ሁሉ ያሟጥጥበታል። ገንዘብ ለማግኘት ሲሯሯጥ ትዳሩ ላይ ውጥረት ሊፈጠር ይችላል፤ ከልጆቹ ጋር የሚያሳልፈው ጊዜ ያጣል፤ አልፎ ተርፎም ጤንነቱ ሊጎዳ ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) ከዚህም አልፎ፣ የገንዘብ ፍቅር ያለው ሰው ለማጭበርበር ሊፈተን ይችላል። አንድ ጠቢብ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “ታማኝ ሰው ብዙ በረከት ያገኛል፤ ሀብት ለማግኘት የሚጣደፍ ግን ንጽሕናውን ማጉደፉ አይቀርም።”—ምሳሌ 28:20

ከሁሉ የተሻለውን ትምህርት ምረጥ

“ጥበብንና የማመዛዘን ችሎታን ጠብቅ።”—ምሳሌ 3:21

ጥሩ ትምህርት መከታተላችን፣ አዋቂ ስንሆን ኃላፊነት የሚሰማን ሰዎችና ወላጆች እንድንሆን ይረዳናል። ይሁንና ትምህርት ቤት የሚሰጠው ትምህርት ብቻውን በሕይወት ስኬታማና ደስተኛ ለመሆን ዋስትና አይሆንም። በሁሉም የሕይወታችን ዘርፍ ስኬታማ መሆን ከፈለግን ከአምላክ የሚገኘውን ትምህርት መማር ያስፈልገናል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክን ስለሚሰማ ሰው ሲናገር “የሚሠራውም ሁሉ ይሳካለታል” ይላል።—መዝሙር 1:1-3