በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክ ወዳጅ እንድንሆን የሚያስችል እውቀት

የአምላክ ወዳጅ እንድንሆን የሚያስችል እውቀት

ፈጣሪያችን ማንነት የሌለው ኃይል አይደለም። ማራኪ የሆኑ ባሕርያት አሉት። ስለ እሱ እንድንማርና ወደ እሱ እንድንቀርብ ይፈልጋል። (ዮሐንስ 17:3፤ ያዕቆብ 4:8) ስለ ማንነቱ ብዙ ነገር ያሳወቀን ለዚህ ነው።

ፈጣሪያችን የግል ስም አለው

“ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣ አዎ፣ አንተ ብቻ በመላው ምድር ላይ ልዑል እንደሆንክ ሰዎች ይወቁ።”—መዝሙር 83:18

መጽሐፍ ቅዱስ፣ እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ብቻ እንደሆነ ያስተምራል። ጽንፈ ዓለምንም ሆነ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች ሁሉ የፈጠረው እሱ ነው። መመለክ ያለበት እሱ ብቻ ነው።—ራእይ 4:11

ይሖዋ አፍቃሪ አምላክ ነው

“አምላክ ፍቅር ነው።”—1 ዮሐንስ 4:8

ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስና በዙሪያችን ባሉ የፍጥረት ሥራዎቹ አማካኝነት ባሕርያቱን ገልጾልናል። ዋነኛ ባሕርይው ፍቅር ነው። ፍቅር የማንነቱ መገለጫ ነው። ስለ ይሖዋ ይበልጥ ባወቅን መጠን ይበልጥ እየወደድነው እንሄዳለን።

ይሖዋ ይቅር ባይ አምላክ ነው

“አንተ . . . ይቅር ለማለት ዝግጁ [ነህ]።”—ነህምያ 9:17

ይሖዋ ፍጹም እንዳልሆንን ያውቃል። ስለዚህ እኛን “ይቅር ለማለት ዝግጁ” ነው። በጥፋታችን እንደተጸጸትን ከነገርነውና መጥፎ ነገር ማድረጋችንን ለማቆም የምንችለውን ሁሉ ካደረግን ይቅር ይለናል፤ የቀድሞ ኃጢአታችንን እንደገና አያነሳብንም።—መዝሙር 103:12, 13

ይሖዋ ጸሎታችንን መስማት ያስደስተዋል

“ይሖዋ ለሚጠሩት ሁሉ፣ . . . ቅርብ ነው። . . . እርዳታ ለማግኘት የሚያሰሙትንም ጩኸት ይሰማል።”—መዝሙር 145:18, 19

ይሖዋ ለየት ያሉ የአምልኮ ሥርዓቶች በመፈጸም ወይም የተለያዩ ሃይማኖታዊ ምስሎች ተጠቅመን እንድናመልከው አይጠብቅብንም። አፍቃሪ የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው ሲናገሩ እንደሚያዳምጧቸው ሁሉ እሱም ስንጸልይ ያዳምጠናል።