በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘የመጽናናት አምላክ’ የሚሰጠው እርዳታ

‘የመጽናናት አምላክ’ የሚሰጠው እርዳታ

‘የመጽናናት አምላክ’ የሚሰጠው እርዳታ

ንጉሥ ዳዊት ብዙ የሚያሳዝኑ ችግሮችና የሚያስጨንቁ ‘ሐሳቦች’ ነበሩበት። ሆኖም ፈጣሪ ስሜታችንን ሁሉ እንደሚረዳልን በፍጹም ተጠራጥሮ አያውቅም። እንደሚከተለው በማለት ጽፏል፦ “እግዚአብሔር ሆይ፤ መረመርኸኝ፤ ደግሞም ዐወቅኸኝ። አንተ መቀመጤንና መነሣቴን ታውቃለህ፤ የልቤንም ሐሳብ ገና ከሩቁ ታስተውላለህ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ገና ቃል ከአንደበቴ ሳይወጣ፣ እነሆ፤ አንተ ሁሉንም ታውቃለህ።”—መዝሙር 139:1, 2, 4, 23

እኛም ብንሆን ፈጣሪያችን ስሜታችንን እንደሚረዳልን እንዲሁም የመንፈስ ጭንቀት ፍጹም ባልሆነው አእምሯችንም ሆነ አካላችን ላይ የሚያስከትለውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የሚሄድ መጥፎ ውጤት ጠንቅቆ እንደሚያውቅ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። አምላክ የመንፈስ ጭንቀት መንስኤው ምን እንደሆነና በአሁኑ ጊዜ ያሉትን አስጨናቂ ሁኔታዎች እንዴት በተሻለ መንገድ መቋቋም እንደምንችል ያውቃል። ከዚህም በላይ የመንፈስ ጭንቀትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዴት እንደሚያስወግድ ገልጾልናል። “የተጨነቁ ሰዎችን የሚያጽናናውና የሚያበረታታው፣ መንፈሳቸውን የሚያድሰውና የሚያስደስተው አምላክ” ተብሎ ከተገለጸው ርኅሩኅ አባታችን የተሻለ ረዳት እንደማናገኝ የታወቀ ነው።—2 ቆሮንቶስ 7:6 ዚ አምፕሊፋይድ ባይብል

ይሁን እንጂ የተጨነቁ ሰዎች ስሜታቸው በሚረበሽበት ጊዜ ‘አምላክ ሊረዳኝ የሚችለው እንዴት ነው?’ ብለው ያስቡ ይሆናል።

አምላክ ለተጨነቁ ሰዎች ቅርብ ነው?

አምላክ ለተጨነቁ አገልጋዮቹ እጅግ ቅርብ ከመሆኑ የተነሳ “የተዋረዱትን መንፈሳቸውን ለማነሣሣት፣ የተሰበረ ልብ ያላቸውን ለማነቃቃት” ከእነሱ ጋር እንደሚኖር ያህል ሆኖ ተገልጿል። (ኢሳይያስ 57:15) ‘አምላክ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ እንደሆነ፣ መንፈሳቸው የተሰበረውንም እንደሚያድን’ ማወቅ እንዴት የሚያጽናና ነው!—መዝሙር 34:18

የተጨነቁ ሰዎች ከአምላክ ማጽናኛ ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው?

የአምላክ አገልጋዮች የሚያስጨንቁ ስሜቶችንና ሁኔታዎችን እንድንቋቋም ሊረዳን ወደሚችለውና ‘ጸሎት ሰሚ’ ወደሆነው አምላክ በቀኑ ውስጥ በማንኛውም ሰዓት መቅረብ ይችላሉ። (መዝሙር 65:2) መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት ለአምላክ ልባችንን እንድናፈስ ያበረታታናል፦ “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።”—ፊልጵስዩስ 4:6, 7

የሚሰማን የዋጋ ቢስነት ስሜት ጸሎታችን በአምላክ ፊት ተሰሚነት አያገኝም ብለን እንድናስብ ቢያደርገንስ?

ያለብን የመንፈስ ጭንቀት አምላክን ለማስደሰት የምናደርገው ጥረት በቂ እንዳልሆነ እንዲሰማን ያደርገን ይሆናል። ይሁን እንጂ በሰማይ የሚኖረው አባታችን ‘ትቢያ መሆናችንን ስለሚያስታውስ’ መንፈሳችን በቀላሉ እንደሚሰበር ያውቃል። (መዝሙር 103:14) ‘ልባችን ሊኮንነን ቢችልም’ እንኳ “አምላክ ከልባችን ይበልጥ ታላቅ” እንደሆነና ‘ሁሉን ነገር እንደሚያውቅ’ ልባችንን ማሳመን እንችላለን። (1 ዮሐንስ 3:19, 20) ስለዚህ መዝሙር 9:9, 10፤ 10:12, 14, 17 እና 25:17 ከመሳሰሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ የተወሰዱ አገላለጾችን በጸሎትህ ውስጥ ልትጠቀምባቸው ትችላለህ።

በጣም ከመጨነቃችን የተነሳ ስሜታችንን በቃላት መግለጽ ቢያስቸግረንስ?

በስሜትህ ላይ የሚደርሰው ሥቃይ በጣም ሲያይል የምትናገረው ሊጠፋህ ይችላል፤ በዚህ ጊዜ ተስፋ አትቁረጥ! “ከርኅራኄ የመነጨ ምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ” ስሜትህንና የሚያስፈልግህን ነገር እንደሚረዳልህ በማወቅ ወደ እሱ መቅረብህን ቀጥል። (2 ቆሮንቶስ 1:3) በዚህ ተከታታይ ርዕሰ ትምህርት ውስጥ የተጠቀሰችው ማሪያ እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ጊዜ በጣም ግራ ሲገባኝ ስለምን እንደምጸልይ አላውቅም። ሆኖም አምላክ ስሜቴን እንደሚረዳልኝና ሊረዳኝ ዝግጁ እንደሆነ አውቃለሁ።”

አምላክ ለጸሎታችን ምላሽ የሚሰጠው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ በአሁኑ ጊዜ ችግሮቻችንን ሁሉ እንደሚያስወግድልን አይናገርም። ይሁን እንጂ የመንፈስ ጭንቀትን ጨምሮ “ሁሉን” ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት ይሰጠናል። (ፊልጵስዩስ 4:13) ማርቲና እንዲህ ብላለች፦ “የመንፈስ ጭንቀት ለመጀመሪያ ጊዜ ባሠቃየኝ ወቅት ልቋቋመው ከምችለው በላይ ሆኖ ስለተሰማኝ ይሖዋ ወዲያውኑ እንዲፈውሰኝ ጸልዬ ነበር። አሁን ግን በየዕለቱ ብርታት እንዲሰጠኝ መጸለይ ብቻ ይበቃኛል።”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ የተጨነቁ ግለሰቦች ያለባቸውን የመንፈስ ጭንቀት እንዲቋቋሙ የሚረዳቸውን መንፈሳዊ ጥንካሬ የሚያገኙበት ምንጭ ነው። ከመንፈስ ጭንቀት ጋር ለ35 ዓመታት ስትታገል የኖረችው ሣራ መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብ ያለውን ተግባራዊ ጠቀሜታ ከራሷ ተሞክሮ አይታዋለች። እንዲህ ትላለች፦ “ከሕክምናው መስክ ያገኘሁትን እርዳታ በጣም አደንቃለሁ። ከሁሉም በላይ ግን የአምላክን ቃል ማንበብ ለመንፈሳዊውም ሆነ ለዕለት ተዕለት ሕይወቴ ጠቃሚ እንደሆነ እገነዘባለሁ። መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ልማድ አዳብሬያለሁ።”

የመንፈስ ጭንቀት ፈጽሞ የማይኖርበት ጊዜ!

ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ሳለ አምላክ የሰጠውን ኃይል ከባድ ሕመሞችን ለመፈወስ እንደሚጠቀምበት በተግባር አሳይቷል። ኢየሱስ በከባድ ሕመም ለሚሠቃዩ ሰዎች እፎይታ ለማምጣት ይጓጓ ነበር። ከዚህም በላይ በስሜት ላይ የሚደርሰው ጫና ምን ያህል ሥቃይ እንደሚያስከትል ከተሞክሮ ያውቀዋል። ክርስቶስ ተሠቃይቶ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት “ከሞት ሊያድነው ለሚችለው በከፍተኛ ለቅሶና እንባ ምልጃና ልመና አቀረበ።” (ዕብራውያን 5:7) ኢየሱስ በዚያን ጊዜ እንዲህ ያለ ሥቃይ ማሳለፉ በአሁን ጊዜ ላለነው ለእኛ ይጠቅመናል፤ ምክንያቱም “[ኢየሱስ] በመፈተን ላይ ላሉት ሊደርስላቸው ይችላል።”—ዕብራውያን 2:18፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2

አምላክ፣ ለመንፈስ ጭንቀት አስተዋጽዖ የሚያደርጉ አስጨናቂ ሁኔታዎችን የማስወገድ ዓላማ እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። አምላክ እንዲህ በማለት ቃል ገብቷል፦ “እኔ፣ አዲስ ሰማያትንና አዲስ ምድርን እፈጥራለሁ፤ ያለፉት ነገሮች አይታሰቡም፤ አይታወሱም። ነገር ግን በምፈጥረው፣ ደስ ይበላችሁ፤ ለዘላለም ሐሤት አድርጉ።” (ኢሳይያስ 65:17, 18) “አዲስ ሰማያት” ተብሎ የተጠራው የአምላክ መንግሥት ‘ለአዲሱ ምድር’ ማለትም በምድር ላይ ለሚኖረው ጻድቅ ኅብረተሰብ ፍጹም የሆነ አካላዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ጤንነት ያስገኛል። ማንኛውም ዓይነት ሕመም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተጠራርጎ ይጠፋል።

“በጥልቁ ጕድጓድ ውስጥ ሳለሁ፣ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ሆይ፤ የአንተን ስም ጠራሁ። ልመናዬን ሰምተሃል፤ ‘ርዳታም ፈልጌ ስጮኽ፣ ከመስማት ጆሮህን አትከልክል።’ በጠራሁህ ጊዜ ቀረብኸኝ፣ እንዲሁም፣ ‘አትፍራ’ አልኸኝ።”—ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:55-57