በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“በምትጸልዩበት ጊዜ ሁሉ እንዲህ በሉ፦ ‘አባት ሆይ’”

“በምትጸልዩበት ጊዜ ሁሉ እንዲህ በሉ፦ ‘አባት ሆይ’”

“በምትጸልዩበት ጊዜ ሁሉ እንዲህ በሉ፦ ‘አባት ሆይ’”

“አባት።” ይህን ቃል ስትሰማ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? አፍቃሪ የሆነና ለቤተሰቡ ደህንነት በጥልቅ የሚያስብ ሰው ነው? ወይስ ኃላፊነቱን ችላ የሚል ምናልባትም ቤተሰቡን የሚበድል ሰው? ይህ በአብዛኛው የተመካው በአባትህ ማንነት ላይ ነው።

“አባት” የሚለውን ቃል ኢየሱስ ወደ አምላክ ሲጸልይና ስለ እሱ ሲናገር ብዙ ጊዜ ተጠቅሞበታል። * ኢየሱስ ተከታዮቹን ስለ ጸሎት ሲያስተምራቸው በሚጸልዩበት ጊዜ ሁሉ “አባት ሆይ” እንዲሉ ነግሯቸዋል። (ሉቃስ 11:2) ይሁን እንጂ ይሖዋ ምን ዓይነት አባት ነው? የዚህ ጥያቄ መልስ በጣም አስፈላጊ ነው። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ ምን ዓይነት አባት እንደሆነ በደንብ ከገባን ይበልጥ ወደ እሱ እንቀርባለን እንዲሁም እንወደዋለን።

በሰማይ ስላለው አባታችን ከኢየሱስ የበለጠ ሊነግረን የሚችል ማንም የለም። ኢየሱስ ከአባቱ ጋር የቅርብ ወዳጅነት አለው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ከአብ በቀር ወልድን ሙሉ በሙሉ የሚያውቅ የለም፣ ከወልድና ወልድ ሊገልጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን ሙሉ በሙሉ የሚያውቅ ማንም የለም።” (ማቴዎስ 11:27) በመሆኑም አብን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ሊያሳውቀን የሚችለው ወልድ ነው።

ታዲያ በሰማይ ስላለው አባታችን ከኢየሱስ ምን ልንማር እንችላለን? ኢየሱስ ምን እንዳለ ተመልከት፦ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።” (ዮሐንስ 3:16) እዚህ ላይ ኢየሱስ፣ በሰማይ ያለውን አባታችንን ዋነኛ ባሕርይ ይኸውም ፍቅሩን ጎላ አድርጎ ገልጿል። (1 ዮሐንስ 4:8) ይሖዋ ፍቅሩን በተለያዩ መንገዶች ገልጿል፤ ከእነዚህም መካከል በእኛ እንደሚደሰት መግለጽ፣ ርኅራኄ ማሳየት፣ ጥበቃ ማድረግ፣ ተግሣጽ መስጠት እንዲሁም የሚያስፈልጉንን ቁሳዊ ነገሮች ማሟላት ይገኙበታል።

አባታችን በእኛ እንደሚደሰት አረጋግጦልናል

ልጆች፣ ወላጆቻቸው በእነሱ እንደሚደሰቱ ማወቃቸው ያበረታታቸዋል። ኢየሱስ፣ አባቱ “በእሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” ብሎ ሲናገር መስማቱ ምን ያህል አበረታቶት እንደሚሆን አስበው። (ማቴዎስ 3:17) ኢየሱስም አባቱ እንደሚወደንና በእኛ እንደሚደሰት አረጋግጦልናል። ኢየሱስ “እኔን የሚወደኝን . . . አባቴ ይወደዋል” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 14:21) እነዚህ ምንኛ የሚያጽናኑ ቃላት ናቸው! ይሁን እንጂ በዚህ እንዳንደሰት ለማድረግ የሚጥር አንድ አካል አለ።

ሰይጣን፣ በሰማይ ያለው አባታችን በእኛ ደስ የሚሰኝ መሆኑን እንድንጠራጠር ለማድረግ ይሞክራል። አምላክን ለማስደሰት እንደማንበቃ ሊያሳምነን ይፈልጋል። ብዙውን ጊዜም ይህን የሚያደርገው በእርጅና ወይም በሕመም ምክንያት በጣም በምንዳከምበት አሊያም በራሳችን ድክመት ወይም በሌሎች ቅር በመሰኘታችን ተስፋ በምንቆርጥበት ጊዜ ነው። አምላክ፣ ደስ ሊሰኝበት እንደማይችል ተሰምቶት የነበረውን ሉካስ የሚባል አንድ ወጣት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ሉካስ ወጣት ሳለ፣ ወላጆቹ ከዚያ ቀደም ያስተማሩትን በርካታ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች እነሱ ራሳቸው መከተል እንደተዉ ይገልጻል። በዚህ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም፣ በሰማይ ከሚኖረው አባቱ ጋር ዝምድና መመሥረት ከብዶት ነበር። በተጨማሪም ሉካስ በተፈጥሮው ችኩል በመሆኑ በተለይ ከሌሎች ጋር ባለው ግንኙነት ረገድ ብዙ ጊዜ ችግር ይገጥመው ነበር። ይሁን እንጂ ታጋሽና አበረታች በሆነችው ሚስቱ እርዳታ ቀስ በቀስ የችኩልነት ባሕሪውን ማስተካከል ቻለ፤ ሉካስ ባለቤቱ “ልዩ በረከት እና ከአምላክ ያገኛት ስጦታ” እንደሆነች ይናገራል። ሉካስ “ክርስቶስ ኢየሱስ ኃጢአተኞችን ለማዳን ወደ ዓለም [እንደመጣ]” መገንዘብ ቻለ። (1 ጢሞቴዎስ 1:15) ሉካስ፣ አምላክ እንደሚወደውና በእሱ እንደሚደሰት ማሰቡ ደስታና እርካታ እንዳመጣለት ይናገራል።

አንተም ይሖዋ እንደሚወድህ ወይም እንደሚደሰትብህ አንዳንድ ጊዜ ጥርጣሬ የሚያድርብህ ከሆነ በ⁠ሮም 8:31-39 ላይ ያለውን ጥቅስ ማንበብህና በዚያ ላይ ማሰላሰልህ ሊያበረታታህ ይችላል። በዚህ ጥቅስ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ምንም ነገር ቢሆን “በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ከተገለጸው የአምላክ ፍቅር ሊለየን እንደማይችል” የሚገልጽ ፍቅር የተንጸባረቀበት ማረጋገጫ ሰጥቶናል። *

ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ አባት

በሰማይ ያለው አባታችን የሚደርስብን መከራ ይሰማዋል። ይሖዋ “ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ” ያለው አምላክ ነው። (ሉቃስ 1:78) ኢየሱስ፣ ፍጽምና ለሌላቸው ሰዎች የአባቱን ዓይነት ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ አሳይቷል። (ማርቆስ 1:40-42፤ 6:30-34) እውነተኛ ክርስቲያኖችም የሰማዩን አባታቸውን ዓይነት ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ ለማሳየት ይጥራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “አንዳችሁ ለሌላው ደጎችና ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ” በማለት የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ ያደርጋሉ።​—ኤፌሶን 4:32

ፌሊፔ የሚባል አንድ ሰው ያጋጠመውን ሁኔታ እንመልከት። አንድ ቀን ወደ ሥራ እየሄደ ሳለ ከጀርባው በስለት የተወጋ ያህል በድንገት ኃይለኛ ሕመም ተሰማው። በመሆኑም በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ተወሰደ። ስምንት ሰዓት የፈጀ ምርመራ ከተደረገለት በኋላ ሐኪሞቹ፣ የአቢይ ደም ቅዳ ቧንቧው ውስጠኛ ሽፋን እንደተቀደደ ተገነዘቡ። ሐኪሞቹ ከዚያ በኋላ በሕይወት የሚቆየው ለ25 ደቂቃ ብቻ በመሆኑ ቀዶ ሕክምና ማድረጉ ምንም ፋይዳ እንደሌለው ተናገሩ።

በቦታው የተገኙ የፌሊፔ የእምነት አጋሮች ይህን ሲሰሙ ከአንጀት በመነጨ ርኅራኄ ተነሳስተው እርምጃ ወሰዱ። በአፋጣኝ ወደ ሌላ ሆስፒታል እንዲዛወር ያደረጉ ሲሆን በዚያም አስቸኳይ ቀዶ ሕክምና ተደረገለት፤ የእምነት ባልንጀሮቹ ቀዶ ሕክምናው እስኪጠናቀቅ ድረስ አብረውት ነበሩ። ደስ የሚለው ነገር የፌሊፔ ሕይወት ተረፈ። ፌሊፔ ያጋጠመውን ነገር መለስ ብሎ ሲያስብ፣ የእምነት አጋሮቹን ላሳዩት ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ ያመሰግናቸዋል። በእርግጥ ፌሊፔ፣ የእምነት ባልንጀሮቹ ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ እንዲያሳዩት ያነሳሳቸው በሰማይ ያለው አባቱ እንደሆነ ያምናል። “አምላክ፣ ልክ እንደ አንድ አፍቃሪ አባት እኔን ለማጠንከር በአጠገቤ የቆመ ያህል ነበር” በማለት ፌሊፔ ይናገራል። በእርግጥም ይሖዋ ብዙውን ጊዜ ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ የሚያሳየው በምድር ያሉት አገልጋዮቹ ይህን ባሕርይ እንዲያንጸባርቁ በማነሳሳት ነው።

አባታችን ጥበቃ ያደርግልናል

አንድ ትንሽ ልጅ አደጋ ሊያጋጥመው እንደሚችል ሲመለከት ጥበቃ ለማግኘት ሮጦ ወደ አባቱ ሊሄድ ይችላል። አንድ ልጅ አፍቃሪ በሆነው አባቱ እቅፍ ውስጥ ሲሆን የደኅንነት ስሜት ይሰማዋል። ኢየሱስ ይሖዋ ጥበቃ እንደሚያደርግለት ሙሉ በሙሉ ይተማመን ነበር። (ማቴዎስ 26:53፤ ዮሐንስ 17:15) እኛም ብንሆን በሰማይ ያለው አባታችን ጥበቃ ስለሚያደርግልን የደኅንነትና የመተማመን ስሜት ሊሰማን ይችላል። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ በዋነኝነት ጥበቃ የሚያደርግልን በመንፈሳዊ ሁኔታ ነው። በሌላ አባባል፣ ከአደጋ እንድንርቅና ከእሱ ጋር ያለንን ወዳጅነት እንድንጠብቅ ለማድረግ የሚያስፈልገንን ትጥቅ በመስጠት ከመንፈሳዊ አደጋ ይጠብቀናል። ይሖዋ ጥበቃ የሚያደርግበት አንዱ መንገድ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር እንድናገኝ በማድረግ ነው። እንዲህ ዓይነቱን ምክር ስናገኝ ይሖዋ ከኋላችን ሆኖ “መንገዱ ይህ ነው፤ በእርሱ ሂድ” እያለ የሚናገረን ያህል ነው።​—ኢሳይያስ 30:21

የሮክ ኤንድ ሮል ሙዚቃ ባንድ አባላት የነበሩትን ቲአጉን እንዲሁም ወንድሞቹን ፈርናንዱንና ራፋኤልን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በሳኦ ፓውሎ፣ ብራዚል በሚገኝ የታወቀ የሙዚቃ አዳራሽ ውስጥ እንዲጫወቱ በተመረጡ ጊዜ በጣም ተደስተው ነበር። ስኬት ደጇን ከፍታ የምትጠብቃቸው ይመስል ነበር። ይሁን እንጂ አንድ የእምነት አጋራቸው፣ ለአምላክ መመሪያዎች አክብሮት እንደሌላቸው በግልጽ የሚያሳይ አኗኗር ካላቸው ሰዎች ጋር መቀራረብ አደጋ እንዳለው አስጠነቀቃቸው። (ምሳሌ 13:20) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርቶ የሰጣቸውን ምክር ለማጠናከር የወንድሙን ተሞክሮ ነገራቸው። ወንድሙ ከመጥፎ ጓደኞች ጋር በመግጠሙ የተነሳ ከአምላክ መመሪያዎች ጋር የሚጋጭ ተግባር እንደፈጸመ ገለጸላቸው። ቲአጉና ወንድሞቹ ይህን ሲሰሙ የሙዚቀኝነት ሥራቸውን ለመተው ወሰኑ። በአሁኑ ጊዜ ሦስቱም በሙሉ ጊዜ ክርስቲያናዊ አገልግሎት ተሠማርተዋል። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ምክር መቀበላቸው ከመንፈሳዊ ጉዳት እንደጠበቃቸው ያምናሉ።

በሰማይ ያለው አባታችን ተግሣጽ ይሰጠናል

አንድ አፍቃሪ አባት ልጆቹ ሲያድጉ ምን ዓይነት ሰዎች እንደሚሆኑ ስለሚያሳስበው ተግሣጽ ይሰጣቸዋል። (ኤፌሶን 6:4) እንዲህ ዓይነቱ አባት ጥብቅ ሊሆን ቢችልም ልጆቹን በጭካኔ አይቀጣም። በተመሳሳይም በሰማይ ያለው አባታችን አንዳንድ ጊዜ እኛን መገሠጽ አስፈላጊ ሆኖ ሊያገኘው ይችላል። ይሁን እንጂ አምላክ ምንጊዜም ተግሣጽ የሚሰጠው በፍቅር ተነሳስቶ ሲሆን ተግሣጹም ቢሆን በፍጹም የሚያስመርር አይደለም። ኢየሱስም በዚህ ረገድ የአባቱን ዓይነት ባሕርይ አሳይቷል፤ ደቀ መዛሙርቱ ለሰጣቸው እርማት ፈጣን ምላሽ ባልሰጡበት ወቅትም ቢሆን ተግሣጽ የሰጣቸው በደግነት ነው።​—ማቴዎስ 20:20-28፤ ሉቃስ 22:24-30

ሪካርዱ የሚባል አንድ ሰው ይሖዋ ተግሣጽ የሰጠው በፍቅር ተነሳስቶ መሆኑን እንዴት እንደተገነዘበ እስቲ እንመልከት። ሪካርዱ፣ አባቱ ትቶት የሄደው ገና የሰባት ወር ሕፃን ሳለ ነበር። ሪካርዱ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ በነበረበት ወቅት አባት የሌለው መሆኑ በጣም ይሰማው ነበር። መጥፎ ተግባሮች መፈጸም የጀመረ ሲሆን በዚህም ምክንያት ሕሊናው ያሠቃየው ነበር። አኗኗሩ ከክርስቲያናዊ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር እንደማይስማማ ስለተገነዘበ የጉባኤውን ሽማግሌዎች ለማነጋገር ወሰነ። ሽማግሌዎቹም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ጥብቅ ሆኖም ፍቅር የሚንጸባረቅበት ምክር ሰጡት። ሪካርዱ የተሰጠውን ተግሣጽ በአድናቆት የተቀበለ ቢሆንም ያደረገው ነገር ክፉኛ ስለሚረብሸው እንቅልፍ የሚያጣበትና የሚያለቅስበት ጊዜ ነበር፤ አልፎ ተርፎም በመንፈስ ጭንቀት ይሠቃይ ነበር። ውሎ አድሮ ግን ይሖዋ የሰጠው ተግሣጽ አሁንም እንደሚወደው የሚያረጋግጥ መሆኑን ተገነዘበ። ሪካርዱ “ይሖዋ የሚወደውን ይገሥጻል” የሚለውን በ⁠ዕብራውያን 12:6 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ አስታወሰ።

እኛም ብንሆን ተግሣጽ ሲባል አንድ ሰው ለፈጸመው ጥፋት ከመቅጣት ወይም እርማት ከመስጠት የበለጠ ነገርን እንደሚጨምር ማስታወሳችን ጥሩ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ተግሣጽን ከሥልጠና ጋር አያይዞ ይገልጸዋል። ስለዚህ በሰማይ ያለው አፍቃሪ አባታችን፣ የሠራነው ስህተት የሚያስከትለውን መዘዝ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን እንድንቀምስ በማድረግ ተግሣጽ ሊሰጠን ይችላል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያመለክተው ይሖዋ የሚሰጠን ተግሣጽ ትክክለኛውን ጎዳና እንድንከተል ስለሚረዳን ሥልጠና ይሆነናል። (ዕብራውያን 12:7, 11) አዎን፣ አባታችን የእኛ ደኅንነት በጣም ስለሚያሳስበው ለገዛ ጥቅማችን ሲል ያርመናል።

አባታችን ቁሳዊ ፍላጎታችንን ያሟላልናል

አንድ አፍቃሪ አባት የቤተሰቡን አካላዊና ቁሳዊ ፍላጎት ለማሟላት ይጥራል። ይሖዋም የሚያደርገው ልክ እንደዚህ ነው። ኢየሱስ “በሰማይ የሚኖረው አባታችሁ እነዚህ ሁሉ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 6:25-34) ይሖዋም “ፈጽሞ አልተውህም፣ በምንም ዓይነት አልጥልህም” በማለት ቃል ገብቷል።​—ዕብራውያን 13:5

ኒሴ የተባለች አንዲት ሴት፣ ባሏ ከሥራ በተባረረበት ጊዜ የእነዚህን ቃላት እውነተኝነት መገንዘብ ችላለች። ባሏ ከሥራ ከመባረሩ ጥቂት ቀደም ብሎ፣ ሁለት ሴቶች ልጆቿን ለመንከባከብና በአምላክ አገልግሎት ለመካፈል የሚያስችላት ተጨማሪ ጊዜ ለማግኘት ስትል ጥሩ ደመወዝ የሚያስገኝ ሥራዋን ለቃ ነበር። ታዲያ አሁን በምን ሊተዳደሩ ነው? ኒሴ ወደ ይሖዋ ጸለየች። በማግሥቱ ባሏ አንዳንድ ንብረቶቹን ለማምጣት ወደ ሥራ ቦታው ተመልሶ ሲሄድ የሚገርም ነገር ገጠመው፤ አለቃው፣ ክፍት የሥራ ቦታ እንዳለና ይህን ሥራ እሱ ማግኘት እንደሚችል ነገረው! በመሆኑም የኒሴ ባል ሥራውን ባጣ ማግሥት ሌላ ሥራ አገኘ። ኒሴና ባለቤቷ ለጸሎታቸው መልስ በማግኘታቸው በሰማይ ያለውን አባታቸውን አመሰገኑ። የእነሱ ተሞክሮ እንደሚያሳየው የሚያስፈልገንን የሚያሟላልን አፍቃሪ አባት የሆነው ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ፈጽሞ አይረሳም።

አባታችን ለሚያሳየን ፍቅር አድናቆታችንን መግለጽ

በእርግጥም በሰማይ ያለውን አባታችንን አስደናቂ ፍቅር ሙሉ በሙሉ ለመግለጽ ቃላት ያጥሩናል! ይሖዋ በእኛ እንደሚደሰት በመግለጽ፣ ርኅራኄ በማሳየት፣ ጥበቃ በማድረግ፣ ተግሣጽ በመስጠት እንዲሁም የሚያስፈልጉንን ቁሳዊ ነገሮች በማሟላትና በሌሎች የተለያዩ መንገዶች አባታዊ ፍቅሩን እንደሚገልጽልን ስናስብ ማንም ሊወዳደረው የማይችል ግሩም አባት መሆኑን እንገነዘባለን!

ታዲያ በሰማይ ያለው አባታችን ላሳየን ፍቅር አድናቆታችንን መግለጽ የምንችለው እንዴት ነው? ስለ እሱና ስለ ዓላማው ይበልጥ ለማወቅ ጥረት ማድረግ እንችላለን። (ዮሐንስ 17:3) ከእሱ ፈቃድና ከመመሪያዎቹ ጋር በሚስማማ መንገድ ሕይወታችንን መምራት እንችላለን። (1 ዮሐንስ 5:3) ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት እሱ ያሳየን ዓይነት ፍቅር ማሳየት እንችላለን። (1 ዮሐንስ 4:11) በእነዚህ ሁሉ መንገዶች ይሖዋን እንደ አባታችን አድርገን እንደምንመለከተውና የእሱ ልጆች በመሆናችን ኩራት እንደሚሰማን እናሳያለን።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 ይሖዋ፣ አባታችን እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ጊዜ ተጠቅሷል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ስለ ይሖዋ ሲናገር “አባት” እና “አብ” በሚሉት ቃላት በተደጋጋሚ ይጠቀም ነበር፤ እነዚህን ቃላት በመጀመሪያዎቹ ሦስት ወንጌሎች ውስጥ ከ60 ጊዜ በላይ እንዲሁም በዮሐንስ ወንጌል ላይ ብቻ 100 ጊዜ ያህል እናገኛቸዋለን። ሐዋርያው ጳውሎስም በጻፋቸው ደብዳቤዎች ላይ ስለ አምላክ ሲናገር እነዚህን ቃላት ከ40 ጊዜ በላይ ተጠቅሟል። ይሖዋ፣ አባታችን የተባለው ሕይወታችንን ያገኘነው ከእሱ ስለሆነ ነው።

^ አን.9 ወደ ይሖዋ ቅረብ ከተባለው በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ላይ “‘ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን’ የሚችል ነገር የለም” የሚለውን ምዕራፍ 24⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ይሖዋ ምን ዓይነት አባት እንደሆነ በደንብ ከገባን ይበልጥ ወደ እሱ እንቀርባለን እንዲሁም እንወደዋለን

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ይሖዋን እንደ አባታችን አድርገን እንደምንመለከተውና የእሱ ልጆች በመሆናችን ኩራት እንደሚሰማን ማሳየት እንችላለን

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ይሖዋ እንደ አባት እንደሚወደን በተለያዩ መንገዶች ያሳያል

እንደሚደሰትብን በመግለጽ

ርኅራኄ በማሳየት

ጥበቃ በማድረግ

ተግሣጽ በመስጠት

የሚያስፈልገንን በማሟላት