በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአምላክ ቃል ተማር

መንፈሳዊ ፍጥረታት ሊጠቅሙን ወይም ሊጎዱን የሚችሉት እንዴት ነው?

መንፈሳዊ ፍጥረታት ሊጠቅሙን ወይም ሊጎዱን የሚችሉት እንዴት ነው?

ይህ ርዕስ በአእምሮህ ሊመላለሱ የሚችሉ ጥያቄዎችን በማንሳት መልሶቹን መጽሐፍ ቅዱስህ ውስጥ የት ቦታ ላይ ማግኘት እንደምትችል ይጠቁምሃል። የይሖዋ ምሥክሮች ለጥያቄዎቹ በተሰጡት መልሶች ላይ ከአንተ ጋር ለመወያየት ፈቃደኞች ናቸው።

1. መላእክት እነማን ናቸው?

መላእክት በሰማይ የሚኖሩ መንፈሳዊ ፍጥረታት ናቸው። መላእክት ከሰዎች የላቁ ፍጥረታት ናቸው። መንፈሳዊ አካል የሆነው እውነተኛው አምላክ መላእክትን የፈጠረው ምድርን ከመፍጠሩ በፊት ነው። (ኢዮብ 38:4, 7፤ ማቴዎስ 18:10) በሚሊዮን የሚቆጠሩ ታማኝ መላእክት በይሖዋ ዙሪያ ሆነው ያገለግሉታል።​—መዝሙር 103:20, 21ን እና ዳንኤል 7:9, 10ን አንብብ።

2. መላእክት ሰዎችን ይረዳሉ?

መላእክት ሎጥ የተባለውን ጻድቅ ሰው ረድተውታል። ሎጥ የሚኖረው በነዋሪዎቿ ክፋት ምክንያት አምላክ እንድትጠፋ በወሰነባት አንዲት ከተማ ውስጥ ነበር። በመሆኑም ሎጥና ቤተሰቡ ከከተማይቱ ሸሽተው እንዲወጡ ሁለት መላእክት አስጠነቀቋቸው። አንዳንድ ሰዎች፣ መላእክቱ የተናገሩትን እንደ ቀልድ በመቁጠር ማስጠንቀቂያውን ችላ አሉት። ሎጥ እና ሴት ልጆቹ ግን አምላክ በመላእክቱ አማካኝነት ያስነገረውን ማስጠንቀቂያ ሰምተው ስለታዘዙ ሕይወታቸውን ማትረፍ ችለዋል።​—ዘፍጥረት 19:1, 13-17, 26ን አንብብ።

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው መላእክት በዛሬው ጊዜ፣ የመንግሥቱን ምሥራች በታማኝነት የሚሰብኩ ሰዎች የሚያከናውኑትን ሥራ በማገዝ ሰዎችን እየረዱ ነው። (ማቴዎስ 24:14) ይህ ምሥራች የማስጠንቀቂያ መልእክትም ይዟል። ለሎጥ እንደተነገረው መልእክት ሁሉ ይህ ማስጠንቀቂያም በቁም ነገር ሊታይ ይገባል። ይህን ማስጠንቀቂያ በመላእክቱ አማካኝነት ያስነገረው አምላክ ነው።​—ራእይ 1:1ን እና ራእይ 14:6, 7ን አንብብ።

ፈተናዎች ሲያጋጥሙንም አምላክ በመላእክቱ አማካኝነት ያጠነክረናል። አምላክ በአንድ መልአክ በመጠቀም ኢየሱስን አበርትቶታል።​—ሉቃስ 22:41-43ን አንብብ።

ከዚህም በተጨማሪ አምላክ በቅርቡ፣ በሌሎች ላይ መከራ የሚያደርሱ ክፉ ሰዎችን ለማጥፋት በመላእክት ይጠቀማል። ይህም ለሰው ዘር እፎይታ ያስገኛል።​—2 ተሰሎንቄ 1:6-8ን አንብብ።

3. አጋንንት ጉዳት ሊያደርሱብን የሚችሉት እንዴት ነው?

በምድር ላይ የኖሩ ብዙ ሰዎች አምላክን ለመታዘዝ አሻፈረን በማለት ክፉዎች እንደሆኑ ሁሉ በሰማይ ላይ የሚገኙ በርካታ መላእክትም በአምላክ ላይ ዓምፀዋል። (2 ጴጥሮስ 2:4) እነዚህ ታዛዥ ያልሆኑ መላእክት አጋንንት ተብለው ይጠራሉ። የእነዚህ መላእክት መሪ ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። ሰይጣንና አጋንንቱ የሰውን ዘር እያሳሳቱ ነው።​—ራእይ 12:9ን አንብብ።

ሰይጣን፣ ሰዎችን ከአምላክ ለማራቅ ሲል ብልሹ የሆነውን የንግድ ሥርዓት፣ ሰብዓዊ መንግሥታትንና የሐሰት ሃይማኖትን ይጠቀማል። በመሆኑም የሰውን ዘር ለሚያሠቃየው የፍትሕ መጓደል፣ ዓመፅ እና መከራ ተጠያቂው ሰይጣን ነው።​—1 ዮሐንስ 5:19ን አንብብ።

4. አጋንንት ሰዎችን የሚያሳስቱት እንዴት ነው?

ሰይጣን፣ የሞቱ ሰዎች መናፍስት እንደሚሆኑና እነዚህ የሙታን መናፍስት ከሰዎች ጋር መነጋገር እንደሚችሉ በማስተማር ብዙዎችን አታልሏል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሙታን ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ይናገራል። (መክብብ 9:5) ሆኖም አጋንንት፣ ሰዎች በሞት ያጧቸውን የሚወዷቸውን ግለሰቦች ድምፅ በማስመሰል ያታልሏቸዋል። (ኢሳይያስ 8:19) አጋንንት በመናፍስት ጠሪዎች፣ በጠንቋዮች፣ ሟርት በሚሠሩ ሰዎች እና በኮከብ ቆጠራ በመጠቀምም ያሳስታሉ። የአምላክ ቃል ከእነዚህ ሁሉ ድርጊቶች እንድንርቅ ያስጠነቅቀናል። በመሆኑም ከአጋንንትም ሆነ ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር የተያያዘ ማንኛውም ነገር ካለን ማስወገድ ይኖርብናል።​—ዘዳግም 18:10, 11ን እና የሐዋርያት ሥራ 19:19ን አንብብ።

ይሖዋን የምንወደው ከሆነ አጋንንትን መፍራት አይኖርብንም። የአምላክን ቃል ማጥናታችን ብሎም በውስጡ ያለውን ተግባራዊ ማድረጋችን ሰይጣንን ለመቃወምና ወደ አምላክ ለመቅረብ ያስችለናል። ይሖዋ ከአጋንንት የበለጠ ኃይል አለው። ታማኝ መላእክቱም በሚያስፈልገን ጊዜ ኃይል ይሰጡናል።​—መዝሙር 34:7ን እና ያዕቆብ 4:7, 8ን አንብብ።

ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 10 ተመልከት።