በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት

አምላክ ሰዎችን በገሃነመ እሳት ያቃጥላል?

አምላክ ሰዎችን በገሃነመ እሳት ያቃጥላል?

የይሖዋ ምሥክሮች ከሰዎች ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መወያየት ያስደስታቸዋል። አንተስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የተያያዘ ግራ የሚያጋባህ ነገር አለ? የይሖዋ ምሥክሮች ስለሚያምኑባቸው ነገሮች ወይም ስለ ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸው ለማወቅ ትፈልጋለህ? ከሆነ በሚቀጥለው ጊዜ ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር ስትገናኝ ጥያቄህን ከማቅረብ ወደኋላ አትበል። የይሖዋ ምሥክሮች ስለ እነዚህ ጉዳዮች ከአንተ ጋር መወያየት ያስደስታቸዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች ከሰዎች ጋር ምን ዓይነት ውይይት እንደሚያደርጉ የሚያሳይ ምሳሌ ከዚህ በታች ቀርቧል። ሚካኤል የሚባል አንድ የይሖዋ ምሥክር ከቤት ወደ ቤት እየሄደ ሲሰብክ አብርሃም የሚባል ሰው እንዳገኘ አድርገን እናስብ።

አምላክ ክፉ ሰዎችን ይቀጣል?

ሚካኤል፦ ታዲያስ አብርሃም፣ እንዴት ሰንብተሃል?

አብርሃም፦ ደህና ነኝ፤ አንተስ እንዴት ነህ?

ሚካኤል፦ በጣም ደህና ነኝ። ሰሞኑን ባለፈው ያልከኝን ነገር ሳስብበት ነበር።

አብርሃም፦ ኧረ፣ ምን ብዬህ ነበር?

ሚካኤል፦ የይሖዋ ምሥክሮች በገሃነመ እሳት አለማመናቸው እንዳስገረመህ ነግረኸኝ ነበር።

አብርሃም፦ አዎ፣ በገሃነመ እሳት የማታምኑ መሆኑ በጣም ገርሞኛል።

ሚካኤል፦ የተሰማህን በግልጽ ስለነገርኸኝ አመሰግንሃለሁ። የሌሎችን አመለካከት መስማት ያስደስተኛል። ከገሃነመ እሳት ጋር በተያያዘ ሰዎች ያላቸው አመለካከት የተለያየ ነው፤ አንተ በዚህ ረገድ ምን ብለህ እንደምታምን ልትገልጽልኝ ትችላለህ?

አብርሃም፦ ያው እኔ የማምነው፣ በጣም መጥፎ የሆኑ ሰዎች ሲሞቱ ወደ ገሃነም እንደሚገቡና በዚያም ለዘላለም እንደሚሠቃዩ ነው።

ሚካኤል፦ ብዙ ሰዎች እንዲህ ዓይነት አመለካከት አላቸው። እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ፤ በሕይወትህ ውስጥ መጥፎ ነገር አጋጥሞህ ያውቃል?

አብርሃም፦ አዎ፣ ከአምስት ዓመት በፊት እህቴ በሰው እጅ ሕይወቷ ጠፍቷል።

ሚካኤል፦ እውነትህን ነው? እንዴት ያሳዝናል! መቼም እሷን ማጣትህ በጣም እንደጎዳህ የታወቀ ነው።

አብርሃም፦ እሱማ ምን ጥያቄ አለው፤ ስለ እሷ ባሰብኩ ቁጥር ነገሩ ያንገበግበኛል።

ሚካኤል፦ አንዳንዶች ገሃነመ እሳት መኖር እንዳለበት የሚሰማቸው መጥፎ ሰዎች በፈጸሙት ድርጊት በጣም ስለተጎዱ እንደሆነ አስተውያለሁ። ደግሞም በክፉዎች ጥቃት የደረሰባቸው ንጹሐን ሰዎች በዳዮቻቸው እንዲቀጡ ቢፈልጉ የሚያስገርም አይሆንም።

አብርሃም፦ እንዴ፣ ታዲያስ! እኔም ብሆን እህቴን የገደለው ሰው በቤተሰባችን ላይ ላመጣው መከራ የእጁን እንዲያገኝ እፈልጋለሁ።

ሚካኤል፦ እንዲህ የሚሰማህ መሆኑ አያስገርምም። መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን ንጹሐን ሰዎች በክፉዎች ጥቃት ሲደርስባቸው አምላክ እንደሚቆጣና ክፉ አድራጊዎችን ለመቅጣት ቃል እንደገባ ይናገራል። ኢሳይያስ 3:11 ምን እንደሚል ልብ በል፤ ጥቅሱ “በደለኞች ወዮላቸው፤ ጥፋት ይመጣባቸዋል፤ የእጃቸውን ያገኛሉና” ይላል። ከዚህ ለማየት እንደምንችለው አምላክ ክፉዎችን ይቀጣል።

አብርሃም፦ ታዲያ አንተ እንደምትለው የገሃነም እሳት የሚባል ነገር ከሌለ አምላክ ክፉዎችን የሚቀጣው እንዴት ነው?

ሚካኤል፦ ይሄ ጥሩ ጥያቄ ነው። በአጭር አነጋገር አምላክ ክፉዎችን የሚቀጣው ለዘላለም እንዲጠፉ በማድረግ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በ2 ተሰሎንቄ 1:9 ላይ ምን እንደሚል ልብ በል፤ እባክህ ጥቅሱን ታነበዋለህ?

አብርሃም፦ እሺ፣ “እነዚህ ሰዎች ዘላለማዊ ጥፋት ተፈርዶባቸው ከጌታ ፊት ይወገዳሉ” ይላል።

ሚካኤል፦ አየህ አብርሃም፣ አምላክ ክፉ ሰዎችን ለዘላለም ሞተው እንዲቀሩ በማድረግ ስለሚቀጣቸው ወደፊት በሕይወት የመኖር ተስፋ አይኖራቸውም።

አብርሃም፦ የጥቅሱ ሐሳብ ገብቶኛል። እኔ ግን ይህ ትክክለኛ ፍርድ አይመስለኝም። መሞትማ ሁሉም ሰው ይሞታል። ታዲያ በጣም መጥፎ የሆኑ ሰዎች ከሌላው ሰው የከፋ ቅጣት ሊበየንባቸውም አይገባም?

ፍትሕ የሚፈጸመው እንዴት ነው?

ሚካኤል፦ እንደማየው ከሆነ የፍትሕ ጉዳይ በጣም የሚያሳስብህ ይመስላል።

አብርሃም፦ አዎ፣ በጣም ያሳስበኛል።

ሚካኤል፦ እንዲህ የሚሰማህ መሆኑ ጥሩ ነው። የሰው ልጆች የፍትሕ ስሜት ሊኖራቸው የቻለው አምላክ ሲፈጥራቸው ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን ነገር የመለየት ችሎታ ስለሰጣቸው ነው። አምላክ ራሱ የፍትሕ ጉዳይ በጣም ያሳስበዋል። ይሁንና የሃይማኖት መሪዎች፣ አምላክ ሰዎችን በገሃነመ እሳት እንደሚያቃጥል ሲያስተምሩ ፍትሐዊ እንዳልሆነ እየተናገሩ ነው ማለት ይቻላል።

አብርሃም፦ ምን ማለትህ ነው?

ሚካኤል፦ እስቲ አንድ ምሳሌ ልንገርህ። ስለ አዳምና ሔዋን የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ታውቀዋለህ?

አብርሃም፦ አዎ፣ አውቀዋለሁ። አምላክ የአንድን ዛፍ ፍሬ እንዳይበሉ ነግሯቸው የነበረ ቢሆንም እነሱ ግን አልታዘዙም።

ሚካኤል፦ ትክክል ነህ። እስቲ በዘፍጥረት 2:16, 17 ላይ የሚገኘውን ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ አብረን እንመልከተው። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር አምላክ ሰውን እንዲህ በማለት አዘዘው፤ ‘በአትክልት ስፍራው ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ ትበላለህ። ነገር ግን መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ፤ ምክንያቱም ከእርሱ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ።’” ከዚህ ለማየት እንደምንችለው አዳም ከተከለከለው ፍሬ ቢበላ ምን እንደሚደርስበት አምላክ ነግሮት ነበር?

አብርሃም፦ እንደሚሞት ነግሮት ነበር።

ሚካኤል፦ ልክ ነህ። እስቲ አስበው፦ አዳም ኃጢአት በመሥራቱ መላው የሰው ዘር ኃጢአተኛ ሆኖ እንዲወለድ ምክንያት ሆኗል። * አዳም እንዲህ ዓይነት ጥፋት ቢሠራም እንኳ አምላክ በገሃነመ እሳት እንደሚያቃጥለው ተናግሯል?

አብርሃም፦ አይ፣ አልተናገረም።

ሚካኤል፦ አዳምና ሔዋን የሚጠብቃቸው ቅጣት ለዘላለም በገሃነመ እሳት መቃጠል ቢሆን ኖሮ አምላክ አስቀድሞ ሊያስጠነቅቃቸው አይገባም ነበር? እንዲህ ያለ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ፍትሐዊና ፍቅር የሚንጸባረቅበት ድርጊት እንደሚሆን አንተም የምትስማማ ይመስለኛል።

አብርሃም፦ አዎ፣ እንደዚያ ይመስለኛል።

ሚካኤል፦ ከዚህም በተጨማሪ አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ በኋላ አምላክ ምን እንዳላቸው እንመልከት። ዘፍጥረት 3:19ን ታነበዋለህ?

አብርሃም፦ እሺ፣ “ከምድር ስለ ተገኘህ፣ ወደ መጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ እንጀራህን በፊትህ ላብ ትበላለህ፤ ዐፈር ነህና ወደ ዐፈር ትመለሳለህ።”

ሚካኤል፦ አመሰግናለሁ። በጥቅሱ መሠረት አዳም ሲሞት ወዴት እንደሚሄድ ነው የተነገረው?

አብርሃም፦ ወደ አፈር።

ሚካኤል፦ ትክክል ነህ። አንድ ሰው፣ ወደ አንድ ቦታ “ተመለሰ” ሊባል የሚችለው ቀድሞውንም እዚያ ከነበረ ነው አይደል?

አብርሃም፦ አዎ።

ሚካኤል፦ ታዲያ አዳም ከመፈጠሩ በፊት የት ነበር?

አብርሃም፦ ሕልውና አልነበረውም።

ሚካኤል፦ ልክ ነህ። ከዚህም ሌላ አምላክ ባስተላለፈው ፍርድ ላይ ስለ ገሃነመ እሳት የተጠቀሰ ነገር እንደሌለ አስተውለህ ይሆናል። አዳም ሲሞት የሚሄደው ወደ መቃጠያ ቦታ ከሆነ አምላክ ይህን እያወቀ አዳም ወደተሠራበት አፈር እንደሚመለስ መናገሩ ፍትሐዊ ይመስልሃል?

አብርሃም፦ አይ፣ ይህማ ፍትሐዊ ሊሆን አይችልም።

ዲያብሎስ የአምላክን ዓላማ ሊያስፈጽም ይችላል?

ሚካኤል፦ ከገሃነመ እሳት ትምህርት ጋር በተያያዘ ግምት ውስጥ ልናስገባው የሚገባ ሌላም ነገር አለ።

አብርሃም፦ ምን?

ሚካኤል፦ ገሃነመ እሳትን “እንደሚቆጣጠር” ማለትም በገሃነም ያሉትን ሰዎች እንደሚያቃጥል የሚታሰበው ማን ነው?

አብርሃም፦ ዲያብሎስ ነው።

ሚካኤል፦ ግንኮ ዲያብሎስ የአምላክ ቀንደኛ ጠላት ነው። አምላክ፣ ሰዎችን ወደ ገሃነመ እሳት በማስገባት ዲያብሎስ እንዲያሠቃያቸው የሚያደርግ ከሆነ አምላክና ዲያብሎስ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ተባብረው የሚሠሩ አይመስልም?

አብርሃም፦ እህም . . . በዚህ መንገድ አስቤው አላውቅም።

ሚካኤል፦ ነጥቡን በምሳሌ ልንገርህ፤ ልጅ አለህ አይደል?

አብርሃም፦ አዎ፣ 15 ዓመት የሆነው ልጅ አለኝ።

ሚካኤል፦ ልጅህ ዓመፀኛ ሆነብህ እንበል። አንተን የሚያሳዝኑ ብዙ መጥፎ ነገሮች ይፈጽማል። በዚህ ጊዜ ምን ታደርጋለህ?

አብርሃም፦ አካሄዱን እንዲያስተካክል እመክረዋለሁ።

ሚካኤል፦ ልጅህ እንዲስተካከል ለመርዳት ደግሞ በተደጋጋሚ ጥረት ታደርጋለህ አይደል?

አብርሃም፦ ይሄማ የት ይቀራል።

ሚካኤል፦ ሆኖም ምንም ያህል ጥረት ብታደርግ የምትነግረውን አልሰማ አለህ እንበል፤ በዚህ ጊዜ ልጁን ከመቅጣት ውጭ ሌላ አማራጭ ይኖርሃል?

አብርሃም፦ አይኖረኝም።

ሚካኤል፦ ይሁንና ለልጅህ መጥፎ ነገሮች በማስተማር ጎጂ ተጽዕኖ የሚያሳድርበት አንድ መጥፎ ሰው እንዳለ ብታውቅ ምን ይሰማሃል?

አብርሃም፦ በጣም እናደዳለሁ።

ሚካኤል፦ እሺ፣ እስቲ አሁን አንድ ነገር ልጠይቅህ፤ ልጅህን ያበላሸው፣ ክፉና መጥፎ ሥነ ምግባር ያለው ሰው እንደሆነ እያወቅህ ልጅህን እንዲቀጣልህ ያንኑ ሰው ትጠይቀዋለህ?

አብርሃም፦ እንዴ! ይሄማ የማይሆን ነገር ነው።

ሚካኤል፦ ሰዎች መጥፎ ነገሮችን እንዲፈጽሙ ተጽዕኖ የሚያሳድረው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው፤ ታዲያ አምላክ፣ እነዚያኑ ሰዎች ለመቅጣት በሰይጣን ዲያብሎስ ይጠቀማል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ይሆናል?

አብርሃም፦ አይ፣ አይሆንም።

ሚካኤል፦ ደግሞስ አምላክ ክፉዎችን በገሃነመ እሳት መቅጣት ቢፈልግ እንኳ ዋነኛ ጠላቱ የሆነው ዲያብሎስ፣ ክፉዎችን በማሠቃየት የአምላክን ፈቃድ የሚፈጽምበት ምን ምክንያት ይኖራል?

አብርሃም፦ ከዚህ ቀደም በፍጹም እንደዚህ አስቤ አላውቅም!

ይሖዋ ክፋትን ሁሉ ያስወግዳል

ሚካኤል፦ ይሁንና አምላክ ክፉዎችን ሳይቀጣ ዝም ብሎ አይተዋቸውም። አካሄዳቸውን ለማስተካከል አሻፈረን በሚሉ ክፉ ሰዎች ላይ እርምጃ ይወስዳል። ይህን ነጥብ የሚያጎላ አንድ የመጨረሻ ጥቅስ አብረን እንመልከት። ጥቅሱ መዝሙር 37:9 ነው፤ ታነበዋለህ?

አብርሃም፦ እሺ፣ “ክፉ ሰዎች ይጠፋሉና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን ምድርን ይወርሳሉ።”

ሚካኤል፦ አመሰግናለሁ። ይሖዋ አምላክ በክፉዎች ላይ ምን ዓይነት እርምጃ እንደሚወስድ አስተዋልክ?

አብርሃም፦ ጥቅሱ አምላክ እንደሚያጠፋቸው ይናገራል።

ሚካኤል፦ ልክ ነህ። በሌላ አባባል ለዘለቄታው ከሕልውና ውጪ ያደርጋቸዋል። ጥሩ ሰዎች ይኸውም ይሖዋን “ተስፋ የሚያደርጉ” ሰዎች ግን በዚህች ምድር ላይ ለዘላለም ይኖራሉ። በእርግጥ ይህን ስል በአእምሮህ ውስጥ አንዳንድ ጥያቄዎች ይፈጠሩ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ ‘ሰዎች መጥፎ ነገር እንዳይሠሩ አምላክ መጀመሪያውኑ ለምን አላስቆማቸውም? ደግሞስ ክፉ ሰዎችን የመቅጣት ዓላማ ካለው እስካሁን ለምን አላጠፋቸውም?’ ብለህ ታስብ ይሆናል።

አብርሃም፦ አዎ፣ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ባውቅ ደስ ይለኛል።

ሚካኤል፦ በሚቀጥለው ጊዜ ስንገናኝ መልሱን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አሳይሃለሁ። *

አብርሃም፦ እሺ፣ ደስ ይለኛል።